የቤት ሠራተኛ

28 ሚያዚያ 2023

መጋቢት 02/2015 ሥልጠና ተጀምሯል። ሥልጠናው የሚሰጠው በነጻ ነው። የዕድሜ ገደብም አልተቀመጠለትም።

ለዚህም የሚሆኑ ከ70 በላይ የሥልጠና ማዕከላት ተዘጋጅተዋል።

ቅድሚያ የሚሰጠው ከዚህ በፊት ወደ ተለያዩ አረብ አገራት ደርሰው ለተመለሱት ነው።

ይህ በውጭ አገራት የሥራ ዕድል ለሚፈልጉ የተዘጋጀ ሥልጠና ነው።

ማንኛውም ሠርቶ መለወጥ የሚፈልግ ሰው ሥልጠናውን ወስዶ ወደ ውጭ አገር ሄዶ መሥራትም ይችላል ተብሏል።

ሥልጠናው ቋንቋን ጨምሮ በመዳረሻ አገራት ያለውን ባህል፣ ሃይማኖት እና የሥራ ሁኔታን የሚያጠቃልል ነው።

ከሥልጠናው በኋላ ምዘና የሚኖር ሲሆን ብቁ ለሆኑትም የምስክር ወረቀት ይሰጣል።

በመጀመሪያው ዙር 67 ሺህ የሚጠጉ ዜጎች ሥልጠናውን አጠናቀዋል። በሁለተኛው ዙር ደግሞ 68 ሺህ የሚጠጉት እየተሳተፉ ነው።

ይህ እየተከናወነ ያለው ወደ መካከለኛው ምሥራቅ በተለይም ወደ ሳዑዲ አረቢያ 500 ሺህ ቤት ሠራተኞችን ለመላክ ስምምነት በመኖሩ መሆኑን የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን ደጋግመው ዘግበዋል።

የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር የኮሙኒኬሽን ሥራ አስፈፃሚ የሆኑት አቶ አበበ አለሙ ግን በተቋሙ በኩል ከሳዑዲ አረቢያ የቀረበ ቁርጥ ያለ ቁጥር አለመኖሩን ለቢቢሲ ተናግረዋል።

“500 ሺህ በሚል በማኅበራዊ ሚድያ የሚዘዋወረው ምንጩ የሚታወቅ አይደለም” ሲሉም ያሰምሩበታል።

መሥሪያ ቤቱ በተያዘው በጀት ዓመት 3.7 ሚሊዮን የሥራ ዕድል ለመፍጠር አቅዷል። “ከዚህ ውስጥ 100 ሺህ ብቻ ነው በውጭ አገር ተጠቃሚ እናደርጋለን ብለን ያቀድነው” ሲሉም የመንግሥትን ዕቅድ ያብራራሉ።

በኮቪድ ወረርሽኝ ተቋረጠ እንጂ ከሳዑዲ አረቢያ ጋር የነበረው ስምምነት እስከ አውሮፓውያኑ 2018 የተደረሰ ነበር።

“የሠራተኞች መሠረታዊ መብት እንዲጠበቅ በሚል ነው አሁን እንደ አዲስ እየተነሳ ያለው” ብለዋል ኃላፊው።

ለሥራ የሚሄዱ ኢትዮጵያውያን የሥራ ቆይታቸው በሚፈጽሙት ስምምነት መሠረት ከሁለት እስከ ሦስት ዓመት ሊቆይ የሚችል ነው።

ይህ ስምምነት በቅርቡ ከሳዑዲ የተመለሱትን አይመለከትም። ለዚህም ሕጋዊ አይደላችሁም በሚል በመመለሳቸው ምክንያት መሆኑን የጠቀሱት ኃላፊው “ወደ ሌላ አገር መሄድ ግን ይችላሉ” ሲሉ ገልጸዋል።

ለጊዜው ሳዑዲ አረቢያ ያቀረበችው ፍላጎት የቤት ሠራተኞችን ለመውሰድ ነው።

እንደ አቶ አበበ ገለጻ “ከረዥም ጊዜ አኳያ ግን የሠለጠኑ እና በከፊል የሠለጠኑትን ወደ ውጭ ለመላክ ቅድመ-ዝግጅት አለ። የተጀመረው ሥልጠናም የዚያ አካል ነው።”

“ስምምነቱ አሠሪዎችን ይቆጣጠራል”

ከዚህ ቀደም በመንግሥት፣ በሠራተኛ አገናኝ ኤጀንሲዎች ወይም በግል በሚደረግ ጥረት የሥራ ዕድሉ ይገኝ ነበር። በዚህ ውስጥ የመንግሥት ተሳትፎ ‘ብዙ’ አልነበረም። አሁን ግን በመንግሥት ዕውቅና የሚሄዱበት ዕድል ነው የተመቻቸው።

የሥራና ክህሎት ሚኒስትሯ ሙፈሪያት ካሚል ለአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን ከሰሞኑ እንደተናገሩት ከዚህ በፊት ከኳታር፣ ከዮርዳኖስ፣ ከሳዑዲ አረቢያ እና ከዩናይትድ አረብ ኢሚሬቶች ጋር ሕጋዊ ስምምነት እንዳለ ጠቁመው፤ ወደ አፍሪካ እና የአውሮፓ አገራትም ወደፊት እንደሚኖር አስታውቀዋል።

ኢትዮጵያ ለዜጎቿ የተሻለ ክፍያ፣ መብት እና ደኅንነታቸው እንዲጠበቅ ከተለያዩ አገራት ጋር መስማማቷን የጠቀሱት ሚኒስትሯ፣ መንግሥትም በውጭ አገራት የሚሠሩ የዜጎቹ መብት እና ጥቅም እንዲከበር ክትትል እንደሚያደርግ ተናግረዋል።

“[የተደረሰው ስምምነት] አሠሪዎችን ይቆጣጠራል። አንድ ቀንም ደመወዛቸው ሳይከፈላቸው ማደር የለበትም። ደኅንነታቸው እና ጤንነታቸው እንዲጠበቅ ይደረጋል” ሲሉ አቶ አበበ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

መንግሥት ሕገወጥ የተባሉ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎችን ከሳዑዲ አረቢያ መልሷል
የምስሉ መግለጫ,መንግሥት ሕገወጥ የተባሉ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎችን ከሳዑዲ አረቢያ መልሷል

አሳሳቢው የ‘ካፋላ’ ሥርዓትስ?

ባንቺ ይመር የእኛ ለእኛ በስደት ማኅበር መሥራች ናት። ባንቺ አሁን የምትገኘው ካናዳ ቢሆንም በሊባኖስ ለሰባት ዓመት ያህል በሰው ቤት ሠርታለች።

ማኅበሩ ትኩረቱን በሊባኖስ በሚኖሩ የቤት ሠራተኛ ኢትዮጵያውያን ዙሪያ ቢያደርግም፣ በሌሎች አገራት የሚገኙ ኢትዮጵያውያን የቤት ሠራተኞችንም ያግዛል።

የእነዚህን ዜጎች የሰብዓዊ መብት ማስከበር እና የበጎ አድራጎት ሥራ ላይ መሠማራቱን ትገልጻለች።

መንግሥት በተለይም ወደ ሳዑዲ አረቢያ ቤት ሠራተኞችን ለመላክ መዘጋጀቱን ተገቢ አይደለም ስትል ትሞግታለች።

ሳዑዲ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ሠራተኞች ከአሠሪዎቻቸው በተጨማሪ በመንግሥት ደረጃ የሰብዓዊ መብት ጥሰት እየተፈጸመባቸው መሆኑን ታነሳለች።

“ከአስር ዓመታት በላይ የዘለቀ የጉልበት ብዝበዛ፣ እስር ቤት ውስጥ ማሰቃየት፣ ንብረታቸውን ነጥቆ ከአገር ማባረርን ጨምሮ ብዙ ዓይነት ጥሰቶች እየተፈጸመባቸው ነው። [የሳዑዲ መንግሥት] በሚያሠማራቸው የፀጥታ ኃይሎች፣ በእስር ቤት ጥበቃዎች ነው ዜጎቻችን የሚዘረፉት እና የመብት ጥሰት የሚፈጸምባቸው” በማለት ይህ መጀመሪያ መፈታት ያለበት መሆኑን አጽንኦት ሰጥታ ትጠቅሳለች።

ሌላው የምታነሳው ስጋት ካፋላ የተሰኘውን ሠራተኞችን ወደ አገር ለማስገባት እና ለመቅጠር የሚያገለግል ሥርዓት ነው። ከሠራተኞች ቅጥር ጋር በተያያዘ የዋስትና ወይም “የስፖንሰርነት ሥርዓት” ነው።

በዚህ አሠራር አንድ አሰሪ ከሌላ አገር የሚቀጥራትን የቤት ሠራተኛ በተመለከተ በርካታ መብቶች እንዲኖረው ያደርጋል።

“ካልተስማማቸው መመለስ ይችላሉ”

አንዲት ሠራተኛ ባስመጣት ቀጣሪ ቁጥጥር ስር ብቻ ሆና ነው ባለችበት አገር ውስጥ መሥራት የምትችለው። ነገር ግን ከአሰሪዎቿ ቤት ወይም የሥራ ቦታ ከወጣች ሕገ ወጥ ስደተኛ መሆንን ያስከትልባታል ይህ የካፋላ ሥርዓት።

ይህ ቁጥጥር ደግሞ ሠራተኛዋ በቀጣሪዎቿ በደል እና ጥቃት ቢደርስባት እንኳን ሌላ አማራጭ እንዲኖራት የማያደርግ አስገዳጅ እና የማይቀየር ነው።

ይህ የካፋላ ሥርዓት በሊባኖስ፣ ዮርዳኖስ፣ በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች፣ በኩዌት፣ በባህሬይን፣ በኦማን፣ በሳዑዲ አረቢያ እና በሌሎችም የባሕረ ሰላጤው አገራት ይተገበራል።

በዚህ ሕግ አማካኝነት ሠራተኞቹ መደራጀት አይችሉም። በአጠቃላይ ሕይወታቸው በአሠሪያቸው ቁጥጥር ስር እንዲወድቅ በማድረጉ ለጥቃት እንዲጋለጡ ማድረጉን የሚያሳዩ በርካታ ጥናቶች አሉ።

ስደተኛ ሠራተኞች ከመደበኛው የአገራቱ የአሰሪ እና ሠራተኛ ሕግ የተገለሉ ናቸው። ይህ በልማድ ሳይሆን በሕግ የተደነገገ ነው።

“በዚህ የካፋላ ሥርዓት ዜጎቻችን ሳዑዲ የሚገቡት በስፖንሰሮቻቸው ስም ነው። እየታዩ ያሉትም እንደባርያ በመሆኑ፣ ዘመናዊ ባርነት ነው” ትላለች ባንቺ።

ኤጀንሲዎች ወይም ቀጣሪዎቻቸው “[ሠራተኞቹ] ከኤርፖርት እንደወጡ ነው መታወቂያቸውን፣ ፓስፖርታቸውን እና ያላቸውን ሰነድ ፈትሽው የሚቀበሉት። ይህንን እንዳያደርጉ የአገሪቱ መንግሥት ቢከለክልም ማንም አያከብረውም” ስትል ስጋቷን ታስቀምጣለች።

አቶ አበበ አለሙ እንደሚሉት አሁን ተግባራዊ እየተደረገው አሰራር “ዜጎቻችን በአግባቡ ሄደው በሚያጋጥማቸው ሁኔታ ባይስማሙ እንኳን ወደ አገራቸው እንዲመለሱ የሚደረገበት ሁኔታ ተዘጋጅቷል” ይላሉ።

የቤት ሠራተኛ ምስል

“ከሚሠሩበት ቤት መጥፋት ወንጀል ነው”

“ለሳዑዲ ብቻ ብለን ያዘጋጀነው ነገር የለም። መካከለኛ ምሥራቅ በሚል ነው እየተሠራ ያለው። በዚህም ሕገ ወጥ አሠራርን ለመከላከል እና አገርም ከዚህ እንድትጠቀም ማድረግ መቻል ነው” ብለዋል አቶ አበበ አለሙ።

ወደ ውጭ አገራት በመሄድ ከሚሠሩ ኢትዮጵያውያን ጋር በተያያዘ ሌላው የሚነሳው ጥያቄ፣ የሚያገኙት ደመወዝ ከሌሎች አገራት አቻ ሠራተኞች አንጻር ዝቅተኛ መሆኑ ነው።

በሳዑዲ አረቢያ በነበራቸው ቆይታ ከፍተኛ የሠራተኛ ፍላጎት መኖሩን ማረጋገጣቸውን የጠቀሱት ወይዘሮ ሙፈሪያት በበኩላቸው፤ ሠራተኞች ትርጉም ያለው የደመወዝ ጭማሪ እንዲደረግ፣ መብትና ደኅንነታቸው እንዲጠበቅ ተነጋግረናል ብለዋል።

ስምምነቱን ከዚህ በፊት ሠራተኞች በሕገወጥ መንገድ ሲኖሩ ሕጋዊ ከለላ እንዳይኖራቸው ይደረጉ የነበሩትን ችግሮች እንደሚቀርፍ አብራርተዋል።

የዜጎች ስምሪት እንደ ከዚህ ቀደሙ በግለሰቦች መልካም ፈቃድ ላይ የተመሠረተ ሳይሆን፤ መንግሥት ለመንግሥት በሚደረግ ጠንካራ የድጋፍ አና የክትትል ሥርዓት ላይ የተመሠረተ ይሆናል ብለዋል።

እንዴት መቆጣጠር ይቻላል?

በሳዑዲ አረቢያ ውስጥ በሕገወጥነት በተለያዩ አስርቤቶች በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን እንዳሉ የመብት ድርጅቶች በተደጋጋሚ ያወጧቸው ሪፖርቶች ያመለክታሉ።

ባንቺ እንደምተለውም በተለያዩ አገራት ውስጥ በቤት ሠራተኝነት ያሉ ኢትዮጵያውያን ጉዳይ እጅግ የከፋ መሆኑን በመጥቀስ፣ “የነበረው ችግር ሳይፈታ ግማሽ ሚሊዮን ዜጎችን በድጋሚ መላኩ ተገቢ አይደለም” ትላልች።

“የኢትዮጵያም ሆነ የሳዑዲ መንግሥታት መብታችሁን እጠብቃለሁ ቢሉም፣ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሠራተኞች ያሉበትን ሁኔታ እና ችግራቸውን ለማወቅ የሚስችል አቅም የላቸውም።”

ባንቺ ጨምራም ከዚህ በፊት ተመሳሳይ ስምምነት የፈጸሙ አገራት ቢኖሩም የዜጎቻችው ሕይወት ምንም ዓይነት መሻሻል እንዳላሳየ ትናገራለች።

“አንድ ሰው ቤት ውስጥ በር ተቆልፎበት ከቤት የማይወጣ ከሆነ፤ ስልክ የሚከለከል ከሆነ ምን እንደገጠመው ማወቅ አይቻልም። ስለዚህም የዜጋችን መብት እና ጥቅም ለመጠበቅ አስቸጋሪ ይሆናል” ትላለች።

ከዚያ ይልቅ ከዚህ ቀደም በመብት ድርጅቶች ብዙ የተባለለት እና “የሠራተኞችን መብት ይገፋል” በሚል አገራቱ እንዲያስወግዱት ሲጠየቁ የቆየው “የካፋላ ሥርዓት መነሳት ወሳን ነው” ትላለች ባንቺ።

“የካፋላ ሥርዓቱ ከተነሳ ማንኛውም ሠራተኛ ቤት ተከራይተው ሥራቸውን ሰርተው ወደ ቤታቸው የሚመለስበት፤ ቀጣሪዎቹ ጋር ሆኖ መሥራት ከፈለገም በራሳቸው የሚወስኑበት ዕድልን ይፈጥራል።”

በዚህም የመኖሪያ እና የሥራ ፈቃዳቸው እንዲሁም ሁሉም ሕጋዊ ሰነዶቻቸው በእጃቸው ላይ ስለሚሆኑ ለጥቃት እና ለበደል የመጋለጥ ዕድላቸው በእጅጉ የቀነሰ ይሆናል የምትለው ባንቺ፣ እነዚህ ነገሮች በቅድሚያ መስተካከል እንዳለባቸው ታሳስባለች።

በዚህ ረገድ በመዳረሻ አገራት የሚገኙ ኤምባሲዎች ሠራተኞች ያሉበትን ሁኔታ ቁጥጥር እና ክትትል ማድረግ የሚያስችላቸው ሥርዓት መዘርጋቱን ደግሞ ሚኒስትሯ ሙፈሪያት ካሚል ተናግረዋል።