መንግሥት ባለፈው ሳምንት ጀምሮ በኦሮሚያ ክልል በተለያዩ ቦታዎች በሚንቀሳቀሰውና የተለያዩ ሽብር ተግባራትን በማከናወኑ በኢፌዴሪ ሕ/ተ/ም/ቤት አሸባሪ ተብሎ ከተፈረጀው መንግሥት ኦነግ ሸኔ ብሎ ከሚለው እራሱን የኦሮም ነፃነት ሰራዊት ብሎ ከሚጠራው ታጣቂ ቡድን ጋር ችግሮችን በውይይት ለመፍታት በታንዛኒያ መቀመጡን ማስታወቁ ይታወሳል።
ይህንንም አስመልክቶ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) ዛሬ ባወጣው መግለጫ፤ ፓርቲው ጥቅምት 24 /2015 የፕሪቶሪያው ስምምነት ሊደረግ መሆኑን ተከትሎ ‹‹በሌሎች የአገሪቷ ክፍሎች ያሉ የታጠቁ ኃይሎችም ጋር በሰላማዊ ንግግር መፍትሔ የሚያገኝበት መንገድ ላይ በአፅንኦት መስራት ያስፈልጋል›› ሲል ጥሪ ማቅረቡን አስታውሷል፡፡
ፓርቲው በመግለጫው፤ አሁንም ሰላም የሰፈነባት እና ዴሞክራሲያዊ ኢትዮጵያን ለማየት ከተፈለገ የትኛውም ዓይነት የሃሳብ ልዩነቶች ከአፈሙዝ ተላቀው ወደ ጠረጴዛ ዙሪያ መቅረብ እንዳለባቸው ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እንደሚያምን አስታውቋል፡፡
በተለይም ባለፉት ጥቂት ዓመታት በኦሮሚያ ክልል በተደጋጋሚ ዜጎች በማንነታቸው ምክንያት ክቡር የሆነው ሕይወታቸውን ሲያጡ ንብረታቸውም ሲወድምና ከቀያቸው ሲፈናቀሉ በገሀድ መታየቱን የገለጸው ኢዜማ፤ <<መንግሥትም በተደጋጋሚ የተፈፀሙትን በደሎች ይህ ታጣቂ ቡድን ሲፈፅማቸው እንደነበር ከማሳወቁ አንፃር ይህን መሰል የዜጎች ሰቆቃ የሚያስቆም ድርድር ውስጥ መግባቱን የምናበረታታው ነው።>> ብሏል።
ፓርቲው አክሎም፤ <<ገዢው ፓርቲ ብልጽግና አገራችንን መምራት የጀመረበትን ጊዜ ጨምሮ ባለፉት አምስት ዓመታት በተለያየ ጊዜ የሚፈጸሙ እንዲህ አይነት ድርድሮች ግልጽነት ሲጎድላቸው እና አፈፃፀማቸው በተገቢ ሁኔታ ሳይከናወን ቀርቶ ብዥታዎችን ሲፈጥር ተመልክተናል፡፡>> ሲል ገልጿል።
<<በቅርብ ጊዜ እንኳ መንግሥት ከሕወሓት ጋር ድርድር አድርጌ ሰላም አውርጃለሁ ባለበት የፕሪቶሪያው ስምምነት እንደ ስምምነቱ ያልተፈጸሙ ጉዳዮችን አስተውለናል፡፡ ሂደቱም ምን ላይ እንደሆነ አሁንም ድረስ በግልፅ አይታወቅም፡፡>> ያለው ኢዜማ፤ በዚህ ምክንያትም ፓርታውን ጨምሮ የተለያዩ አካላት ላይ አሁንም ድረስ ከፍተኛ ቅሬታን እያስነሳ መሆኑን ገልጿል፡፡
ስለሆነም መንግሥት ከዚህ ቀደም በለውጡ ሰሞን ኦነግ ከኤርትራ ወደ አገር ቤት ከገባ በኋላ <<በስምምነቱ መሠረት አልተፈጸመልኝም>> ሲል እንደነበረው ተመሳሳይ ችግር እንዳይፈጠር፤ በተለይም ከሕወሓት ጋር ከተደረገው ስምምነት ልምዶች መነሻ በማድረግ፣ የድርድሩን ሂደትና ስምምነቱን በተመለከተ ህዝቡ ሊኖረው የሚገባውን ግልፅ መረጃ ፤ እነማን እየተሳተፉ እንደሆነ፣ የስምምነቱን ይዘት፣ እንዴት እንደሚፈጸም እና በአፈፃፀሙም ጊዜ ተግባራዊነቱን ለዜጎች ተገቢና በቂ መረጃን በማስተላለፍ ከተጨማሪ ውዥንብርና ትርምስ ማኅበረሰቡን እንዲጠበቅ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) አሳስቧል፡፡
