
21 መጋቢት 2023, 07:56 EAT
አሜሪካ የሩሲያ ወታደሮች በዩክሬን እየፈጸሙት ያለውን “የጦር ወንጀል” እንዲያቆሙ የቻይናው ፕሬዚዳንት በቭላድሚር ፑቲን ላይ ጫና እንዲያደርጉ ጠየቀች።
አሜሪካ ይህንን ያለችው የቻይናው ፕሬዚዳንት ዢ ጂንፒንግ ከጦርነቱ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ሞስኮ ማቅናታቸውን ተከትሎ ነው።
ፕሬዚዳንት ፑቲን እና አቻቸው ዢ ጂንፒንግ ዛሬ መጋቢት 12፣ 2015 ዓ.ም እንደገና ተገናኝተው ይወያያሉ።
የዋይት ሃውስ የብሔራዊ ደህንነት ምክር ቤት ቃለ አቀባይ ለቻይናው ፕሬዚዳንት ባስተላለፉት መልዕክት ፕሬዚዳንት ፑቲን ወታደሮቻቸውን ከዩክሬን እንዲያወጡ እንዲያሳስቧቸው ጠይቀዋል።
ጆን ኪርቢ የተኩስ አቁም ፍላጎት ብቻውን በቂ እንዳልሆነም ነው የተናገሩት።
“ፕሬዚዳንት ዢ በዩክሬን ከተሞች፣ ሆስፒታሎች እና ትምህርት ቤቶች ላይ የሚደርሰውን የቦምብ ጥቃት፣ የጦር ወንጀሎች እና ጥሰቶችን እንዲያቆሙ እና ወታደሮቻቸውን እንዲያስወጡ በፕሬዚዳንት ፑቲን ላይ ግፊት እንደሚያደርጉ ተስፋ እናደርጋለን” ብለዋል።
አክለውም “ነገር ግን ቻይና በተደጋጋሚ እንደምታደርገው የተኩስ አቁም ጥሪ ልታደርግ ትችላለች። ይህም ሁኔታ የሩሲያ ጦር በዩክሬን ሉዓላዊ ግዛት ውስጥ እንዲቆይ የሚያደርግና የሩሲያን ህገወጥ ወረራም በተሳሳካ ሁኔታ እውቅና የሚሰጥ ስለሆነም ስጋት አለን” ብለዋል።
- የሕዝብ ተወካዮች የአፍሪካ ኅብረት መንግሥትን እና የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊትን እንዲያሸማግል ጠየቁ21 መጋቢት 2023
- ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን በጦር ወንጀል ለፍርድ ይቀርቡ ይሆን?18 መጋቢት 2023
- ዓለም አቀፉ የወንጀል ፍርድ ቤት በፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ላይ የእስር ትዕዛዝ አወጣ17 መጋቢት 2023
ፑቲን በዩክሬን ያለውን ከፍተኛ ቀውስ ለመፍታት የቻይናው ፕሬዚዳንት ዢ ጂንፒንግ ባቀረቡት ባለ 12 ነጥብ እቅድ ላይ እንደሚወያዩ ተናግረዋል።
“ለድርድር ሁልጊዜም ክፍት ነን” በማለት ፕሬዚዳንት ፑቲን ተናግረዋል። የሁለቱ አገር መሪዎች እርስ በርስ የተጠራሩት “ውድ ጓደኛ “ በሚል ነው።
ቻይና አንድ ዓመት ያለፈውን ጦርነቱን ለማስቆም እቅድ ያወጣች ሲሆን ይህም ግጭት በዘላቂነት የማቆምና የሰላም ድርድርን ያካተተተ ነው።
የቻይና እቅድ ዩክሬን ለማንኛውም ውይይት ቅድመ ሁኔታ አድርጋ ያቀረበችውን የሩሲያ ወታደሮች ከግዛቷ የመውጣት ጉዳይ አላካተተም።
ይልቁንም የሁሉንም አገሮች ሉዓላዊነት ባከበረ መልኩ፣ ሁሉም አካላት ምክንያታዊ እንዲሆኑና ከግጭት እንዲቆጠቡ እንዲሁም ሁኔታውን ቀስ በቀስም ለማርገብ ያለመ እንደሆነም ተነግሯል።
ዕቅዱ በሩሲያ ላይ የተጣለውን የአንድ ወገን ማዕቀብ ያወገዘ ሲሆን ይህም የዩክሬን አጋሮች በሆኑት ምዕራባውያን ላይ ያነጣጠረ እንደሆነም ተጠቅሷል።