May 1, 2023 – EthiopianReporter.com


ዜና መንግሥት የሦስት ዓመታት የልማትና ኢንቨስትመንት ዕቅድ በበጀት ዓመቱ ለማፅደቅ እየሠራ መሆኑን አስታወቀ
መንግሥት የሦስት ዓመታት የልማትና ኢንቨስትመንት ዕቅድ በበጀት ዓመቱ ለማፅደቅ እየሠራ መሆኑን አስታወቀ
ቀን: April 30, 2023
- አገራዊ የስፓሻል ልማት ማዕቀፍ ረቂቅ ሰነድ መዘጋጀቱ ተጠቁሟል
ከ2016 እስከ 2018 የበጀት ዓመት ተግባራዊ የሚደረገውና በኢትዮጵያ ለመጀመርያ ጊዜ በሚባል ደረጃ የተዘጋጀው፣ የልማትና የመንግሥት ኢንቨስትመንት ዕቅድ፣ በሰኔ ወር ተጠናቆ ለፓርላማ እንደሚቀርብ ተገለጸ፡፡
ስለ ዕቅዱ የተገለጸው፣ የፕላንና ልማት ሚኒስቴርና የተጠሪ ተቋማት የዘጠኝ ወራት ሪፖርት ሐሙስ ሚያዝያ 19 ቀን 2015 ዓ.ም. ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሲቀርብ ነው፡፡
‹‹በአሥር ዓመታት የልማት ዕቅድ ማዕቀፍ ውስጥ ሆኖ የተዘጋጀ ነው›› የተባለው ይህ ዕቅድ፣ ዋናው መሪ የልማት ዕቅድ የሌሉትን ዝርዝር ጉዳዮች ያካተተ መሆኑ ተጠቅሷል፡፡
የሦስት ዓመታት ዕቅዱ ዝርዝር የልማት ፕሮግራሞችን የሚለይ፣ ለማስፈጸም አስፈላጊ የሆኑና መተግበር ያለባቸው ፕሮግራሞች የሚተገበሩበትን ቦታ፣ የፋይናንስ ምንጫቸውንና የሚያስፈልገውን መጠን ይዞ በዝርዝር የሚዘጋጅ እንደሆነ ተገልጿል፡፡
አዲሱ የመንግሥት ኢንቨስትመንት ዕቅድ በበጀት ወይም በአስፈጻሚው ብቻ የሚፈጸመውን ሳይሆን፣ በመንግሥት የልማት ድርጅቶች (የፌዴራልም ሆነ የክልል) እና በልማት አጋሮች የሚሠራውን የሚያካትት ነው ተብሏል፡፡
በዚህ ዝግጅት ትልቁን ድርሻ ይይዛል ከተባለው ከገንዘብ ሚኒስቴር ጋር የተዘጋጀው የሦስት ዓመታት ዕቅድ የዶክመንት ዝግጅት እየተጠናቀቀ መሆኑንና ፓርላማው ለዕረፍት ከመበተኑ በፊት እንዲፀድቅ እንደሚያደርግ፣ የፕላንና ልማት ሚኒስትሯ ፍፁም አሰፋ (ዶ/ር)፣ የመሥሪያ ቤታቸውንና የተጠሪ ተቋማቱን የዘጠኝ ወራት ዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርት ለፕላን፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ባቀረቡበት ወቅት ተናግረዋል፡፡
ዕቅዱን በተባለው ጊዜ ፓርላማው ባያፀድቀው እንኳን ዝግጅቱ በሰኔ መጨረሻ ተጠናቆ፣ በመጪው መስከረም ወር እንዲፀድቅ እንደሚደረግ ሚኒስትሯ አክለዋል፡፡
ያለፉት አሥር ዓመታት የፕሮግራም በጀት አፈጻጸም ምን ይመስላል የሚለው በሚኒስቴሩ ተገምግሞ፣ ለሦስት ዓመታቱ ዕቅድ ግብዓት ሆኖ ጥቅም ላይ መዋሉ የተገለጸ ሲሆን፣ በተጨማሪም የመንግሥት የልማት ፕሮግራሞች በዕቅድና በትግበራ ላይ የነበራቸው አፈጻጸምም በቁጥር፣ በቀጣይነትና በተደረገባቸው ወጪ ላይ በመመሥረት የነበራቸው ደረጃ ተለይቶ በሦስት ዓመቱ ዕቅድ ሰነድ ውስጥ መካተቱ ተጠቅሷል፡፡
በእያንዳንዱ ዘርፍ በሥራ ላይ ያሉ ፖሊሲዎችና እየተዘጋጁ ያሉ ፖሊሲዎች ማስፈጻሚያ የልማት ፕሮግራም መለየቱን፣ የፕላንና ልማት ሚኒስትሯ አስታውቀዋል፡፡
‹‹እዚህ አገር በጣም ጥሩ ፖሊሲዎች አሉ፡፡ ነገር ግን 25 እና 30 ዓመታት የሞላቸውን ፖሊሲዎች አተገባበራቸውን ስንፈትሽ ጥሩ ያልሆኑ በጣም ብዙ ናቸው፤›› ያሉት ፍፁም (ዶ/ር)፣ ከታዩ ክፍተቶች አንዱ ፖሊሲዎች ሲፀድቁ ለማስፈጸም የሚያስፈልጉ ፕሮግራሞችና አስፈላጊ የሆኑ ፕሮጀክቶች ዝርዝር አለመካተቱ እንደሆነ፣ በዚህም ብዙውን ጊዜ ፖሊሲ ሐሳብ ሆኖ ሲቀር እንደሚስተዋል አስረድተዋል፡፡
ስለሆነም እያንዳንዱን ፖሊሲ ለመተግበር ምን ዓይነት ፕሮግራም መቀረፅ አለበት የሚለው፣ ለእንዳንዱ ዘርፍ ተለይቶ በሦስት ዓመቱ ዕቅድ ውስጥ መካተቱ ተገልጿል፡፡
ሌላው በዚህ ግብ ውስጥ የልማት ተጠቃሚነትና የመሠረተ ልማት ሥርጭት ፍትሐዊነትን ማረጋገጥ ሲሆን፣ ከዚህ አኳያ የልማት ተጠቃሚነትን፣ የመሠረተ ልማት ሥርጭት ፍትሐዊነት በዋናነት በልማት ዕቅድ ውስጥ በማካተት የሚተገበር መሆኑ ተገልጿል፡፡
በአሥር ዓመት የልማት ዕቅዱ ላይ ከአሥሩ ምሰሶዎች አንዱ አካታችነትና ማኅበራዊ ፍትሕ ማረጋገጥ የሚለው እንደሆነ ያስታወሱት ፍፁም (ዶ/ር)፣ ይህንን በግልጽ ማዕቀፍ ለመደገፍ አገራዊ የስፓሻል ልማት ማዕቀፍ ረቂቅ ሰነድ ተዘጋጅቷል ብለዋል፡፡
ሚኒስትሯ እንደገለጹት፣ ‹‹አንድ ዕቅድ በዚህ ጊዜ ይተገበራል›› የሚለው ታውቆ ‹‹የት ይተገበራል›› የሚለው መታየት ካልቻለ የልማት ተደራሽነትን ፍትሐዊነት ለማረጋገጥ ይቸግራል፡፡
ይህንን በተመለከተ ሰፊ ጥናት ሲደረግ ቆይቶ ማዕቀፉ እንደተዘጋጀና በማዕቀፉ መሠረት ግምገማዎች እንደሚደረጉ፣ እያንዳንዱ ዘርፍ የሚተገብረው ሥራ በስፓሻል ዕቅዱ መሠረት መሆኑን ማየትና መገምገም ተጠያቂነትን ለማረጋገጥ ክትትልና ድጋፍ ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
በሌላ በኩል ከተመጣጠነ የልማት ተጠቃሚነትና የተለያዩ ቦታዎችን ዕምቅ አቅም በአግባቡ ጥቅም ላይ ከማዋል አንፃር፣ በመንግሥት መወሰድ ያለባቸው የፖሊሲ አቅጣጫዎችና ስትራቴጂዎች ከክልልና ከፌዴራል ባለድርሻ አካላት ጋር በመመካከርና መረጃ በመሰብሰብ መለየቱ ተጠቅሷል፡፡
እያንዳንዱ ከተማና አካባቢ ምን ዓይነት የልማት አቅም እንዳለው፣ የሚደረገው የመንግሥትም ሆነ የግል ኢንቨስትመንትን ያንን አቅም መሠረት ያደረገ ካልሆነ በስተቀር፣ የፖለቲካ ውሳኔዎች እየሆኑ የሚደረጉ የልማት ሥራዎች ዘላቂነት እንደማይኖራቸው ፍፁም (ዶ/ር) ተናግረዋል፡፡
ለአብነትም አንድ ኢንዱስትሪ ፓርክ መገንባት ካስፈለገ የሚገነባበት አካባቢ አቅም፣ ማዕድን ከሆነ ማዕድንን መሠረት ያደረገ የኢንዱስትሪ ፓርክ መሆን እንዳለበት ተገልጾ፣ ቱሪዝምም ከሆነ የሚከናወኑት የኢንቨስትመንት ሥራዎችም ሆኑ ማበረታቻዎች ቱሪዝምን መሠረት ያደረጉ መሆን እንዲችሉ የሚያስችል ልየታ ነው ተብሏል፡፡
የፕላንና ልማት ሚኒስቴር ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመሆን ሁለት ዓመታት የፈጀ ጥናት አድርጎ የተዘጋጀው ረቂቅ ሰነዱ፣ ሌሎች የልማት አጋሮችም የተሳተፉበት መሆኑ ታውቋል፡፡
የፕላንና ልማት ሚኒስቴር፣ እንዲሁም ተጠሪ የሆኑለት ሦስት ተቋማት ማለትም የፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት፣ የኢትዮጵያ ስታትስቲክስ አገልግሎትና የአካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን በዘጠኝ ወራት ያከናወኗቸውን ተግባራት በመጥቀስ፣ በጥንካሬና በእጥረት የተለያዩ ጉዳዮች ላይ የቋሚ ኮሚቴ አባት ጥያቄዎችንና አስተያየቶችን ሰንዝረው ነበር፡፡
የፌዴራል መሥሪያ ቤቶችና ክልሎች በዕቅዳቸውና በሪፖርታቸው የኢትዮጵያ ስታትስቲክስ አገልግሎትን መረጃ እንዲጠቀሙበት የአሠራር ሥርዓት አለመዘርጋቱ፣ አገራዊ የልማት ዕቅዶችን ከክልሎችና ከከተማ አስተዳደሮች ጋር አናበው በመሥራትና ተጨባጭ የሆነና ተዓማኒነት ያለውን ሪፖርት ግልጽ አድርጎ ያለመቅረብ ውስንነት አለ የሚሉ ጉዳዮች በቋሚ ኮሚቴ አባላት ተነስተው ነበር፡፡
