April 10, 2023

በአማኑኤል ይልቃል

በአማራ ክልል፤ ሰሜን ሸዋ ዞን፤ አጣዬ ከተማ ዛሬ ከንጋት ጀምሮ የተከፈተው በከባድ መሳሪያ የታገዘ ተኩስ እስከ አመሻሽ ድረስ መቀጠሉን ስድስት የከተማዋ ነዋሪዎች ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናገሩ። የአጣዬ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ በከተማዋ ተኩስ እንዳለ ቢያረጋግጡም፤ በየትኛው አካል የተፈጸመ እንደሆነ እስካሁን አለመታወቁን ገልጸዋል።

የኤፍራታና ግድም ወረዳ ዋና ከተማ በሆነችው አጣዬ ከተማ ተኩስ የተከፈተው፤ ዛሬ ሰኞ ሚያዝያ 2፤ 2015 ከንጋቱ 12 ሰዓት ገደማ ጀምሮ መሆኑን የከተማይቱ ነዋሪዎች ተናግረዋል። የመጀመሪያው የተኩስ ድምጽ የተሰማው “አላላ” በተባለው የኤፍራታና ግድም ወረዳ ቀበሌ አካባቢ እንደሆነ ነዋሪዎቹ አስረድተዋል። 

ፎቶ፦ ከ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ማህደር የተወሰደ

አላላ ቀበሌ፤ በአማራ ክልል የኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን ጅሌ እና ጥሙጋ ወረዳ ውስጥ ላሉ ቀበሌዎች አዋሳኝ ቦታ ነው። ከዚሁ ቀበሌ የተነሳው ተኩስ፤ ጠዋት አንድ ሰዓት ገደማ ላይ ወደ መሃል የከተማው አከባቢ እንደተስፋፋ ነዋሪዎቹ ገልጸዋል። በንግድ ስራ ላይ የተሰማሩ አንድ የከተማዋ ነዋሪ “ሁላችን ወደ መደበኛ ስራችን እየተሰማራን፤ ህጻናት ይዘን ወደ ትምህርት ቤት እየወሰድን ባለበት ነው የተኩስ ድምጽ የተሰማው” ሲሉ ከተማዋ ላይ ድንገተኛ ተኩስ መከፈቱን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አብራርተዋል።

የአጣዬ ከተማ ነዋሪዎች “በዲሽቃ እና ሌሎች ከባድ መሳሪያዎች የታገዘ” ሲሉ የጠሩት ተኩስ የተከፈተው፤ የከተማዋን ዙሪያ ከከበቡት ተራሮች ላይ “በሁሉም አቅጣጫ ነው” ይላሉ። የአጣዬ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ አሳልፍ ደርቤ፤ “አጣዬ ዙሪያውን ጦርነት አለ” ሲሉ ተኩሱ በሁሉም አቅጣጫ የሚሰማ መሆኑን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አረጋግጠዋል።

የተኩስ ልውውጡ በማን መካከል እየተደረገ ስለመሆኑ ከ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ጥያቄ የቀረበላቸው ከንቲባው፤ “ገና ያልተጣራ ስለሆነ ይሄ ነው ማለት አልችልም። ዞሮ ዞሮ ዙሪያውን ጦርነት አለ” የሚል ምላሽ ሰጥተዋል። የከተማዋ ነዋሪዎች ግን ተኩሱ የተከፈተው በ“ሸኔ” ታጣቂ ቡድን ነው ባይ ናቸው። “ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ያነጋገረቻቸው አንድ የከተማዋ ነዋሪ፤ “ሸኔ ነው ለማለት ያስቻለን፤ መሳሪያ አጣጣላቸው፣ ተኩስ አከፋፈታቸው፣ አጋጣሚዎችን የመጠቀም ሁኔታቸው ሲታይ የተቀናጀ ነገር ነው” ሲሉ አስረድተዋል። 

ተመሳሳይ ሀሳብ የሚያነሱ ሌላ ነዋሪም፤ ጥቃቱን ሊከላከሉ የሞከሩ አርሶ አደሮች የሚተኮስባቸው መሳሪያ “ከአቅም በላይ” መሆኑን ጠቅሰው፤ “ገበሬ ቢሆን ተመሳሳይ መሳሪያ ነው የሚኖረው” የሚል መከራከሪያ አንስተዋል። እንደ ነዋሪዎቹ ገለጻ የዛሬው ተኩስ የተከፈተው፤ በአጣዬ ከተማ ዙሪያ ባለው ተራራ ላይ ሰፍረው የነበሩ የአማራ ክልል ልዩ ኃይል አባላት ከሁለት ቀን በፊት ከአካባቢው መንቀሳቀሳቸውን ተከትሎ ነው። 

የከተማይቱ ነዋሪዎች ከሰሞኑ ከልዩ ኃይል የአደረጃጀት ለውጥ ጋር በተያያዘ በመንግስት የተጀመረው ስራ፤ በአካባቢው ተሰማርተው ለነበሩት የልዩ ኃይል አባላት መነሳት በምክንያትነት ይጠቅሳሉ። ስማቸው እንዳይገለጽ የጠየቁ አንድ የከተማዋ ነዋሪ፤ “እስካሁን በነበረው ሁኔታ፤ ‘አስፈላጊ ነው’ ተብሎ ክልሉ ያሰፈራቸው ልዩ ኃይሎች ነበሩ። ሰሞኑን ወደ ፌደራል እና መከላከያ ትቀላቀላላችሁ ተብሎ ተራራውን ይዘው የነበሩት ወርደው ነው ያሉት። ወደ ሌላ አካባቢ፣ ወደ ቤተሰብ የሄዱም አሉ” ብለዋል።

ዛሬ በከተማዋ ላይ ተኩስ የከፈቱት ታጣቂዎች፤ የልዩ ኃይል አባላት እንደሌሉ መረጃ ደርሷቸው ሊሆን እንደሚችል እኚሁ ነዋሪ ግምታቸውን ገልጸዋል። ከአዲስ አበባ በ271 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የምትገኘው አጣዬ ከተማ ባለፉት ዓመታት ከአስር ጊዜ በላይ ባስተናገደችው ግጭት እና ጥቃት ምክንያት ተደጋጋሚ ውድመት ማስተናገዷ የሚታወቅ ነው። 

በአማራ ክልል ስር ባሉት የኤፍራታና ግድም እንዲሁም የጅሌ ጥሙጋ አካባቢዎች በተደጋጋሚ ለሚከሰቱት ግጭቶች፤ በአካባቢው ይንቀሳቀሳል የሚባለው የ “ሸኔ” ታጣቂ ቡድን፣ የአማራ ልዩ ኃይል አባላት እና የፋኖ ታጣቂዎች በተለያዩ ወገኖች ተጠያቂ ሲደረጉ ቆይተዋል። የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ዶ/ር ይልቃል ከፋለ ከሁለት ሳምንት በፊት ለክልሉ ቴሌቪዥን ጣቢያ በሰጡት ቃለ መጠይቅ፤ በሰሜን ሸዋ ዞን እና በኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን ውስጥ የሚታዩ ቀጣይነት ያላቸው ግጭቶችን “በዘላቂነት መቋጨት” አለመቻሉን አስታውቀው ነበር።

በዛሬው የተኩስ ልውውጥ የተጎዱ እና የተገደሉ ሰዎች እንዳሉ የሚገልጹት የአጣዬ ከተማ ነዋሪዎች፤ ሆኖም የተከፈተው ተኩስ ባለመርገቡ ምክንያት ምን ያህል ሰዎች ጉዳት እንደደረሰባቸው ማረጋገጥ አለመቻላቸውን አስረድተዋል። አንድ የከተማዋ ነዋሪ በበኩላቸው የዛሬው ተኩስ መበርታቱን ተከትሎ፤ ሴቶች እና ህጻናት ወደ አጎራባች ቀበሌዎች መሸሻቸውን ጠቅሰዋል። “እኛ ንብረት እንዳይዘረፍ እንጠብቅ ብለን ነው እዚህ የቀረነው። አሁንም ተደብቀን ነው ያለነው” ብለዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)