መንግስት የገቢ ግብርን እንዲቀንስ የሚጠይቅ ሰላማዊ ሰልፍ ለማካሄድ መታሰቡ ተገለጸ።
የኢትዮጵያ ሰራተኞች ማህበራት ኮንፌደሬሽን (ኢሰማኮ) መንግስት የገቢ ግብርን እንዲቀንስ ለመጠየቅ አዲስ አበባን ጨምሮ በአምስት ከተሞች ሰላማዊ ሰልፍ ለማድረግ ማቀዱን ገልጿል።
የኮንፌደሬሽኑን ፕሬዝዳንት ካሳሁን ፎሎን ጠቅሶ #አል_ዐይን አማርኛ በሰራው ዘገባ ሰልፉ ከፊታችን ባለው የሰራተኞች ቀን (ሜይ ዴይ) በአዲስ አበባ፣ ድሬዳዋ፣ አዳማ፣ ሀዋሳ፣ ጅማና ሌሎችም ከተሞች እንደሚደረግ ተናግረዋል ብሏል።
የሰልፉ ዋነኛ ዓላማ የተባለውም፥ ቆይታ፤ ሰራተኛው በኑሮ ውድነቱ መኖር ባለመቻሉ የገቢ ግብርን እንዲቀንስ ለመጠየቅ ሲሆን በተጨማሪም ዝቅተኛ የደሞዝ ወለል እንዲወሰን፣ የኤጄንሲ ሰራተኞች 20/80 ክፍያ ገቢራዊት እንዲሁም የመደራጀት መብትን ለመጠየቅ ያለመ መሆኑን አንስተዋል።
ይህን ጥያቄ ለመንግስት የሚያቀርቡና ከተለያዩ የሰራተኛ ማህበራት ይውጣጣሉ የተባሉ በመቶ ሽህዎች የሚቆጠሩ ሰልፈኞች የፊታችን ሰኞ ድምጻቸውን ያሰማሉ ተብሎ ይጠበቃል ሲል ዘገባው አክሏል።
ሰልፉ ከሚመለከተው አካል ፈቃድ ስለማግኘቱ እንዲሁም የት እና በምን ሁኔታ ይካሄዳል የሚለው ዝርዝር መረጃ በዘገባው አልተካተተም።
“መንግሥት ለውይይት በሩን ከፍቶ የሠራተኞችን ጥያቄ መመለስ፤ የሠራተኛ ታክስን መቀነስ አለበት” | አቶ ካሳሁን ፎሎ
በተለያዩ ተቋማት ውስጥ በኤጀንሲዎች የተቀጠሩ ሰዎች በተደጋጋሚ ከመብት ጥሰት ጋር ተያይዞ ቅሬታ ሲያቀርቡ ይስተዋላል። ከሚቀርቡት ቅሬታዎች አንዱ ደግሞ ከክፍያ ጋር ተያይዞ የሚነሳ ነው። ኤጀንሲዎች ካስቀጠሩት ሰው ላይ እስከ 60 -70 በመቶ ለግላቸው ይጠቀማሉ። ሠራተኛው ወሩን ሙሉ ሰርቶ የሚያገኘው 30 – 40 በመቶ የሚሆነውን ነው።
ይህን ተከትሎ በ2011 ይህን አሰራር ለመገደብ የ20/80 የክፍያ ክፍፍል መመሪያ በሰራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር አማካኝነት ቢወጣም ከኤጀንሲዎች ጋር መግባባት ባለመቻሉ እስከ ፍርድ ቤት የዘለቀ ክርክር እንደነበር የኢትዮጵያ ሠራተኛ ማህበራት ኮንፌዴሬሽን(ኢሰማኮ) ፕሬዝደንት አቶ ካሳሁን ፎሎ ያነሳሉ።
መመሪያው በፍርድ ቤትም ውሳኔ ያገኘ ሲሆን ይህ መመሪያ ተግባራዊ እንዲሆን ሚኒስቴር መስሪያቤቱ ለክልል እንዲሁም ለከተማ መስተዳድር ሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮዎች ደብዳቤ ቢጽፍም እስካሁን ግን ህጉ ተግባራዊ እየተደረገ አለመሆኑን አቶ ካሳሁን ይገልጻሉ።
“ለምሳሌ አንድ ድርጅት ለሰራተኛ 10,000 ብር ቢከፍል 7,000 እና 6,000 የሚሆነውን ኤጀንሲዎች ይወስዳሉ፤ ኤጀንሲዎቹ ይህንን የሚያገኙት የአስተዳደራዊ ሥራ በመስራታቸው ብቻ ነው። ተመልከት፦ አንድ ኤጀንሲ ከአንድ ሰራተኛ 5,000 ብር ቢያገኝና 10 ሰዎችን ቢያስቀጥር 50,000 ብር ያገኛል። ሌላ ነገር ሳትሰራ በዚህ ብቻ ሀብት ማካበት ነው የተያዘው። ለዚህም ነው የ20 በ80 ክፍፍል ተግባራዊ እንዲሆን የምንታገለው” ሲሉ አቶ ካሳሁን ይናገራሉ።
ሌላው ከሰራተኞች የዝቅተኛ ደሞዝ ውሳኔን ተከትሎ ፕሬዝዳንቱ ማኅበራቸው ይህ ውሳኔ በህግ እንዲወጣ ንቅናቄ የጀመረው በ2011 መሆኑን ይገልጻሉ። የሀገሪቱን ኢኮኖሚያዊ ሁኔታ የሚያጠና እና በሀገሪቱ ያለውን ዝቅተኛ የደመወዝ ደረጃ ለመወሰን የሚያስችል ቦርድ እንዲኖረን አዋጅ ቢወጣም በሀገራዊ ምርጫ እንዲሁም በሀገሪቱ በነበረው ጦርነት ምክንያት አፈፃፀሙ ዘግይቷል።
“አንድ ሰው ቢያንስ አንድ ሽሮ በ50 ብር በቀን አንዴ ገዝቼ ልብላ ቢል 1,500 ብር በወር ያስፈልገዋል ይህ ሌሎች ነገሮችን ሳይጨምር ነው። ኢንዱስትሪ ፖርኮች እንዲሁም ሌሎች ተቋሞች አሁን ላይ ያለው ዝቅተኛ ክፍያ ከ800 – 1200 ባለው ነው። እኛም መንግስት ዝቅተኛ የደሞዝ ተመን እንዲወስን እየጠየቅን እንገኛለን” ሲሉ ያስረዳሉ።
ዝቅተኛ ክፍያ ብቻ ሳይሆን በአማካይ ከፍተኛ ክፍያ ይከፈላቸዋል የሚባሉ ሰራተኞችም አሁን ባለው ሁኔታ ከፍተኛ የኑሮ ጫና ውስጥ ናቸው የሚሉት ፕሬዝዳንቱ ማኅበራቸው መንግስት የሥራ ግብርን አንዲቀንስ ጥያቄ ማቅረቡን አንስተዋል።
“በአንድ በኩል የ20/80 ህግ ተፈፃሚ እንዲሆን በሌላ በኩል የገቢ ግብር ቅነሳ እንዲደረግ ለተለያዩ የሚመለከታቸው አካላት ደብዳቤ ጽፈናል። በዚህ ረገድ ማኅበሩ ሊሄድ የሚችለው የመጨረሻው ደረጃ ወደ ጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት አቅርቧል፤ ነገር ግን እስካሁን ምንም መልስ አላገኘንም” ሲሉ ነገው የገለጹት።
