May 2, 2023 – BBC Amharic 

የኤርትራ ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ
የምስሉ መግለጫ,የኤርትራ ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ

ከ 5 ሰአት በፊት

የኤርትራ ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ግጭት በመሸሽ መጠለያ ለሚፈልጉ ሱዳናውያን የአገራቸው በር ክፍት መሆኑን ተናገሩ።

ፕሬዝዳንት ኢሳያስ ይህንን ያሉት ከሁለት ሳምንት በላይ በሆነው የሱዳን ቀውስ ምክንያት ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የአገሪቱ ዜጎች ወደ ጎረቤት አገራት እየተሰደዱ ባለበት ጊዜ ነው።

ፕሬዝዳንቱ ለአገራቸው ቴሊቪዥን በሰጡት ቃለ ምልልስ “አሳዛኝ እና አስከፊ” ያሉት የሱዳን ግጭት በፍጥነት መቆም እንዳለበት አሳስበዋል።

ለዚህም የምሥራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት ባለሥልጣን በእንግሊዝኛ ምህጻሩ ኢጋድ በሱዳን ለተፈጠረው ችግር ቅድሚያ ሰጥቶ ሊፈታው እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

ከሁለት አስርት ዓመታት በላይ ከቀጠናዊ ድርጅቱ ኢጋድ እራሷን አግልላ የቆየችው ኤርትራ ከወራት በፊት ወደ አካባቢያዊ ስብስቡ ለመመለስ ፍላጎት እንዳለት ማሳወቋ ይታወቃል።

ኤርትራ የየብስ ድንበር የምትጋራት ጎረቤቷ ሱዳን ጋር የቀረበ ግንኙነት ያላት ሲሆን፣ በርካታ ዜጎቿም ሱዳን ውስጥ ይገኛሉ።

የሱዳን ጉዳይ በአሁኑ ወቅት በዓለም አቀፍ ደረጃ አሳሳቢ ነው ያሉት ፕሬዝዳንት ኢሳያስ፣ በርካታ አገራት በተናጠል ችግሩን ለመፍታት ፍላጎት ቢያሳዩም የሱዳንን ችግር ለመፍታት እና የሱዳናዊያንን ፍላጎት መሠረት ያደረገ መንግሥት እንዲመጣ ማገዝ የሚኖርበት ግን ኢጋድ ነው ብለዋል።

ፕሬዝዳንት ኢሳያስ የሱዳንን ግጭት ባወሱበት በዚህ ቃለ ምልልስ “በሱዳን የመከላከያ እና የደኅንነት ተቋማት አንድነት ላይ ጥያቄ እና ብዥታ ሊነሳ አይገባም” ብለዋል።

ኢሳያስ አገራቸው ኤርትራ ሱዳን ላጋጠማት ችግር የምትችለውን ሁሉ እገዛ ለመስጠት አትሳሳም ያሉ ሲሆን፣ ነገር ግን የሱዳን ሕዝብ በቅድሚያ የገጠመውን ችግር ራሱ የሚፈታበት ዕድል ሊሰጠው ይገባል ሲሉ ተናግረዋል።

በአገራቸው የተከሰተውን ቀውስ በመሸሽ የሚሰደዱ ሱዳናውያንን በተመለከተም ፕሬዝዳንቱ “ባሕሩም፣ አየሩም፣ የብሱም ለሱዳናዊያን ክፍት ነው” ብለዋል።

ይህም ለሱዳናውያን ብቻ ሳይሆን በተከሰተው ግጭት ሳቢያ ችግር ለገጠማቸው ኤርትራውያንም ሆነ ለሌሎች አገራት ዜጎች ኤርትራ በሯ ክፍት መሆኑን ፕሬዝዳንት ኢሳያስ ተናግረዋል።

ነገር ግን “ኤርትራ የስደተኛ ሱቆችን መክፈት አትፈልግም” በማለት በአገሪቱ ውስጥ የስደተኛ ካምፖችን በመክፈት የውጭ ድርጅቶች ጣልቃ እንዲገቡ እንደማይፈቅዱ ገልጸዋል።

ከዚያ ይልቅ አገራቸው ለሱዳን ሕዝብ የምትችለውን ሁሉ በማድረግ ችግር ላይ ያሉትን የጎረቤት አገራት ዜጎችን እንደምታግዝ “የሱዳን ወንድም እና እህቶቻችን ከለላን ፍለጋ ወደኛ ከመጡ የኤርትራ ሕዝብ ያለውን ለማካፈል ፍቃደኛ ነው” በማለት ፕሬዝዳንቱ ተናግረዋል።

ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አሁን በሱዳን የተፈጠረው ችግር መነሻው የአገሪቱ ወታደራዊ መሪዎች የሕዝቡን ሲቪል የመንግሥት የመመሥረት ፍላጎትን ገሸሽ አድርገው ለሥልጣን መሻማታቸው ያመጣው ነው ብለዋል።

ፕሬዝዳንቱ ለረዥም ዘመን በሥልጣን የቆዩት ኡመር አልበሽር ከሥልጣን ከተወገዱ በኋላ እንዴት የፖለቲካ ሁኔታው ወደ ግጭት ሊያመራ እንደቻለም ፕሬዝዳንቱ አብራርተዋል።

ከሁለት ሳምንት በላይ የሆነው የሱዳን ቀውስ በኃያላኑ የአገሪቱ ጄኔራሎች መካከል የተቀሰቀሰ ነው። ከሁለት ዓመት በፊት የተካሄደውን ተከትሎ ሥልጣን የጨበጡት ከፍተኛ መኮንኖች አገሪቱን ወደ ሲቪል አስተዳደር ለመመለስ በወጣው ዕቅድ ላይ ሳይስማሙ በመቅረታቸው ነበር ግጭት ውስጥ የገቡት።

በአገሪቱ ሠራዊት አዛዥ ጄኔራል አልቡርሃን እና በጄኔራል ዳጋሎ የፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች መካከል በመካሄድ ላይ ባለው ግጭት ከአምስት መቶ በላይ ሰዎች የተገደሉ ሲሆን፣ በሺዎች የሚቆጠሩ ደግሞ ጉዳት ደርሶባቸዋል።

ውጊያው እየተባባሰ በመሄዱም በ10 ሺዎች የሚቆጠሩ ሱዳናውያን ነፍሳቸውን ለማትረፍ ወደ ጎረቤት አገራት እየተሰደዱ ነው።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትም በተቀናቃኝ ወታደራዊ አንጃዎች መካከል እየተካሄደ ባለው ውጊያ ምክንያት ከ800 ሺህ በላይ ሱዳናውያን አገራቸውን ጥለው ሊሰደዱ እንደሚችሉ አስጠንቅቋል።