· Getachew Shiferaw

  · የግድያ ወንጀልን ለፖለቲካ ሸቀጥ መጠቀም መቆም አለበት!

በአቶ ግርማ ግድያ ከመንግስት ይልቅ ኢዜማና አብን ኃላፊነት ያለበት መግለጫ አውጥተዋል።

መንግስት የሚባለው በግለሰብ፣ በፓርቲ፣ በደጋፊዎቹ በኩል በሙሉ አቅሙ ከወንጀለኛ ይልቅ ክልልና ህዝብን ፍረጃ ውስጥ ገብቶ የሟቾቹን ህይወት የፖለቲካ ሸቀጥ አድርጎታል። ነውር ነው። ጉዳዩን ለፖለቲካ መጠቀሚያ ያደረጉት ሟቾቹና ቤተሰቦቻቸው ፍትሕ እንዳያገኙ እያድበሰበሱ ነው። በቀጣይም ሰው እየተገደለ የፖለቲካ መጠቀሚያ የሚሆንበትን አሉታዊ ባህል የሚፈጥር አደገኛ አካሄድ ነው። የሟቾቹ ቀብር ሳይፈፀም ይህን ያህል የፖለቲካ ሸቀጥና የፍረጃ ጋጋታ ከመፍትሄ ይልቅ ችግር የሚያወሳስብ፣ ወንጀሉን የሚያድበሰብስ መሆኑ መታወቅ አለበት።

የአማራ ህዝብ ችግሮች ተፈጥረውበትም፣ ሞት የዘመቻ ማስጀመርያ የሚሆንበት አካሄድ ተለምዷል። ይህ አካሄድ ሟቾች እና ቤሰቦቻቸው ፍትሕ እንዳያገኙ ትልቅ ደንቃራ ነው። የሚጠሉትን ህዝብ አጋጣሚ አገኘሁ ብሎ ከፕሮፖጋንዳው ጀምሮ የተቀናጀ ዘመቻ ለመክፈት እየተሰራ እንደሆነ እየነገሩን ነው። ከጠቅላይ ሚኒስትሩ እስከ ፓርቲው፣ ከሽመልስ አብዲሳ በቅርብ ህዝብ ነቅቶበት ጥላቻውን ግልፅ እስካደረገው ኤርሚያስ ለገሰ ድረስ ያለው እንደማሳያ እንጅ ዘመቻው ቀላል አይደለም።

መሰል ወንጀል ለአማራ ህዝብ ትግል መሰናክል እንደመሆኑ እውነታውን ማወቅ ይፈልጋል። ይህ የሚሆነው ግን ከፍረጃና አጋጣሚ አገኘሁ ከሚል አካሄድ ይልቅ ገለልኛና ፍትህ እንዲኖር በማድረግ ነው።

በግራ በቀኝ የሚደረገው ፍረጃና አጋጣሚውን ለመጠቀም የሚደረገው መቋመጥ ቆሞ ወንጀሉ በገለልኛ አካሄድ መመርመር ይገባዋል። የሰዎችን ሞት የፖለቲካ መጠቀሚያ ማድረግ ለማንም አይጠቅምም። የጥላቻ መግለጫው፣ ፍረጃው ቆሞ ለፍትሕ ምቹ ሁኔታ መፍጠር፣ ማድበስበስን ማቆም ያስፈልጋል።

የአማራ ጉዳይ ያገባኛል የሚል ሁሉ መሰል ክስተቶች ከህዝብ አንድነት፣ ከቀጣይ ፖለቲካና ከፍትሕ አንፃር መመልከት፣ እልህና ብሽሽቅን ማስወገድ፣ በጉዳዩ ላይ ያልተገቡ አስተያየቶችን ከመሰንዘር መቆጠብ ያስፈልጋል።

ሟቾችን ነፍስ ይማር! ቤተሰቦቻቸውን መፅናናት ይስጣቸው።