May 2, 2023 – BBC Amharic 

ኮሎኔል ቻርልስ ኦኬሎ ኢንጎላ
የምስሉ መግለጫ,ኮሎኔል ቻርልስ ኦኬሎ ኢንጎላ የተገደሉት ቤታቸው ውስጥ ነው

ከ 4 ሰአት በፊት

የኡጋንዳ ብሔራዊ ጦር ወታደር የሚጠብቃቸውን የመንግሥት ሚኒስትር መኖሪያ ቤታቸው ውስጥ ተኩሶ ገደለ።

የሠራተኛ ሚኒስቴር ምክትል ሚኒስትር የሆኑት እና በጡረታ የተገለሉት ኮሎኔል ቻርልስ ኦኬሎ ኢንጎላ በዋና መዲናዋ ካምፓላ ውስጥ ዛሬ ማክሰኞ ጠዋት መገደላቸው ተገልጿል።

የግድያው መንስኤ እንዲሁም በእርሳቸው እና በጠባቂያቸው መካከል አለመግባባት ስለመኖር አለመኖሩ እስካሁን ግልጽ አይደለም።

አንዳንድ የዐይን እማኞች ወታደሩ በአካባቢ ወደ ላይ በመተኮስ ሲያልፍ እንደነበር ተናግረዋል።

ስሙ በይፋ ያልተገለጸው ወታደር የሚጠብቃቸውን ሚኒስትር ከገደለ ከደቂቃዎች በኋላ እራሱን አጥፍቷል።

በክስተቱ በርካታ ሰዎች ጉዳት እንደደረሰባቸውም የወጡ ሪፖርቶች አመልክተዋል።

በማኅበራዊ ሚዲያ የተጋሩ ተንቀሳቃሽ ምስሎችም የአካባቢው ነዋሪዎች አደጋው በተፈጠረበት ቦታ በድንጋጤ ተሰብስበው አሳይተዋል።

ኮሎኔል ኢንጎላ ቀደም ብሎ የኡጋንዳ መከላከያ ሚኒስትር ምክትል ሚኒስትር ሆነው አገልግለዋል።

የካምፓላ ከተማ ፖሊስ ምክትል ቃል አቀባይ ሉክ ኦዎየሲጊሬ ግድያው መፈጸሙን እንዳረጋገጡለት ሞኒተር የተባለው ጋዜጣ ዘግቧል።

ዛሬ ጠዋት የተካሄደውን የአገሪቱ ፓርላማ ስብሰባን የመሩት የምክር ቤቱ አፈ ጉባኤ አኒታ አሞንግም የሚኒስትሩን ሞት አረጋግጠዋል።

“ዛሬ ጠዋት የሚያሳዝን ዜና ነው የሰማሁት። የተከበሩ ኢንጎላ በግል ጠባቂያቸው በጥይት የተገደሉ ሲሆን፣ ገዳዩም እራሱን አጥፍቷል። ምንም የምንለውጠው ነገር የለም፣ የሆነው የእግዚአብሔር ፈቃድ ነው። ነፍስ ይማር” ብለዋል አፈ ጉባኤዋ።

ግድያው የተፈጸመበት ስፍራ በፖሊስ ተከልሎ ጥበቃ እየተደረገለት ሲሆን፣ የሚኒስትሩ እና የገዳዩ አስከሬን በቤታቸው ውስጥ እንደነበረ ሞኒተር ዘግቧል።

ግድያው ከተፈጸመ በኋላ በርካታ ሰዎች በሚኒስትሩ ቤት አካባቢ የነበሩ ሲሆን፣ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናትም ተገኝተዋል። የሥርዓተ ጾታ ሚኒስትሯ ቤቲ አሞንጊም በስፍራው ከተገኙት ሰዎች መካከል አንዷ ናቸው።

ግድያው ከመፈጸሙ በፊት በቦታው የነበሩ የዐይን እማኞች ገዳዩ ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ እንዳልተከፈለው በመግለጽ ያለበትን ችግር እና ቅሬታውን ሲገልጽ ነበር ብለዋል።

በተጨማሪም ባለቤቱ ነፍሰጡር መሆኗን፣ “አራት ሚሊዮን ሽልንግ እንዳልተከፈለው” በመናገር የሚኒስትሩ ልጆች ትምህርት ቤት እየሄዱ የእሱ ልጆች ግን ትምህርት እንዳቆሙ ሲናገር ነበር ተብሏል።

ለሚኒስትሩ ሞት ከጠባቂያቸው ጋር ያለ የገንዘብ ወይም የክፍያ አለመግባባት ሊሆን እንደሚችል ተገምቷል።