April 9, 2023
በተስፋለም ወልደየስ
የአማራ ክልል ልዩ ኃይል አባላትን “በፌደራል እና በክልል የጸጥታ ተቋማት ማደራጀትን” አስመልክቶ በተላለፈው ውሳኔ ላይ የሚነሳው ጥያቄ “ከወቅታዊ ሁኔታ አንጻር ትክክል ቢሆንም፤ በሀገር ደረጃ የተወሰነው ውሳኔ የሚጠቅም ነው” ሲሉ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ዶ/ር ይልቃል ከፋለ ተናገሩ። ይህን ውሳኔ በተመለከተ በተሰራጨ “አጥፊ ፕሮፖጋንዳ” ምክንያት፤ የተወሰኑ የአማራ ክልል ልዩ ኃይል አባላት ከካምፖቻቸው በመውጣት ወደ ከተሞች እና ወደ የቤተሰቦቻቸው መሄዳቸውንም ርዕሰ መስተዳድሩ ገልጸዋል።
ዶ/ር ይልቃል ይህን ያሉት የአማራ ክልል ወቅታዊ ሁኔታን በተመለከተ ለክልሉ ቴሌቪዥን ጣቢያ ዛሬ እሁድ ሚያዝያ 1፤ 2015 በሰጡት መግለጫ ነው። በክልሎች የሚገኙ ልዩ ኃይሎችን በተለያዩ የጸጥታ ማዋቅሮች “መልሶ የማደራጀት ውሳኔ”፤ “በፌደራል መንግስት እና በክልል መንግስታት ስምምነት የተወሰነ” መሆኑን የተናገሩት ዶ/ር ይልቃል፤ ይህን ተከትሎ የወጣው የማስፈጸሚያ ፕሮግራም “በሁሉም ክልሎች ተግባራዊ የሚደረግ” መሆኑን አስታውቀዋል።
“የአማራ ክልል ልዩ ኃይልን በተለየ መንገድ የሚጎዳ ነገር እና ውሳኔ ለብቻው አልተደረገም። ወጥ እና ሀገራዊ ውሳኔ ነው የተደረገው። በሁሉም ክልል የሚፈጸም ነው። ለቀጣይ ሀገር ግንባታም የሚጠቅም፣ አብሮነትን የሚያሳድግ ነው ብለን እናምናለን” ሲሉ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር በዛሬው መግለጫቸው አጽንኦት ሰጥተዋል። ሆኖም የአማራ ክልል ከሌላው ክልል ተነጥሎ፤ “ጥያቄ የሚያነሳበት መንገድ ምንድነው የሚለው በደንብ መታየት አለበት” ብለዋል።
“ከወቅታዊ ሁኔታ አንጻር የሚነሳው ጥያቄ ትክክል ቢሆንም፤ በሀገር ደረጃ አፈጻጸሙ መሄድ ያለበት እና የሚጠቅም መሆኑን ደግሞ በውል መገንዘብ ይገባናል። ስለሆነም ከዚህ ችግር በመተባበር፣ በመወያየት እና ችግርን እና ቅሬታን በሰላምና በውይይት በመፍታት መውጣት እንችላለን” ሲሉ ዶ/ር ይልቃል ተስፋቸውን ገልጸዋል። በሀገር ደረጃ የተወሰነውን ውሳኔ በአማራ ክልል ተፈጻሚ ከመደረጉ አስቀድሞ፤ “የጸጥታ መዋቅሩን ደረጃ በደረጃ ለማወያየት ጥረቶች መደረጋቸውን” ለዚህ በማሳየነት ጠቅሰዋል።
ሆኖም “ውይይቱ ከመጠናቀቁ በፊት በአንዳንድ የልዩ ኃይል አካባቢዎች ከካምፕ የመውጣት እንቅስቃሴ” መታየቱን የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር በዛሬው መግለጫቸው አስታውቀዋል። ይህ የሆነው አስቀድሞ በተሰራ “አጥፊ የፕሮፖጋንዳ ስራ” እና “በመረጃ ጉድለት” መሆኑንም አመልክተዋል። በክልሉ ህዝብ እና በልዩ ኃይል አባላት ላይ የተደረገው ቅስቀሳ፤ “ልዩ ኃይል ትጥቅ ሊፈታ ነው። ልዩ ኃይል ሊበተን ነው” የሚል መሆኑንም ገልጸዋል።
በዚህ ቅስቀሳም የተወሰኑ የክልሉ የልዩ ኃይል አባላት “ከካምፕ በመውጣት ወደ አንዳንድ የከተማ አካባቢዎች እና ቤተሰቦቻቸው ጋር መሄዳቸውን” ርዕሰ መስተዳድሩ በዛሬው መግለጫቸው ላይ ይፋ አድርገዋል። “ይሄም ሊሆን የቻለው በአጥፊ ፕሮፖጋንዳው እየታገዘ፣ በተወሰነ ደረጃም ቢሆን በአፈጻጸም ላይ በታየ ክፍተት ነው” ሲሉም የድርጊቱን መንስኤ አብራርተዋል።
“አጥፊ ፕሮፖጋንዳ ላይ ተመስርቶ ውሳኔ መወሰን ጎጂ ነው። በእያንዳንዱ ልዩ ኃይል ባለበት ካምፕ ችግር እንኳ ቢኖር፤ ተወያይቶ መፍትሔ መድረስ የሚቻልበት ዕድል አለ” ያሉት ዶ/ር ይልቃል፤ ከካምፕ የወጡ የክልሉ ልዩ ኃይል አባላት ወደ ምድብ ቦታቸው እንዲመለሱ ጥሪ አቅርበዋል። “ይሄ ልዩ ኃይል የሚበተን፣ ትጥቅ የሚፈታ አይደለም” ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ ይልቁንም የቀረበለት ቀጣይ “የአደረጃጀት እና የላቀ ተልዕኮ”፤ በፌደራል እና በክልል የጸጥታ መዋቅሮች ገብቶ “ኃላፊነቱን እንዲወጣ የሚያስችል” መሆኑን ጠቁመዋል።
ዶ/ር ይልቃል በዛሬው መግለጫቸው ደጋግመው ያነሱት ጉዳይ፤ በፌደራል መንግስት የተላለፈው የልዩ ኃይሎችን በሌሎች የጸጥታ መዋቅሮች ውስጥ የማስገባት ውሳኔ “የአማራን ክልል ልዩ ኃይልን በተለየ መንገድ ትጥቅ ማስፈታት እና ለመበተን የታለመ ዓላማ የሌለው መሆኑን” ነው። ይህንኑ ገለጻ ባለፉት ቀናት በዚህ ጉዳይ ላይ ተከታታይ መግለጫ እየሰጡ ያሉ ባለስልጣናትም አጽንኦት ሰጥተው ሲያስተጋቡት ቢቆዩም፤ በአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች ተቃውሞዎች መካሄዳቸውን ቀጥለዋል።
የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር በመግለጫቸው፤ “በአንዳንድ ከተሞች አካባቢ የሰላማዊ ሰልፍ እንቅስቃሴ፣ የአድማ ጥሪ እና የሰዎች እና የተሽከርካሪዎች እንቅስቃሴን የመገደብ አዝማሚያዎች እየታዩ” መሆናቸውን አረጋግጠዋል። ዶ/ር ይልቃል “በመረጃ ክፍተት” ምክንያት እንደተከሰቱ የገለጿቸው እነዚህን ድርጊቶች፤ የክልሉ ህዝብም ሆነ የየአካባቢው ህብረተሰብ “በጽሞና ሊመለከታቸው” እንደሚገባ አሳስበዋል።
Tweet
በደጀን ከተማ በተቃውሞ መንገድ በመዘጋቱ፤ የሀገር አቋራጭ ትራንስፖርት አገልግሎት ተቋረጠ።
በከተማይቱ በዛሬው ዕለት የንግድ እንቅስቃሴ መቆሙ እና የአገልግሎት ሰጪ ተቋማት መዘጋታቸውም
ተገልጿል።
ዝርዝሩ፦ https://ethiopiainsider.com/2023/10539/ #Ethiopia #Amhara
Translate Tweet
40 Retweets 4 Quotes 142 Likes
“የአማራ ክልል በጦርነት የከረመ ክልል ነው። በጦርነቱ ምክንያት ህዝባችን የተጎሳቆለ ነው። በጦርነቱ ምክንያት የተጎዳው መሰረተ ልማት እና የህብረተሰብ ክፍል ገና ማገገም አልቻለም። ከዚህ ችግር ሳናገግም ወደ ሌላ ችግር መሸጋገር የአማራ ክልል ህዝብ በሁለንተናዊ መልኩ እንዲደቅ ማድረግ ነው” ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ የክልሉ ህዝብ “ሊደርስ የሚችለውን ጉዳት አስቀድሞ በማጤን ማስከን” እንደሚገባ አሳስበዋል። ዶ/ር ይልቃል በአንዳንድ አካባቢዎች በግልም ሆነ በቡድን ደረጃ ይደረጋሉ ያሏቸው “ህገ ወጥ እንቅስቃሴዎች”፤ ለአማራ ህዝብ የማፈይዱ በመሆኑ መቆም አለባቸው ብለዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)