የስንዴ ምርት

19 መጋቢት 2023, 09:47 EAT

ዩክሬን እና ሩሲያ በሚሊዮኖች ቶን የሚሰፈር የእህል ምርትን በጥቁር ባሕር በኩል ለማሳለፍ ከወራት በፊት የደረሱት ስምምነት የጊዜ ገደብ ከመጠናቀቁ በፊት እንዲራዘም ተስማሙ።

ምንም እንኳ ሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነት ላይ ቢሆኑም ከዚህ ቀደም ፈርመውት የነበረውን የእህል ማስተላለፍ ስምምነት አራዝመውታል።

ነገር ግን አዲሱ ስምምነት እስከመቼ እንደሚዘልቅ የሚታወቅ ነገር የለም።

ዩክሬን ስምምነቱ ለ120 ቀናት ይቆያል ስትል ሩሲያ ደግሞ ከ60 ቀናት በላይ መዝለቅ አይችልም ብላለች።

ሩሲያ፤ ሞስኮው ላይ የተጣሉ ማዕቀቦች እስካላሉ ድረስ ስምምነቱን ከሁለት ወራት በላይ ማቆየት አልችልም የሚል አቋም ይዛለች።

ሁለቱ አገራት ስምምነቱን ለመጀመሪያ ጊዜ ሲፈርሙ ጉዳዩን ያስተባበሩት ቱርክ እና የተባበሩት መንግሥታት ነበሩ።

በወቅቱ ስምምነቱ ባይደረስ ኖሮ በዓለም አቀፍ ደረጃ የምግብ እጥረት ይከሰታል የሚል ስጋት ነበር።

ዩክሬን የተለያዩ የእህል ምርቶችን በገፍ ከሚያመርቱ የዓለማችን አገራት መካከል አንዷ ናት። ነገር ግን የሩሲያን ወረራ ተከትሎ ዩክሬን ምርቷን በጥቁር ባሕር ወደብ በኩል ማስተላለፍ ሳትችል ቆይታለች።

እንደ የመን ያሉ በምግብ እጥረት እየተቸገሩ አገራት ከዩክሬን የሚመጣ ጥራጥሬ ላይ ጥገኛ ናቸው።

የቱርኩ ፕሬዝዳንት ረሲፕ ጣይብ ኤርዶዋን ቅዳሜ ሩሲያ እና ዩክሬን ስምምነታቸውን ማራዘማቸውን ይፋ አድርገዋል።

ዩክሬን እና ሩሲያ ስምምነታቸውን ያራዘሙት የቀድሞው ስምምነት ሊጠናቀቅ የሰዓታት ዕድሜ ሲቀሩት ነው።

“ይህ ስምምነት ለዓለም የምግብ አቅርቦ ትልቅ ጠቀሜታ አለው። ዩክሬን እና ሩሲያን አመሰግናለሁ። ስምምነቱ እንዲራዘም ጥረዋል። የተባበሩት መንግሥታት ዋን ፀሐፊም እንዲሁ” ብለው ፕሬዝዳንቱ።

ነገር ግን የቱርኩ ፕሬዝዳንትም ሆኑ የተባበሩት መንግሥታት ስምምነቱ ለምን ያክል ጊዜ እንደተራዘመ ያሉት ነገር የለም።

ዩክሬን ስምምነቱ ለአራት ወራት ያክል እንዲቆይ እንደምትሻ ቢነገርም፣ ሩሲያ ግን በግማሽ እንዲያጥር ትሻለች።

በተባበሩት መንግሥታት የሩሲያ አምባሳደር ቫሲሊ ኔቤንዚያ አርብ ዕለት የአውሮፓ ኅብረት፣ ዩናይትድ ኪንግደም እና ዩናይትድ ስቴትስ ማዕቀባቸውን ለማንሳት ሁለት ወር አላቸው ብለው ነበር።

አምባሳደሩ ስምምነቱ እንዲቆይ ከተፈገለ የሩሲያ ግብርና ዘርፍ ላይ ያነጣጠረው ማዕቀብ ይነሳ ብለዋል።

ሞስኮ እንደምትለው ሩሲያውያን አምራቾች የምግብ ምርት እና ማዳበሪያ ለዓለም ገበያ ማቅረብ ቢፈልጉም የተጣለው ማዕቀብ ማነቆ ሆኖባቸዋል።

ሩሲያ፤ ምንም እንኳ ማዕቀብ ቀጥታ የምግብ ምርት እና ማዳበሪያ ላይ ያተኮረ ባይሆንም ክፍያ፣ ኢንሹራንስ እና ትራንስፖርት ላይ የተጣለው ማዕቀብ የወጭ ንግድን አክብዶታል ትላለች።

ባለፈው ኅዳር ዩክሬን ክራይሚያ ውስጥ ጥቃት መፈፀሟን ተከትሎ ሩሲያ ለአጭር ጊዜ ያክል ራሷን ከስምምነቱ ብታገልም ከቀናት በኋላ ተመልሳለች።

የተባበሩት መንግሥታት እንደሚለው ስምምነቱ ከተፈፀመ በኋላ 25 ሚሊዮን ቶን (25 ትሪሊዮን ኪሎ ግራም) የእህል ምርት ከዩክሬን ተነስቶ ወደ ተቀረውን ዓለም አዳርሷል።