ጥቁር ጭስ
የምስሉ መግለጫ,በቅርብ በተከሰተው ፍንዳታ በሱዳን ሰማይ ላይ ጥቁር ጭስ ታይቷል።

ከ 7 ሰአት በፊት

የቢቢሲ ዓለም አቀፍ አገልግሎት ለሱዳን በአረብኛ ቋንቋ የአደጋ ጊዜ ጊዜያዊ የራዲዮ አገልግሎት ዛሬ ማክሰኞ እንደሚጀምር አስታወቀ።

ጊዜያዊ የራዲዮ አገልግሎቱ ለሦስት ወራት ያህል በቀን ሁለት ጊዜ የሚተላለፍ ሲሆን፣ በጦርነት ውስጥ ባለችው አፍሪካዊት አገር ላሉት ሰዎች ዜና እና መረጃዎችን ያቀርባል።

ከዚህም ባሻገር ከዐይን እማኞች እና ከዲፕሎማሲያዊ ጥረቶች ጋር በተያያዘ የሚወጡ ዜናዎች በፕሮግራሙ ይካተታሉ።

አገልግሎቱ በሱዳን የተዛቡ መረጃዎችን ለመከላከል እንደሚረዳም ቢቢሲ ገልጿል።

የቢቢሲ ዋና ዳይሬክተር ቲም ዴቪ፣ “በዚህ አስቸጋሪ ወቅት ይህ የራዲዮ አገልግሎት መጀመሩ ወሳኝ ነው” ብለዋል።

የራዲዮ አገልግሎቱ በዮርዳኖስ ዋና ከተማ ኦማን እና በግብፅ መዲና ካይሮ ከሚገኙ ቡድኖች የሚቀርቡ ትንተናዎች እና አስተያየቶች ተካተውበት ከለንደን በቀጥታ ይተላለፋል።

በሱዳን በአጭር ሞገድ ላይ ፕሮግራሙ በአረብኛ የሚተላለፍ ሲሆን፣ በበይነ መረብም መረጃዎችን ማድመጥ እንደሚቻል ቢቢሲ ገልጿል።

ዴቪ በሰጡት መግለጫ፣ “ዓለም አቀፍ አገልግሎቱ ትክክለኛ ዘገባ እና መረጃዎችን የማግኘት እጥረት ላለባቸው በዓለም ዙሪያ ለሚገኙ በርካቶች አስፈላጊ መረጃን ይሰጣል” ብለዋል።

በመሆኑም በሱዳን የተጀመረው የአደጋ ጊዜ የራዲዮ አገልግሎት “በአገሪቷ ካለው የማያስተማምን ሁኔታ አንጻር ወሳኝ ነው” ብለዋል።

በሱዳን ዋና ከተማ ካርቱም እንዲሁም በሌሎች አካባቢዎች የተቀሰቀሰው ውጊያ የአገሪቷ ወታደራዊ አመራሮች የሥልጣን ሽኩቻ ቀጥተኛ ውጤት ነው።

ውጊያው እየተካሄደ ያለውም በሱዳን መደበኛ ጦር እና ራፒድ ሰፖርት ፎርስ ( አርኤስኤፍ) በሚል በሚጠራው ፈጥኖ ደራሽ ኃይል መካከል ነው።

የቢቢሲ ዓለም አቀፍ አገልግሎት ዳሬክተር ሊሊያን ላንደር እንዳሉት “በሱዳን ያለው ሁኔታ በፍጥነት ተባብሶ ዜጎች ግልጽ፣ ገለልተኛ የሆነ መረጃ እና ምክር የሚፈልጉበት አሳሳቢ ሁኔታ ውስጥ ገብተዋል።”

በሱዳን የቢቢሲ አረብኛ የአደጋ ጊዜ የራዲዮ አገልግሎት በአገሪቱ ውስጥ ስላለው ሁኔታ ወቅታዊ ዘገባዎችን የሚያቀርብ ሲሆን፣ ለአድማጮችም ሕይወታቸውን ሊያተርፉ የሚችሉበትን መንገድ ያመላክታል።

ፕሮግራሙ ጠዋት ላይ በ21 ሺህ 510 ኪሎኸርዝ እና ከሰዓት በኋላ ደግሞ በ5 ሺህ 310 ኪሎኸርዝ ላይ ይተላለፋል።

የመጀመሪያው ፕሮግራሙም ዛሬ ማክሰኞ ከሰዓት መተላለፍ ይጀምራል።