May 2, 2023 

(አዲስ ማለዳ) የፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ጊዜ ቀጠሮ ችሎት ሕገ-መንግሥቱን እና ሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓቱን በኃይል ለማፍረስ ሲንቀሳቀሱ ነበር ተብለው በተጠረጠሩ 11 ግለሰቦች ላይ የዘጠኝ ቀን የምርመራ ማጣሪያ ጊዜ ፈቅዷል።

ፍርድ ቤቱ በተጠርጣሪዎቹ ላይ ተጨማሪ ምርመራ እንዲከናወንባቸው ተጨማሪ ጊዜ የፈቀደው ፖሊስ የሠራውን ምርመራ ከተመለከተ በኋላ ነው።

ለተጨማሪ ምርመራ የጊዜ ቀጠሮ የተፈቀደባቸው ተጠርጣሪዎችም ጌታሆይ ዓለሙ ተበጀ፣ ሃብታሙ ዳኜ፣ ዳዊት አባቡ፣ ቴድሮስ ተሾመ፣ ጌታቸው ጥዑመ ልሳን፣ ትዛዙ ታረቀኝ፣ ሙሉቀን ወንዴ፣ ዋና ሳጅን ቢያዝን ምሕረቱ፣ ምስጋና ማሩ፣ በቀለ ኃይሌ (ዶ/ር) እና ጌትነት ወንደሰን ናቸው።

ፖሊስ በጀመረው የምርመራ ሥራ ተጠርጣሪዎቹ ኢ-መደበኛ መዋቅራዊ አደረጃጀት ፈጥረው ሲንቀሳቀሱ እንደነበር ማስረጃ ሰብስበናል ሲል ለችሎቱ አብራርቷል።

ለወንጀል ተሳትፏቸው የሚያስረዱ የምስክሮችን ቃል መቀበሉን እና በእጃቸው ላይ የተገኙ ኤሌክትሮኒክስ መሳሪያዎችን በሚመለከተው አካል እንዲመረመር መላኩንም አስረድቷል።

የገንዘብ ዝውውርን በሚመለከት ለማጣራት ለባንኮች ማስረጃ መጠየቁንም ነው ፖሊስ ለችሎቱ ያብራራው።

ተጨማሪ የምስክር ቃል ለመቀበል እና ቀሪ ሥራዎችን አከናውኖ ለማቅረብም የ14 ቀን ተጨማሪ ጊዜ እንዲሰጠው ጠይቋል።

የተጠርጣሪዎቹ ጠበቆችም ለፖሊስ ከዚህ በፊት የተሰጠው ጊዜ በቂ መሆኑን ጠቅሰው፣ ተጨማሪ የምርመራ ቀናት ሊሰጥ አይገባም ሲሉ ተከራክረዋል። የተጠርጣሪዎቹ የዋስትና መብት እንዲፈቀድም ጠይቀዋል።

መርማሪ ፖሊስ በበኩሉ ‹‹ተጠርጣሪዎቹ በዋስ ቢወጡ ምስክር ሊያስፈራሩ እና ሊደልሉብን እንዲሁም በመንግሥት የተጀመረውን የሕግ ማስከበር ሥራ ሊያደናቅፉ ይችላሉ›› ሲል ስጋቱን ገልጾ የዋስትና ጥያቄያቸውን ተቃውሟል።

የግራ ቀኙን ክርክር ያዳመጠው የጊዜ ቀጠሮ ችሎቱ የፖሊስን የምርመራ መዝገብ አስቀርቦ ከተመለከተ በኋላ የቴክኒክ እና የፎረንሲክ ማስረጃዎች መሰብሰባቸውን መመልከቱን አብራርቷል።

በዚህ መሰረትም ፍርድ ቤቱ ተጠርጣሪዎቹ የጠየቁትን የዋስትና ጥያቄ ለጊዜው ውድቅ በማድረግ ለተጨማሪ ምርመራ ለፖሊስ የ9 ቀን የምርመራ ጊዜ መፍቀዱን ኢዜአ ዘግቧል።