March 20, 2023 – BBC Amharic 

የኢራን ፕሬዝዳንት ኢብራሂም ራኢሲ
የምስሉ መግለጫ,ሳዑዲን እንዲጎበኙ የተጋበዙት የኢራን ፕሬዝዳንት ኢብራሂም ራኢሲ

ከ 4 ሰአት በፊት

ሳዑዲ አረቢያ እና ኢራን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን መልሰው ለመጀመር ከተስማሙ ከሳምንት በኋላ ሳዑዲ ለኢራኑን ፕሬዝዳንት የጉብኝት ግብዣ ማቅረቧ ተነገረ።

ኢራን እንዳስታወቀችው ለፕሬዝዳንት ኢብራሂም ራኢሲ ግብዣው የቀረበው ከንጉሥ ሳልማን በተጻፈ ደብዳቤ ሲሆን፣ ከሳዑዲ በኩል ግን ይህን የሚያረጋግጥ ነገር አልተሰማም።

ለዘመናት በጠላትንት ሲተያዩ የቆዩትን ሁለቱን አገራት ያቀራረበችው ቻይና ስትሆን፣ ይህም የአካባቢውን አጠቃላይ ፖለቲካዊ ሁኔታ ይቀይረዋል ተብሎ ይጠበቃል።

የኢራን ከፍተኛ ባለሥልጣን የሆኑት አህመድ ጃምሺዲ በትዊተር ላይ እንዳሰፈሩት፣ ፕሬዝዳንት ራኢሲ ሪያድን እንዲጎበኙ እንደተጋበዙ እና በሁለቱ አገራት መካከል ያለውን ግንኙነት ለማስፋት ኢራን ፍላጎት ስላላት ግብዣውን እንደተቀበሉት ገልጸዋል።

በሌላ በኩል ደግሞ የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሆሲን አሚር፣ ኢራን እና ሳዑዲ በውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደረጃ ንግግር ለመጀመር እንደተስማሙ እና ለዚህም ሦስት ቦታዎች መመረጣቸውን ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።

ነገር ግን ሚኒስትሩ ለስብሰባው የተመረጡትን ቦታዎች እና መቼ ሊካሄድ እንደሚችል አልገለጹም።

አገራቱ በሁለት ወራት ውስጥ ኤምባሲዎቻቸውን እንደሚከፍቱ፣ እንዲሁም የንግድ እና የደኅንነት ግንኙነታቸውን እንደሚጀምሩ አስታውቀዋል።

ከዚህ ቀደም ሁለቱን አገራት ለማቀራረብ በርካታ ሙከራዎች ቢደረጉም ሳይሳኩ ቆይተው አሁን በቻይና ድጋፍ ከስምምነት መድረሳቸውን አሜሪካ እና የተባበሩት መንግሥታትን ጨምሮ በርካቶች በበጎ ተመልክተውታል።

ሳዑዲ አረቢያ ከኢራን ጋር ያላትን ግንኙነት ያቋረጠችው ከሰባት ዓመት በፊት ተቃዋሚ ሰልፈኞች ቴህራን ውስጥ የሚገኘውን ኤምባሲዋን ጥሰው ከገቡ በኋላ ነው።

ይህ የተከሰተው ሳዑዲ ከሽብር ጋር የተያያዘ ድርጊት ፈጽመዋል ያለቻቸውን ታዋቂ የሺአ ሙስሊም መሪ ሼክ ኒምር አል-ኒምርን በሞት መቅጣቷን ተከትሎ ነበር።

ከዚያ ጊዜ በኋላ በሱኒ ሙስሊሞች የምትመራው ሳዑዲ አረቢያ እና ሺአዋ ኢራን በአካባቢው የበላይነትን ለመያዝ በሚል አንዳቸው ሌላኛቸውን ሲከሱ ቆይቷል።

በተጨማሪም ሁለቱ አገራት በየመን እና በሶሪያ ውስጥ ሲካሄዱ በቆዩት እና በሌሎችም በርካታ አካባቢያዊ ግጭቶች ውስጥ ተቃራኒ ኃይሎችን በመደገፍ በእጅ አዙር ሲፋለሙ ቆይተዋል።

በተጨማሪም በአካባቢው የሳዑዲ አረቢያ አጋር የሆነችው እና በተመሳሳይ ጊዜ ከኢራን ጋር ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቷን ካቋረጠችው ባህሬን ጋር ያላትን ግንኙነት ለማሻሻል እንደምትፈልግ የኢራን ባለሥልጣን ተናግረዋል።

ባህሬን ይህንን የኢራን ፍላጎትን በተመለከተ ያለችው ነገር ባይኖርም፣ ቀደም ሲል ኢራን እና ሳዑዲ አረቢያ ግንኙነታቸውን መልሶ ለመጀመር መወሰናቸውን በተመለከተ በውንታዊነት ተቀብላዋለች።

ኢራን በተጨማሪም ዮርዳኖስን እና ተባበሩት አረብ ኤምሬትስን ጨምሮ ከሌሎች የመካከለኛው ምሥራቅ አገራት ጋር ያላትን ግንኙነት ለማሻሻል ፍላጎት እንዳለት ግልጻለች።