ወ/ሮ ቀለብ ስዩም ከነአራስ ልጃቸው በፀጥታ ሀይሎች ታፈኑ
የባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ ጽ/ቤት ኃላፊ የሆኑት ወ/ሮ ቀለብ ስዩም በኦህዴድ/ብልፅግና የፀጥታ ሀይሎች ታፍነው ተወስደዋል። ወ/ሮ ቀለብ ስዩም (አስቴር) የታፈኑት ከአራስ ልጃቸው ጋር ነው። የግፍ እስረኛዋ በአሁኑ ሰአት ሜክሲኮ በሚገኘው የፌደራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ይገኛሉ።
ወ/ሮ ቀለብ የታሰሩት የባልደራስ ፓርቲ ም/ፕሬዝዳንት አቶ አምሀ ዳኜው ከአፈና በዋስ በተለቀቁ በ2ኛ ቀናቸው ነው። ይህም እስሩ ፍፁም ፖለቲካዊ መሆኑን ያሳያል። ፓርቲያችን የግፍ እስረኛዋ በአስቸኳይ እንዲፈቱ ያሳስባል።
ባልደራስ
የአማራ ፋኖ አንድነት የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ እና የምስራቅ አማራ ፋኖ ስልጠና እና መምሪያ ኃላፊ ፋኖ መንበር አለሙ በጎንደር ከተማ ታፈነ፤ ከሶስተኛ ፖሊስ ጣቢያ እንዲወጣ ተደርጎ ወዳልታወቀ ስፍራ መወሰዱ ተሰምቷል።
አንደበተ ርትዑ ሲሉ ብዙዎች የሚጠሩት የአማራው ጀግና የአማራ ፋኖ አንድነት የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ እና የምስራቅ አማራ ፋኖ ስልጠና እና መምሪያ ኃላፊ ፋኖ መንበር አለሙ በጎንደር ከተማ መታፈኑ ታውቋል።
ፋኖ መንበር አለሙ ከአንድ ጓደኛው ጋር ሚያዝያ 21/2015 ምሽት አካባቢ ጎንደር ከተማ ቀበሌ 18 ሸዋ ዳቦ አካባቢ በደህነት እና በፖሊስ አባላት ከታፈኑ በኋላ ወደ ሶስተኛ ፖሊስ ጣቢያ ተወስደው መታሰራቸው ተገልጧል።
ይሁን እንጅ አማራ ሚዲያ ማዕከል (አሚማ) ያነጋገራቸው ምንጮች እንዳረጋገጠው እነ ፋኖ መንበር ሚያዝያ 22/2015 ከቀኑ 6 ሰዓት አካባቢ ከጣቢያ እንዲወጡ ተደርጓል።
በፌደራል ፖሊስ ተይዘው ወዳልታወቀ ስፍራ መወስዳቸውን ምንጮች ለአሚማ የገለጹ ሲሆን አንዳንዶች ደግሞ ፋኖዎቹ የተወሰዱት ወደ አዘዞ የፌደራል ካምፕ ነው፣ ምንአልባትም ወደ አዲስ አበባ ሊወስዷቸው ይችላሉ ሲሉ ሌሎች ደግሞ ወደ ባህር ዳር አሳልፈው ሳይወስዷቸው አልቀረም ሲሉ ግምታቸውን ተናግረዋል።
አሚማ ስለ ጉዳዩ የጎንደር ሶስተኛ ፖሊስ ጣቢያ አዛዥን ኮማንደር ድሳለኝ አበራን ያነጋገረ ቢሆንም “የማውቀው ነገር የለኝም” የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።
ፋኖ መንበር አለሙ ለሰፊው የአማራ ህዝብ በፋኖነት ተሰልፎ ከፍተኛ ትግል በማድረግ፣ ግፍን በመጠየፍ እና ግፈኞችን ፊት ለፊት አምርሮ በመታገልና ለአማራ ብሎም ለሀገር የሚበጀውን ነገር ሁሉ ያለምንም ማቅማማት በመናገር ይታወቃል።
ይያህም ቀደም ሲል የታሰሩት ሳይዘነጋ በተለይ የአማራ ልዩ ኃይልን እና የአማራ ፋኖን ትጥቅ እናስፈታለን በሚል የተጀመረውን ስርዓታዊ ዘመቻ ተከትሎ በሽህ የሚቆጠሩ የአማራ ልጆችን ማፈኑ አሁንም ተጠናክሮ እንደቀጠለ ስለመሆኑ አመላካች ነው።
አሚማ
