April 29, 2023 – Konjit Sitotaw 

ወደ ደብረ ኤልያስ፣ ጎጃም፣ የገባው ሁለት አውቶብስ ታጣቂ በኮማንደር ደጉ እና ኮሚሽነር አለኸኝ እንደሚመራ ታወቀ
ህዝቡን ሊያሸብር የገባው ታጣቂ ኃይል ዛሬም አልወጣም

“በደብረ ኤልያስ በረሃው አካባቢ ፋኖ ይሰለጥናል” በሚል ሰበብ ከሁለት አውቶብስ በላይ የአማራ ልዩ ኃይል ልብስ የለበሱ ታጠቂዎች ገብተዋል። ይህ ኃይል የሚመራው የአብይ አህመድ ኦህዴድ/ኦነግ አገዛዝ ተላላኪ ሆኖ በሚያገለግለው ምሰራቅ ጎጃም ዞን አስተዳደር መሆኑ ተለይቷል።
በዛሬው ዕለት የውስጥ የመረጃ ምንጮች እንደገለፁት ይህ፣ ፀረ-አማራ ኃይል የሚመራው በኮማንደር ደግዋለ እና በኮሚሽነር አለኸኝ መሆኑ ተረጋግጧል። የወሰዱት ኃይል በረሀው አካባቢ የሚገኘው ተክለሃይማኖት ገዳም ዙሪያ መቀመጡ ተገልጿል።

ከዚህ ቀደም በተመሳሳይ በደብረ ኤልያስ ሥላሴ ገዳም “ፋኖ ይሰለጥናል” በሚል ገዳሙ ላይ ተኩስ በመክፈት 11 ፀበልተኞችን እና መነኮሳትን መግደላቸውን እና ቀሳውስትን ማቁሰላቸውን ኢሰመጉ አረጋግጧል። ዛሬም የተክለ ሃይማኖት ገዳም አደጋ ላይ መውደቁ ተገልጿል።

በአካባቢው የሚኖረው አርሶ አደር በተደጋጋሚ በዞኑ አስተዳደሮች በሚደርስበት ጥቃት ምክንያት አልምቶ መኖር አለመቻሉን በምሬት ገልጿል።
በምስራቅ ጎጃም ዞን የሚኖር የአማራ ህዝብ በደብረ ኤልያስ እና በቸር ተከል ህዝብ እንዲሁም ገዳማት ላይ በመንግስት ታጣቂዎች የሚደርሰውን ጥቃት አውቆ ከጎናችን በመሆን ሊያግዝን ይገባል ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል።

የደብረ ኤልያስም ሆነ የቸር ተከል ህዝብ ላለፉት ዕመታት ምንም የመሰሠተ ልማት አውታር ያላገኘ እና በራሱ ትግል ለፍቶ የሚኖር ማህበረሰብ ስለሆነ ዛሬም ህዝቡ ጥያቄ ሳያቀርብ “ወታደር እየላኩ የህዝቡን ሠላም የሚነሱ አመራሮችም ለይተናቸዋል፤ አደብ ሊገዙ ይገባል” ሲሉ አስጠንቅቀዋል።