የዕብራይስጥ መጽሐፍ ቅዱስ

ከ 5 ሰአት በፊት

እጅግ ጥንታዊ፣ የተሟላው የዕብራይስጥ መጽሐፍ ቅዱስ በእስራኤል ቴል አቪቭ ከተማ ለእይታ ቀረበ።

መጽሃፍ ቅዱሱ በዕብራይስጥ ቋንቋ የተጻፈ ሲሆን ለህዝብ እይታ ከቀረበ በኋላም በጨረታ ይሸጣል ተብሏል።

መጽሃፍ ቅዱሱ ከ1 ሺህ 100 ዓመታት በፊት በግብጽ ወይም ሌቫንት በተሰኘው ግዛት እንደተጻፈ ይታመናል።

24ቱንም የዕብራይስጥ መጻህፍቶችን በአንድ ጥራዝ የያዘ፣ ስርዓተ ነጥብ፣ አናባቢ፣ ዘዬዎችንና የግርጌ ማስታወሻዎችን የያዘ መጽሃፍ ቅዱስ ነው ተብሏል።

መጽሃፍ ቅዱሱ በግንቦት ወር በኒውዮርክ በሚገኘው ሶቴቢስ ጨረታ ድርጅት ለጨረታ የሚቀርብ ሲሆን ከ30 እስከ 50 ሚሊዮን ዶላርም ይሸጣል ተብሎ ይጠበቃል።

ከዚህ ቀደም የአሜሪካ ህገ መንግሥት የመጀመሪያ እትም በ43.2 ሚሊዮን ዶላር ከሁለት ዓመት በፊት የተሸጠ ሲሆን የመጽሃፍ ቅዱሱ ሽያጭ ከዚህ ከበለጠም እጅግ ውድ በሆነ ዋጋ የተሸጠ ታሪካዊ ሰነድም ይሆናል ተብሏል።

የዕብራይስጥ መጽሃፍ ቅዱስ በሶስት ክፍሎች የተከፈሉ 24 መጻሕፍትን የያዘ ሲሆን የክርስትና እምነት ተከታዮችም ብሉይ ኪዳን ብለው ይጠሯቸዋል።

የዕብራይስጡ መጽሐፍ ቅዱስ ጽሁፎች እስከ መካከለኛው ዘመን መጀመሪያ ድረስ የማይታወቁ ነገሮችን ይዞ የነበረ ሲሆን ማሶሬቴስ በመባል የሚታወቁት አይሁዳውያን ሊቃውንት የጹሁፉን ደረጃ የሚያስተካክል ማስታወሻዎችን ፈጠሩ።

በ930 አካባቢ ተጠርዞ የወጣው መጽሃፍ ቅዱስ የመጀመሪያው የማሶሬቲክ ጽሑፍ ተደርጎም ነው የሚወሰደው።

ሆኖም በአውሮፓውያኑ 1947 በሶሪያ አሌፖ ከተማ በደረሰ የእሳት ቃጠሎ ጉዳት 487 ገጾችን ከያዘው መጽሃፍ ቅዱስ ውስጥ 295ቱ ብቻ ናቸው የተረፉት።

በአሁኑ ወቅት ለዕይታ የቀረበው መጽሃፍ ቅዱስ እንደሚያሳየው በ900 አካባቢ የተሰባሰበ ሲሆን የጨረታው ድርጅት እንዳለው 12 ገጾች ብቻ ናቸው የጎደሉት።

“ለመጀመሪያ ጊዜ የተሟላ የዕብራይስጥ መጽሃፍ ቅዱስ ከነ አናባቢዎቹ፣ ከግርጌ ማስታወሻም ጋር የተገኘ ሲሆን ይህም ትክክለኛው ጽሑፍ እንዴት መጻፍ እንዳለበት የሚጠቁም ነው” ሲሉም የአይሁድ የሥነ ጥበብ ሥራ ባለሙያ የሆኑት ሻሮን ሚንትስ ለአጃንስ ፍራንስ ፕሬስ የዜና ወኪል ተናግረዋል።