May 1, 2023 – EthiopianReporter.com


ዜና ኢትዮጵያ ካርቱም የሚገኙ ዲፕሎማቶቿን ወደ ገዳሪፍ አዛወረች
ኢትዮጵያ ካርቱም የሚገኙ ዲፕሎማቶቿን ወደ ገዳሪፍ አዛወረች
ቀን: April 30, 2023
- ሃምሳ አገሮች ዜጎቻቸውን በኢትዮጵያ በኩል ለማስወጣት ጠይቀዋል
ከተጀመረ ሁለት ሳምንታት ያለፈው የሱዳን ጦርነት፣ በፀጥታ ሥጋትና በመሠረታዊ አገልግሎቶች መቋረጥ ምክንያት፣ ኢትዮጵያ ካርቱም የሚገኙ ዲፕሎማቶቿን ወደ ገዳሪፍ ማዛወሯ ተገለጸ፡፡
በሱዳን ሠራዊትና በፈጥኖ ደራሽ ልዩ ኃይል መካከል በተቀሰቀሰው ግጭት፣ በመቶዎች ሲሞቱ በሺዎች የሚቆጠሩ ቆስለዋል፡፡ ጦርነቱ ከተነሳ በኋላ በርካታ አገሮች ዜጎቻቸውን በየብስ፣ በአየርና በባህር ይዘው እየወጡ ነው፡፡ በዚህ ግጭት እስካሁን ሃምሳ አገሮች ዜጎቻቸውን በኢትዮጵያ በኩል ይዘው ለመውጣት መጠየቃቸውን፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡
በካርቱም የኢትዮጵያ ኤምባሲ ባወጣው መግለጫ፣ ኢምባሲው የሚገኝበት አካባቢ የውጊያ ቀጣና በመሆኑ የኤሌክትሪክ አገልግሎት መቋረጥ፣ የምግብ አቅርቦት ማግኘት አለመቻልና ዜጎችን መርዳት አደጋች ደረጃ ላይ መድረሱን አስታውቋል፡፡ ኤምባሲው የተወሰኑ ሠራተኞች እንዲቀሩ ተደርጎ፣ አምባሳደሩን ጨምሮ ቀሪዎቹ ወደ ገዳሪፍ ቆንስላ መዛወራቸውን አክሏል፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ መለስ ዓለም (አምባሳደር) ዓርብ ሚያዚያ 20 ቀን 2015 ዓ.ም ለጋዜጠኞች በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፣ በሱዳን እየተካሄደ ካለው ጦርነት ጋር በተገናኘ የኢትዮጵያ መንግሥት በአገር አቀፍ ደረጃ ግብረ ኃይል አቋቁሞ እየተንቀሰቀሰ ነው ብለዋል፡፡
ግብረ ኃይሉ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርን ጨምሮ አጎራባች ክልሎችንና የተለያዩ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶችን አካቶ የተቋቋመ መሆኑን፣ በአሁኑ ወቅት ባለሙያዎችን ድንበር ድረስ በመላክ እየተሠራ ነው ሲሉ አስረድተዋል፡፡
ገዳሪፍ የሚገኘው የቆንስላ አገልግሎት ላይ ጫናው ከፍ ማለቱን ጠቅሰው፣ ለኢትዮጵውያን፣ ለዓለም አቀፍ ድርጅቶች፣ ለተለያዩ አገሮች ዜጎችም ጭምር አገልግሎት እየሰጠ መሆኑን ቃል አቀባዩ ተናግረዋል፡፡ በመቶዎች የሚቆጠሩ የውጭ አገሮች ዜጎች የኢትዮጵያን ድንበር ተሻግረው ወደ ኢትዮጵያ መግባታቸውን ቢናገሩም፣ ቁጥራቸው ምን ያህል እንደሆነ አልገለጹም፡፡ የፈረንሣይ፣ የአሜሪካ፣ የእስራኤል፣ የቱርክ፣ የኬንያና የኡጋንዳን ጨምሮ በርካታ ዜጎች ይገኙበታል ብለዋል፡፡
‹‹ኢትዮጵያ እንግዳ ተቀባይ አገር ከመሆኗ ባሻገር ሱዳናውያን ኢትዮጵያ ፈተና ውስጥ በነበረችበት ወቅት ሁሉ ሁልጊዜም ከጎኗ የቆሙ በመሆናቸው፣ አሁን የእነሱን ዕንባ ለማበስ ያለንን ውስን ሀብት ተጠቅመን የሰብዓዊ ድጋፍ ለማድረግ እየሞከርን ነው፤›› በማለት ገልጸዋል፡፡
ይሁን እንጂ አንዳንድ ወገኖች በሁለቱ ሕዝቦች መካከል ሳንካ እንዲኖር በማኅበራዊ ሚዲያ የተለያዩ ዘመቻ እያደረጉ ቢሆንም፣ መንግሥት ለእያንዳንዱ የማኅበራዊ ሚዲያ ሪፖርት መልስ መስጠት ተገቢ አይደለም የሚል እምነት አለው ብለዋል፡፡
‹‹የሱዳን ሰላም አለመሆን ጎረቤት ሲቃጠል እንደማለት ነው፡፡ የሱዳን አለመረጋጋትና የሰላም ዕጦት ለኢትዮጵያ ብቻ አይደለም ለአካባቢው ብዙ ትርጉም አለው፤›› ብለዋል፡፡ ይህ ጦርነት ቢያንስ ቢያንስ ሕገወጥ የጦር መሣሪያ ዝውውርና የሰዎች ዝውውርን የበለጠ የከፋ እንደሚያደርገው፣ በኢኮኖሚው መስክም ሱዳን የኢትዮጵያ የውጭ ምርቶች መዳረሻ በመሆኗ ካለው ግንኙነት አንፃር ሲታይ የሱዳን የሰላም ዕጦት ለኢትዮጵያ ትልቅ ትርጉም አለው ብለዋል፡፡
ሱዳን ውስጥ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን መኖራቸውን ያብራሩት ቃል አቀባዩ፣ ዜጎች ኤምባሲ ሄደው ስለማይመዘገቡ ቁጥራቸው በውል እንደማይታወቅ አስረድተዋል፡፡ ይሁን እንጂ ኢትዮጵያ የዜጎቿ ደኅንነት እንዲጠበቅ የተቋቋመው ግብረ ሃይል ካርቱምና ገዳሪፍ ካለው ኤምባሲ ጋር እንደሚሠራ ጠቁመዋል፡፡
ግብረ ኃይሉ የቀውስ ጊዜ ሁኔታ ላይ እንዲሠራ በማሰብ ጦርነቱ እንደተከሰተ ወዲያውኑ መቋቋሙን የገለጹት መለስ (አምባሳደር)፣ ሱዳን የሚገኙ ዜጎች ጉዳትና ችግር እንዳይገጥማቸውና ከሱዳን ወደ ኢትዮጵያ የሚመጣ የፀጥታም ሆነ የሰብዓዊ ቀውስ እንዳይፈጠር በማሰብ ነው ሲሉ አክለዋል፡፡
በመሆኑም የግብረ ኃይሉ ዓላማ ጦርነቱ በኢትዮጵያ ላይ ጉዳት እንዳያደርስ ማድረግ፣ የተለያዩ አገሮች ዜጎቻቸውን ከሱዳን ማስወጣት ሲፈልጉ ኢትዮጵያን እንደ ሁነኛ አማራጭ አድርገው በማሰባቸው፣ በኢትዮጵያ በኩል የሚወጡ የሌሎች አገር ዜጎች ሊደረግላቸው የሚገባውን ድጋፍ ማመቻቸት፣ ዜጎች እንዴት እንደሚወጡና የቆንስላ አገልግሎት እንዴት ያግኙ የሚለውን፣ ሕክምና ሲፈልጉ እንዴት ማስተናገድ ይገባል በሚል አገሪቱ ካላት ውስን ሀብት ላይ በመጠቀም ለማስተናገድ እንጂ የሌላ አካል ተፅዕኖ ስላለ አለመሆኑን አብራርተዋል፡፡
ቃል አቀባዩ በሱዳን የተቀሰቀሰው ጦርነት በህዳሴው ግድብ ላይ የሚደረገውን ድርድር በሚፈለገው ጊዜና ፍጥነት እንዳይሄድ የራሱ ተፅዕኖ ስለሚኖረው፣ ሱዳናውያን ወደ ሰላም እስኪመጡ መጠበቅ የግድ የሚል ይሆናል ብለዋል፡፡
