April 21, 2023

በአማኑኤል ይልቃል

የዎላይታ ሕዝቦች ነፃነት ንቅናቄ (ዎሕነን) የተሰኘ አገር አቀፍ የፖለቲካ ፓርቲ፤ መስራች ጠቅላላ ጉባኤውን ነገ ቅዳሜ በወላይታ ሶዶ ከተማ ሊያደርግ ነው። በተለያዩ አካባቢዎች በሚኖሩ የወላይታ ተወላጆች ላይ እየደረሰ ይገኛል ያለውን “ማንነት ተኮር ጥቃት ማስቆም” ከቀዳሚ አጀንዳዎቹ አንዱ እንደሆነ የገለጸው አዲሱ የፖለቲካ ፓርቲ፤ የወላይታ የክልልነት ጥያቄን እንደሚደግፍም አስታውቋል። 

በተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች ውስጥ በአመራርነት በሰሩ እና አባል በነበሩ ግለሰቦች አስተባባሪነት እየተመሰረተ ያለው ዎሕነን፤ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ጊዜያዊ የምዝገባ ሰርተፊኬት ያገኘው ከሶስት ወራት በፊት በታህሳስ ወር መጀመሪያ ላይ ነበር። ፓርቲው ጊዜያዊ የምዝገባ ሰርተፊኬቱን ካገኘ በኋላ እስካለፈው መጋቢት ወር ድረስ ህጋዊ እውቅና እንዲያገኝ የሚያስችለውን መስራች አባላትን የማሰባሰብ ስራ ሲያከናውን እንደነበር ከምስረታ አስተባባሪዎች ውስጥ አንዱ የሆኑት አቶ ወልደማርያም ልሳኑ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል።

የወላይታ ህዝብ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ውስጥ “ተበትኖ” የሚኖር መሆኑን የሚገልጹት እኚሁ አስተባባሪ፤ በዚህም ምክንያት የሚቋቋመው የፖለቲካ ፓርቲ “ሀገር አቀፍ” እንዲሆን መደረጉን አስረድተዋል። በ2011 ዓ.ም በወጣው የኢትዮጵያ የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ሥነ ምግባር አዋጅ መሰረት፤ ሀገር አቀፍ የፖለቲካ ፓርቲ ለመመስረት አስር ሺህ መስራች አባላት ሊኖሩ ይገባል። ከእነዚህ መስራች አባላት ውስጥ 40 በመቶው የአንድ ክልል መደበኛ ነዋሪ መሆን እንዳለባቸው የደነገገው አዋጁ፤ ቀሪዎቹ ቢያንስ በሌሎች አራት ክልሎች ውስጥ መደበኛ ነዋሪ መሆን እንዳለባቸው አስፍሯል። 

በዚህም መሰረት ዎሕነን 40 በመቶ የሚሆነውን የመስራች አባላት ፊርማ የሰበሰበው፤ ከነባሩ የደቡብ ክልል እንደሆነ ሌላኛው የፓርቲው የምስረታ አስተባባሪ አቶ ታምራት ማጨ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገልጸዋል። ቀሪዎቹን የፓርቲው መስራች አባላት ፈርማ የማሰባሰብ ስራ የተከናወነው፤ በትግራይ፣ ኦሮሚያ፣ ጋምቤላ እና አፋር ክልሎች እንዲሁም በአዲስ አበባ ከተማ መሆኑንም አክለዋል።

የፓርቲው ምስረታ አስተባባሪዎች የመስራች አባላትን ፊርማ ለማሰባሰብ፤ ወደ ትግራይ ክልል የተጓዙት ባለፈው ወር መሆኑን አቶ ታምራት ተናግረዋል። “እዚያ ካሉ የፖለቲካ ኃይሎች ጋር በመተባበር፤ መቀሌ ከተማ አካባቢ ትኩረት አድርገን ነው የሰራነው” ሲሉም በትግራይ ክልል የነበረውን የመስራች አባላት ፊርማ የማሰባሰብ ሂደት አስረድተዋል። እስከ መጋቢት ወር ድረስ በተደረገው ፊርማ ማሰባሰብ ብቻ 13 ሺህ መስራች አባላት መመዝገባቸውን ሌላኛው የምስረታ አስተባባሪ ጠቅሰዋል።

በአምስት ክልሎች እና በአዲስ አበባ ከተማ እስካሁን ድረስ 30 ሺህ ገደማ እጩ አባላትን መመዝገቡ የተነገረለትን የዎላይታ ሕዝቦች ነፃነት ንቅናቄ ፓርቲ ማቋቋም ካስፈለገባቸው ገፊ ምክንያቶች ውስጥ፤ በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች በሚኖረው የወላይታ ህዝብ ላይ “በተደጋጋሚ የሚደርሰው ማንነት ተኮር ጥቃት” አንዱ እንደሆነ አቶ ወልደማርያም ተናግረዋል። የደቡብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ደኢህዴን) ከፍተኛ አመራር የነበሩት እና ባለፈው ምርጫ እናት ፓርቲን በመወከል የተወዳደሩት የአሁኑ የዎሕነን ምስረታ አስተባባሪ፤ በወላይታ ህዝብ ላይ የሚደርሰውን ጥቃት “በኢትዮጵያዊ ሆደ ሰፊነት ያየንባቸው ብዙ ጊዜያት ነበሩ” ይላሉ። 

የወላይታ ተወላጆች ጉዳዩን “በሆደ ሰፊነት” ለማለፍ ቢሞክሩም “የሚደርሰው ጥቃት አልቆመም” የሚሉት አቶ ወልደማርያም፤ ይህ ያልሆነበት አንዱ ምክንያት “ህዝቡ የሚደርስበትን ነገር በተደራጀ መልኩ ለመመከት የሚያስችል እና በሰላማዊ መንገድ ሊያታግል የሚችል ተቋም እስካሁን ድረስ ወላይታ ላይ ባለመፈጠሩ [ነው]” ሲሉ ይሞግታሉ። እርሳቸው ይህን ይበሉ እንጂ፤ ለወላይታ ህዝብ መብት እና ጥቅም ለመታገል መቋቋማቸውን ያስታወቁ የፖለቲካ ፓርቲዎች በዞኑ ለዓመታት ሲንቀሳቀሱ ቆይተዋል።

የዎላይታ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ዎሕዴግ) እና ዎላይታ ብሔራዊ ንቅናቄ (ዎብን) የሚል ስያሜ ያላቸው እነዚህ ፓርቲዎች፤ በምርጫ ቦርድ የተመዘገቡት በክልላዊ ፓርቲነት ነው። ሁለቱ ተቃዋሚ ፓርቲዎች፤ “ቱሳ” የሚል ጥምረት በመፍጠር በስድስተኛው ሀገር አቀፍ ተወዳድረዋል። በወላይታ ዞን በተካሄደው አጠቃላይ ምርጫ፤ ከሁለቱ ተቃዋሚዎች በተጨማሪ 10 የፖለቲካ ፓርቲዎች ዕጩዎችን አቅርበው መወዳደራቸው አይዘነጋም። በምርጫው ላይ ከተወዳደሩት ፓርቲዎች ውስጥ ገዢው ብልጽግና ፓርቲ፣ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ)፣ እናት፣ አዲስ ትውልድ እንዲሁም ነጻነት እና እኩልነት ፓርቲዎች ይጠቀሳሉ። 

በባለፈው ምርጫ ዋነኛ መከራከሪያ ከነበሩ ጉዳዮች ውስጥ፤ የወላይታ የክልልነት ጥያቄ የሚጠቀስ ነው። ራስን ችሎ በክልልነት የመደራጀት ጥያቄ ጠንከር ባለ መልኩ ከሚነሳባቸው የደቡብ ክልል ዞኖች ውስጥ አንዱ በሆነው የወላይታ ዞን፤ ጉዳዩ በዞኑ አመራሮች ጭምር ድጋፍ ያገኘ ነበር። የወላይታ ዞን ምክር ቤት የክልልነት ጥያቄውን በታህሳስ 2011 ዓ.ም. ማጽደቁን ተከትሎ፤ የዞኑ አስተዳደር ክልላዊ መንግስቱን የሚያደራጅ  ሴክሬታሪያት ጽህፈት ቤት አቋቁሞ ወደ ተግባራዊ እንቅስቃሴ ጭምር ተገብቶ እንደነበር አይዘነጋም። 

Tweet

Ethiopia Insider

@ethiopiainsider

የወላይታ ዞን ምክር ቤት ዛሬ ባካሄደው አስቸኳይ ጉባኤ የወላይታ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት እንዲቋቋም

ውሳኔ አሳለፈ።የክልሉን መንግስት ለማደራጀት የሚያስችል የሴክሬቴሪያት ጽ/ቤት እንዲቋቋም እና የቅድመ

ዝግጅት ስራዎች እንዲከናወኑም ወስኗል።

Translate Tweet

Image


15
Retweets
9 Quotes 58 Likes 1 Bookmark

ይህንን እንቅስቃሴ ሲደግፉ የነበሩት የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ዳጋቶ ኩምቤ እና ሌሎች አመራሮች ከታሰሩ በኋላ ግን የክልልነት ጥያቄው ተቀዛቅዞ ቆይቷል። በክልል የመደራጀት ጥያቄውን አጽድቆ የነበረው የወላይታ ዞን ምክር ቤትም፤ ከቀደመ ውሳኔው የሚቃረነውን በ“ክላስተር የመደራጀት” ሃሳብ በሐምሌ 2014 ዓ.ም ባደረገው ስብሰባ ደግፏል። በገዢው የብልጽግና ፓርቲ የቀረበው ይህ የውሳኔ ሃሳብ፤ የወላይታ ዞን በደቡብ ክልል ስር ካሉ ሌሎች አስር መዋቅሮች ጋር በመሆን አንድ ክልል እንዲመሰርት የሚያደርገው ነው። 

“ደቡብ ኢትዮጵያ” የሚል ስያሜ የሚይዘውን አዲሱን ክልል ለመመስረት ባለፈው ጥር ወር መጨረሻ ላይ ወላይታ ዞንን ጨምሮ በአስራ አንድ መዋቅሮች ህዝበ ውሳኔ ተካሄዷል። ሆኖም በወላይታ ዞን የተካሄደው ህዝበ ውሳኔ በምርጫ ቦርድ አማካኝነት ውድቅ ተደርጓል። ቦርዱ ይህን ውሳኔ ያሳለፈው፤ በዞኑ በመራጮች ምዝገባ ሂደት እና ድምጽ በተሰጠበት ወቅት “መጠነ ሰፊ ጥሰቶች” በማግኘቱ መሆኑን አስታውቋል። እነዚህን ጥሰቶች የፈጸሙ አካላት በህግ ተጠያቂ ሳይደረጉ፤ ህዝበ ውሳኔውን በድጋሚ ለማድረግ እንደሚቸገር ምርጫ ቦርድ ማስታወቁ አይዘነጋም። 

በነገው ዕለት የምስረታ ጉባኤውን የሚያካሄደው ዎህነን በፕሮግራሙ ካካተታቸው ጉዳዮች ውስጥ የክልልነት ጥያቄ አንዱ መሆኑን ከፓርቲው ምስረታ አስተባባሪዎች አንዱ ይሆኑት አቶ ወልደማርያም ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። የወላይታ ህዝብ በተለያዩ ጊዜያት በተደረጉ የመዋቅር ለውጦች ምክንያት ተጎጂ መሆኑን የሚገልጹት አስተባባሪው፤ “ክልሎች በሚፈርሱበት ሰዓት የመጀመሪያው ተጠቂ” እንደሆነም ያነሳሉ። የወላይታ ዞን በክልልነት እንዲደራጅ ጥያቄ በቀረበበት ወቅት “ጥቃቶች” እንደደረሱበትም ያክላሉ። 

Tweet

Ethiopia Insider

@ethiopiainsider

ምርጫ ቦርድ በወላይታ ዞን የተደረገው ህዝበ ውሳኔ እና የመራጮች ምዝገባ ውድቅ ተደርጎ በድጋሚ

እንዲካሄድ ወሰነ፡፡ቦርዱ በዞኑ የተካሄደው ህዝበ ውሳኔ ውድቅ ያደረገው፤ “መጠነ ሰፊ” ጥሰቶች

በመፈጸማቸው መሆኑን አስታውቋል፡፡

https://ethiopiainsider.com/2023/9832/

Translate Tweet

Image

· 3,311 Views

5 Retweets 3 Quotes 13 Likes

ዎሕነን የወላይታን የክልልነት ጥያቄ እንደሚደገፍ የሚገልጹት አቶ ወልደማርያም፤ ፓርቲው በ“እውነተኛ ህብረ ብሔራዊ ፌደራሊዝም የሚያምን” እንደሆነ አስረድተዋል። የወላይታ ህዝብ በዚህ ስርዓት ውስጥ ተጠቃሚ እንዲሆን መስራት፤ ሌላኛው የፓርቲ ዓላማ መሆኑንም አመልክተዋል። ህዝቡ በፌደራሊዝም ስርዓቱ  ከሚጠቅምባቸው ጉዳዩች ውስጥ፤ ወላይትኛ የፌደራል የስራ ቋንቋ መደረጉ አንዱ መሆኑን በማሳያነት ጠቅሰዋል። ወላይትኛ የፌደራል የስራ ቋንቋ ቢሆን፤ “መንግስት በሚያግባባ ቋንቋ ሰፊውን የገጠሩን ማህበረሰብ mobilize በማድረግ ለልማት መጠቀም የሚያስችል መሰረት እንዲኖረው [ያስችለዋል]” ይላሉ የፓርቲው ምስረታ አስተባባሪ።  

የዎላይታ ሕዝቦች ነፃነት ንቅናቄ ነገ ቅዳሜ ሚያዝያ 14፤ 2015 በወላይታ ሶዶ ከተማ በሚያካሄደው መስራች ጠቅላላ ጉባኤው፤ እነዚህን እና ሌሎች ዓላማዎቹ በዝርዝር የተካተቱበትን የመመስረቻ ጽሁፍ፣ ፕሮግራም እና ህገ ደንብ ይጸድቃል ተብሎ ይጠበቃል። በነገው ጉባኤ የፓርቲው ፕሬዝዳንት፣ ምክትል ፕሬዝዳንት እና ዋና ጸሀፊን ጨምሮ ሌሎች አመራሮች ምርጫም ይከናወናል። ይህንኑ የምስረታ ጉባኤ ለመከታተል፤ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ታዛቢዎቹን ወደ ስፍራው መላኩን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አረጋግጧል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)