አንዳንድ ተአምረኛ ቤተሰቦች
አንዳንድ ተአምረኛ ሰዎች አሉ። አበርክቷቸው ጎልቶ የሚነገርላቸው፣ ስራቸው የሚመሰክርላቸው ፣ ስማቸው ከመቃብርም በላይ የዋለ። አንዳንዴ እነዚህ ሰዎች ከአንድ የቤተሰብ ጣራ ስር ማዕድ ተጋርተው ፣ አንድ ላይ ጠጥተው የወጡ ይሆናሉ። የሚከተሉት ቤተሰቦች ይገርሙኛል…
፩- የነጋድራስ ተሰማ እሸቴ ቤተሰብ
ሞያ የተካኑ ባለ ዘርፈ ብዙ ሙያ ባለቤት ነበሩ። በኢትዮጵያ የመጀመሪያው መካኒክ ናቸው ተብሎ ይነገራል። በተጨማሪም ሎሬት ፀጋዬ ገ/መድሕን የመሰከረላቸው ጎበዝ ገጣሚ፣ ድምጻዊ፣ ማሲንቆ ተጫዋች፣ ሰዓሊ፣ የቅርጻ ቅርጽ ባለሞያ ነበሩ። ከሁሉም ደግሞ ነጋድራስ ተሰማ በአለቃ ገብረሃና ደረጃ መጠቀስ የሚችሉ ወግ አዋቂ ነበሩ።
ነጋድራስ ተሰማ ጥቂት የማይባሉ የሀገር ውስጥ እና የባህር ማዶ ቋንቋዎችንም ይናገሩ ነበር። ከሀገር ውስጥ አማርኛ ኦሮምኛና ሃረሪኛን ከውጭ ደግሞ አረብኛ ፣ ጀርመንኛ፣ ጣሊያንኛና ፈረንሳይኛን ይናገሩ የነበሩ ባለብዙ ቋንቋ ተናጋሪ ነበሩ።
* ክቡር አቶ ይድነቃቸው ተሰማ ፦ የነጋድራስ ተሰማ እሸቴ ልጅ ናቸው። ፣ ጎበዝ ተማሪና ሁለገብ ስፖርተኛ ነበሩ። በአትሌቲክስ በቦክስ ስፖርት ፣ በአጭር ርቀት ሩጫ የተዋጣላቸው ስፖርተኛ የነበሩ።
ጋሽ ይድነቃቸው ተሰማ በአለም አቀፍ ተቋማት ውስጥ ስለነበሩበት የሃላፊነት እርከን እንዲሁም ስላበረከቱት አስተዋጽኦ እንዘርዝር ብንል ቦታ አይበቃንም። ጋሼ ከሀገራቸውን አልፈው አህጉራቸውን በከፍተኛ ደረጃ በማገልገል አኩሪ ታሪክ ጽፈዋል፡፡
በአፍሪካ ብሔራዊ ኦሎምፒክ ኮሚቴ መስራችነት እንዲሁም የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት በመሆን ትልቅ አስተዋፅኦ አበርክተዋል።
፪- የገብሩ ደስታ ቤተሰብ ፦ አባት ከንቲባ ገብሩ የጎንደር ከንቲባ የነበሩና የአማርኛ ሰዋሰው ፀሀፊ ናቸው።
* ክብርት ዶ/ር ስንዱ ገብሩ፦ የገብሩ ደስታ ልጅ። በንጉሱ ዘመን የመጀመሪያዋ ሴት የፓርላማ አባል ሲሆኑ የመጀመሪያዋ ሴት ርእሰ መምህርም ናቸው። በጣሊያን ወረራ እንኳ ሃገራቸውን ጥለው አልተሰደዱም። የሀገር ፍቅር ልባቸው ላይ የሚንቦጎቦግ ብርቱ ሴትም ናቸው።
ክብርት ስንዱ ገብሩ በርካታ ቲያትሮችንም ለመድረክ አብቅተዋል። ብዙ ቋንቋ ተናጋሪም ነበሩ። የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲም ለሀገራቸው ባበረከቱት አስተዋፅኦ የክብር ዶክትሬት ሰጥቷቸዋል።
* እማሆይ ፅጌ ማርያም ገብሩ ፦ ሌላኛዋ የቤተሰቡ ልጅ። አለማቀፍ እውቅናን ያገኙ ፣ በዘመናዊ የሙዚቃ ታሪክ ፋና ወጊ የነበሩ የሙዚቃ ሰው ናቸው። በቫዮሊን እና በፒያኖ ሙዚቃዎችን በማቀናበር በቀዳሚነት የሚጠቀሱ ናቸው።
እማሆይ በተለያየ ጊዜ የተለያዩ ሀገሮች ውስጥ ስለቆዩ ነው መሰለኝ ልክ እንደ እህታቸው ስንዱ የተለያዩ ቋንቋዎችን አቀላጥፈው ይናገራሉ። ከሁሉም ሙያዊ አበርክቷቸው አለም አቀፍ እውቅናን ያስገኘላቸው። ሀገራቸውንም ያስጠራላቸው ሆኗል።
፫- የገብረ እግዚአብሄር ቤተሰብ ፦
* ስብሃት ለአብ ገብረ እግዚአብሄር፦ ከአድዋ ርባገረድ ተነስቶ የአማርኛ ስነፅሁፍ ሜዳ ላይ እንደ ልቡ የሆነና ትልቅ ቦታንም ያገኘ ነው። አማርኛ ስነፅሁፍን አንድ ደረጃ ያሻገረ ድንቅ ደራሲ። የጠለቀና የሰፋ የንባብ ልምድ ባለቤትም ነው። ስለ ስብሃት ተወርቶ አያልቅም።
* ዶ/ር ተወልደብርሃን ገብረእግዚአብሄር ፦ በአካባቢ ጥበቃ ዘርፍ አገልግሎት የተከበረ ሥም ያላቸው ናቸው። ዶክተር ተወልደ በዘርፉ ላደረጉት ምርምርና ከፍተኛ ግንዛቤ እንዲፈጠር ላደረጉት ጥረት እውቅናን አግኝተዋል። ትልልቅ የትምህርት ተቋማትንም በሃላፊነት መርተዋል። የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሳይንስ ፋኩልቲ ዲን ነበሩ። የአስመራ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ነበሩ፡፡
ዶ/ር ተወልደ የተባበሩት መንግሥታት በአካባቢ ጥበቃ ዙሪያ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ላደረጉ ሰዎች የሚሰጠውን “Champions of the Earth” ሽልማትንም አግኝተዋል፡፡ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የክብር ዶክትሬትም ሰጥቷቸዋል፡፡
፬- የገብረ የሐንስ ቤተሰብ ፦
* ዶ/ር እጓለ ገብረየሐንስ ፦ እጓለ በመጀመሪያ መንፈሳዊ ትምህርትን ተማሩ። ሲማሩ ከነበሩበት ተመርጠው ለመንፈሳዊ ትምህርት ወደ ግሪክ አቀኑ።
ኋላ ላይ እዛው ባሉበት ሀገር ነገረ መለኮትን ፣ የግሪክ ስነፅሁፍ እና ፍልስፍናን አጠኑ። ጎበዝ ተማሪ እንደነበሩ ይነገራል። ለፍልስፍና ትምህርት ጉጉ የነበሩት እጓለ በዚህ ብቻ ግን አላበቁም ወደ ጀርመን አቅንተው ተማሩ። እዛም አላበቁም ወደ እንግሊዝ ሃገር ሄደው ተምረዋል።
ታዲያ ይሄ ሁሉ የዶ/ር እጓለ ትምህርት ፣ ምርምር ፣ እውቀት ፣ ሃሰሳ … ምናልባት በክፍለ ዘመኑን ከተፃፉት ድንቅ መፅሀፎች ተርታ የሚሰለፍ «የከፍተኛ ትምህርት ዘይቤ» የሚባል ቅርስን ያበረከተ ይመስለኛል።
* ሃይሉ ገብረዮሐንስ፦ (ገሞራው) ህይወቱ ሁሉ ትግል የነበረ ገጣሚ ነው። ቀ.ኃ.ስ እያለ የሚገጥማቸውን ግጥሞች የሰሙ የአገዛዙ ሰዎች «መርዛሙ ብእረኛ» ይሉት ነበር።
በተደጋጋሚ እየታሰረ ፣ ከትምህርቱም እየተባረረ ነው ኋላ ላይ ከሀገር የወጣው። በስደት ብዙ ተንከራቷል። ያረፈውም ውጪ ሀገር ነበር። እድሜልኩን የተሻለች ኢትዮጵያ እንድትፈጠር በብእሩ ታግሏል። ለዚህ ውለታ የተከፈለው ክፍያ ግን በስደት መኖርን ነው።
ከላይ የተጠቀሱት ባለታሪኮች እያንዳንዳቸው በሀገር ደረጃ የላቀ አበርክቶ ያላቸው ነበሩ። ቢለዩንም ስማቸውና ስራቸው የሚረሳ አይመስለኝም። ይብቃን መሰለኝ (…)
