
ታዋቂው የብዝሃ ሕይወት ሳይንስቲስት ሎሬት ዶ/ር ተወልደ ብርሃን ገብረእግዚአብሄር ከዚህ ዓለም በሞት መለየታቸው ተሰምቷል።
ሎሬት ዶ/ር ተወልደ ብርሃን ባደረባቸው ሕመም በአገር ውስጥ በሕክምና ሲረዱ ቆይተው በ83 ዓመታቸው ትናንት ሰኞ መጋቢት 11/2015 ለማክሰኞ አጥቢያ 9፡00 ላይ በሞት መለየታቸውን ደራሲ እና ጋዜጠኛው ዘነበ ወላ አስታውቋል።
ዶክተር ተወል ደብርሃን በአካባቢ ጥበቃ ዘርፍ አገልግሎት የተከበረ ሥም ያላቸው ሲሆን፤ በዘርፉ ላደረጉት ምርምር እና በጉዳዩ ዙሪያ ከፍተኛ ግንዛቤ እንዲፈጠር ላደረጉት ጥረት በፈረንጆቹ 2000 (Right Livlihood Award) ሽልማትን አግኝተዋል፡፡
በተጨማሪም፣ በፈረንጆቹ 2006 ዓመት የተባበሩት መንግሥታት በአካባቢ ጥበቃ ዙሪያ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ላደረጉ ሰዎች የሚሰጠውን Champions of the Earth ሽልማት አግኝተዋል፡፡ ከተማሩበት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ደግሞ በ1997 የክብር ዶክትሬት ዲግሪ ተቀብለዋል፡፡
ሎሬት ዶ/ር ተወልደ ብርሃን የሦስት ሴቶች ልጆች አባት ሲሆኑ ከ60 በላይ ሌሎች ልጆችን ያሳደጉ ልበ ቀና ሰው እንደነበሩ ይነገርላቸዋል።
ታዋቂው የአካባቢ ጉዳይ ሳይንስቲስት ዶክተር ተወልደ ብርሃን ገብረእግዚአብሄር የደራሲ ስብሐት ገብረእግዚአብሔር ታናሽ ወንድም መሆናቸው ይታወቃል።
ምንጭ፦ አዲስ ማለዳ