March 20, 2023 – BBC Amharic

የታሊባን  ባለስልጣናት

ከ 4 ሰአት በፊት

በአፍጋኒስታን የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ዘመዶቻቸውን የቀጠሩ ባለሥልጣናት ከሥራ እንዲያሰናብቱ ታሊባን አዘዘ።

የመንግሥት ባለሥልጣናት የቀጠሯቸውን ልጆቻቸውን እና ዘመዶቻቸውን በማሰናበት በምትኩ በሌሎች እንዲተኩ እንዲሁም ወደፊት ከዚህ ዓይነት ተግባር እንዲቆጠቡ ታሊባን አሳስቧል።

እንደ አውሮፓውያኑ በ2021 ታሊባን ወደ ሥልጣን ሲመለስ ልምድ ያላቸውን ሠራተኞች ያባረረ ሲሆን፣ ሌሎች ደግሞ አገሪቱን ጥለው ተሰደዋል።

በዚህም ምክንያት ከባለሥልጣናት ጋር ባላቸው ግንኙነት ምክንያት ልምድ የሌላቸው ሠራተኞች በመንግሥት ተቋማት ውስጥ ተቀጥረዋል የሚሉ መረጃዎች ተናፍሰዋል።

መቀመጫውን በፓኪስታን ፔሻዋር ያደረገው አፍጋኒስታን ኢስላሚክ ፕሬስ እንደዘገበው ከሆነ የአፍጋኒስታን ባለሥልጣናት ልጆቻቸውን በመንግሥት መሥሪያ ቤቶች በመሾማቸው ታሊባን ይህንን ለማስተካከል ትዕዛዝ አውጥቷል።

ባለሥልጣናቱ የታዘዙበት ይህ ማስታወቂያ ፎቶ በአስተዳደራዊ ጉዳዮች ቢሮ የትዊተር ገጽ ላይ ተለጥፎ ታይቷል።

ታሊባን መልሶ ሥልጣን ከተቆጣጠረ በኋላ የከፋ የኢኮኖሚያዊ እና የሰብአዊ ቀውስን እየተጋፈጠ ነው።

በአገሪቱ የውጭ ኃይሎች ከሁለት አስርት ዓመታት በላይ የቆዩ ሲሆን፣ በ10 ሺህ ሚቆጠሩ ሰዎች እንዲሞቱ እና በሚሊዮኖች እንዲፈናቀሉ ምክንያት የሆነ ጦርነት ሲያካሂዱ ቆይተዋል።

ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በታሊባን መንግሥት ባለሥልጣናት ላይ ማዕቀብ የተጣለ ሲሆን፣ ባሕር ማዶ የሚገኙ የአሀሪቱ ማዕከላዊ ባንክ ንብረት ታግዷል።

በተጨማሪም በውጭ አገራት የሚገኙ በርካታ የአፍጋኒስታን ንብረቶች የታገዱ ሲሆን፣ ይህም የአገሪቱን ኢኮኖሚ አሽመድምዷል።

አፍጋኒስታን 1 ትሪሊዮን ዶላር የሚገመት የተፈጥሮ ጋዝ እና መዳብን ጨምሮ በርካታ የተፈጥሮ ሃብት እንዳላት ይገመታል። ሆኖም ይህ ሃብት ለአስርት ዓመታት በዘለቀው አለመረጋጋት ምክንያት ጥቅም ላይ መዋል አልቻለም።

የታሊባን መንግሥት በሴቶች ላይ ያለው አሉታዊ አያያዝ እና አመለካከት በዓለም አቀፍ ደረጃ እንዲነቀፍ እና የአገሪቱ ኢኮኖሚ እየተዳከመ ባለበት ጊዜ ከዓለምአቀፉ ሕብረተሰብ እየተነጠለ እንዲሄድ አድርጎታል።

በአሁኑ ወቅት ሴቶች በአብዛኛው አፍጋኒስታን ውስጥ ከሚገኙ ሁለተኛ ደረጃ ደረጃ ትምህርት ቤቶች እና ከዩኒቨርሲቲዎች ታግደዋል።