
መሳይ መኮንን የጠሚ/ሩን የሃላላ ኬላ የምርቃት ፕሮግራም ንግግራቸውን እየተከታተልኩ ነበር። በቅንጡ ሎጆች ግንባታ ዙሪያ ጠ/ሚሩ እየሄዱበት ስላለው ርቀት ብዙ ማለት የሚያስችል ቢሆንም ለጊዜው ልተወው። ሰውዬው ትልቁ ችግራቸው ሀገሪቱን አንቀው ትንፋሽ አሳጥተው ሲጥ ሊያደርጓት ከጫፍ የደረሱትን ችግሮች የመረዳት አቅሙም ፍላጎቱም ስለሌላቸው አይናቸው ላይ የተጋደሙትን ግዙፍ እሾሆች እየዘለሉ የቅንጦት ፕሮጀክቶች ላይ ገንዘብና ጊዜ ማባከናቸው ነው። ይሄ የልማት አርበኝነት አይደለም። እሳቸው ስር ቱስ ቱስ እያሉ ወናፍ ይዘው የሚያራግቡላቸው በጥቃቅንና አነስተኛ የተደራጁ የማህበራዊ ሚዲያ ሰራዊት አባላትን ጭብጨባና ሙገሳ እየተከታተሉ ራሳቸውን እንደ ልማት መሪ አድርገው የሚቆጥሩ መሆናቸው ነው ትልቁ ድክመታቸው። በነገራችን ላይ ለእነዚህ ሎጆች የሚወጣው ገንዘብ ሲጠራ ያስደነግጣል። ከራሳቸው አንደበት በሰማሁት በሰቃ ሀይቅ ላይ ለሚሰራው ሎጅ 3ቢሊየን ብር ወጥቶበታል። አጃኢብ ነው?!
የእሳቸው ከመናፈሻ ቦታ ግንባታ ጋር የገቡት ቃልኪዳን ያስደምማል። የእስካንዴኒቪያን ሀገራት መሪ እንጂ የአንዲት ኮሳሳ፡ 30ሚሊየን የተራበ ህዝብ ባዶ አንጀቱን ታቅፎ የሚስልባትና የሚተራመስባት ሀገር መሪ አይመስሉም። ይህን እንደስኬት ለማውራት ማይክ ሲጨብጡ ሳይ ስነልቦናቸው ግርም ይለኛል። ለማንኛውም የእሳቸው ነገር ”የምትበላው የላት የምትከናነበው አማራት” በሚል ገልጸነው ወደ ንግግራቸው እንመለስ። የወቅቱን ሁኔታ አንስተዋል። የአቶ ግርማ የሺጥላ ግድያን መነሻ አድርገው የተለመደውን ማስፈራራትና ፉከራ አስምተዋል። ”አትሞክሩን፡ ክንዳችን እሳት፡ ልባችን ተራራ ነው” ሲሉም አይበገሬ መሆናቸውን አስረግጠው ነግረውናል። ስለህግና ሀሳብ ልዕልና አንስተው የፈለገ ይግጠመን ብለዋል። በሁሉም ሜዳዎች የሚችለን የለም በማለትም ትከሻቸውን ገልመጥ እያደረጉ እያዩ ነግረውናል። የአቶ ግርማ የሺጥላን ግድያ ወኔ መቀስቀሺያ፡ ካድሬን ማነቃቂያ፡ ደጋፊን መሰብሰቢያ አድርገው ”ግርማ ይበልጥ አጠናክሮናል” ሲሉም ቀስቅሰውበታል።
ለአቶ ግርማ አሁንም ሰላማዊ እረፍትን እንመኛለን። የገደሏቸው ማንም ይሁን ማን እንዲህ የፖለቲካ መሸቀጪያ የሚያደርጓቸውን ልቦና ይስጣቸው ከማለት ውጪ ምንም ማለት አይገባም። ጠቅላይ ሚኒስትሩና መንግስታቸው ከአቶ ግርማ ግድያ ጀርባ እጃቸው አለበት የሚል በመረጃና ማስረጃ ያልተደገፈ ድምዳሜ መስጠት አያስፈልግም። ዛሬ ሰሜን ሸዋና ጎንደር በይፋ የተከፈተውን ጦርነት ካየን በኋላ ግን ለጠሚ/ሩ የአቶ ግርማ ሞት ሰርግና ምላሽ የሆነላቸው ክስተት ነው ብንል ያስኬዳል። ከአንድ ሳምንት በፊት ከአቶ ግርማ መገደል ቀናት አስቀድሞ የደረሰን መረጃ ጠ/ሚሩ በአማራ ክልል ያለውን መሳሪያ በሙሉ ለመንጠቅ ያቀዱትን ስትራቴጂ ለመፈጸም ለሶስት ወራት ዝግ የሆነ፡ ከየትኛውም ግንኙነት ውጪ በተደረገ መልኩ ዘመቻ ሊከፍቱ እንደተዘጋጁ የሚያሳይ ነበር። ይህን ጦርነት ለመክፈት ፊሽካውን እንዴትና መቼ መንፋት እንዳለባቸው እያሰቡበት ነበር። እንግዲህ የአቶ ግርማን ግድያ እንደፊሽካ ተጠቅመውታል። መንግስታቸው ያድርገውም አያድርገውም ግድያውን ግን ጦርነት ለማወጅ ሰበብ ምክንያት ሆኖላቸዋል። አደረጉትም።
የዛሬው ንግግራቸው ላይ ስለህግ እስከመቃብር ድረስ ታማኝ እንደሆኑ አብዝተው አንስተዋል። የህግ የበላይነት ቢኖርማ ዛሬ እሳቸውና ከእሳቸው ጎን የህሊና ጸሎት ሲያደርግ የነበረው ጌታቸው ረዳ በሚሊዮን ዜጎች ህይወት መጥፋት ቤታቸው ከርቸሌ በሆነ ነበር። ለህግ እንደዚያ ጥሩ ልብና አቋም ቢኖራቸው ኖሮ ከ10ሺህ በላይ የአማራ ተወላጆችን አፍሰው በየማጎሪያ እስር ቤቱ አይቆልፉባቸውም ነበር። በህግ ፍቅር ወድቀው መቃብር ድረስ አብረው ለመዝለቅ ወኔው ቢኖራቸው ኖሮ ሀገርን በቁሟ እየጋጡ ያሉ አውደልዳይ ሹሞቻቸውንና ጥገኛ ባለሀብቶችን ተጠያቂ አድርገው ያሳዩን ነበር። እንደቃላቸው ለህግ ቆራጥ አቋም መውሰድ ቢችሉማ ኖሮ አዲስ አበባ ዙሪያ በመቶ ሺዎች የሚፈናቀሉት ዜጎች ጉዳይ በህግና በህግ ብቻ እንዲታይ በማድረግ እጅግ የሚያስደነግጠውን መጠነ ሰፊ ሰብዓዊ ቀውስ ያስቆሙት ነበር። ስለህግ እንዲህ አብዝተው የሚጨነቁ ቢሆን ኖሮ የትላንቱን አይነት አሳፋሪ ድራማ ከህወሀት ዘመን ጋር ከመቃብር ውስጥ ከተውት በትክክለኛ ፍትህ ዜጎች የሚዳኙበትን ስርዓት ያቆሙ ነበር።
ስለሀሳብ ልዕልና ሲያነሱ መቼም የሚናገሩትን አምኖ የሚቀበል አይጠፋም። በዙሪያቸው በኮሎኮሏቸው፡ ሲጠሯቸው አቤት፡ ሲልኳቸው ወዴት በሚሉ፡ ግዑዛን መከበባቸው ሰውዬውን ስለሌላው ዓለም ምንም ዓይነት እውቀት እንዳይኖራቸው አድርጓል። መለኪያቸው ሳያላምጡ የሚውጡ ደጋፊዎቻቸው ናቸው። መስፈሪያቸው ከህወሀት ዘመን ተንከባለው አሁን ድረስ ከወንበራቸው ጋር እንደሙጫ ተጣብቀው ህዝብን መከራ የሚያበሉ፡ እንደመዥገር ደሙን የሚመጡ ግሳንግስ ባለስልጣናት ናቸው። አንድ ዓይነት ስብስብ። ግራና ቀኝ ማየት የማይችል፡ ቀለል ያለች ሎጂክ ለመረዳት ተራራ መግፋት የሆነባቸው አቅመ ቢሶች የተከማቹበት ፓርቲ። በብሄር ኮታ የተሰበሰቡ፡ ከመንደራቸው ወጥተው ለማሰብ አቅምም ችሎታም የሌላቸው፡ በህሊናና በሆድ መሀል ያለው ድንበር የጠፋባቸው፡
የሀገር እርግማኖች ያቆሙት ፓርቲ መሪ ናቸው እንግዲህ ስለሀሳብ ልዕልና ሊያስረዱን ቴሌቪዥን መስኮት ላይ የተደቀኑት። እስቲ አንዲት ቀለል ያለች ጥያቄ ላንሳባቸው። መቼ ይሆን ለጋዜጠኞች ክፍት የሆነ መድረክ የሚሰጡት? ሀሳብ የማይፈሩ ከሆነ ባለፉት አምስት ዓመታት ስለምንስ ብለው ጋዜጣዊ መግለጪያን ሲሸሹ ከረሙ? አቶ መለስ ዜናዊ አድርገውት ኖረዋል። አቶ ሃይለማርያም ደሳለኝም በዘመናቸው ለጋዜጠኞች ቅርብ ነበሩ። የእርስዎ ሽሽት ለምን ይመስልዎታል? ማይክ ጨብጦ ዲስኩር ማንበልበል? የሚጠይቅ ሳይኖር፡ ራስ ተናግሮ ብቻ ለራስ ማጨብጨብ? ታዲያ እንዴት መንግስትዎን ከሀሳብ ልዕልና ጋር ያስታርቁታል?
ጂኒዎችዎ ሰሜን ሸዋን ደም እየቀቡ ነው። የላኩት የሞት መልዕክተኛ ሰሜን ጎንደር ላይ ንጹሃንን እየገደለ ነው። በዚህ አካሄድዎ መንግስትዎ የሚጸና አይሆንም። ስለሀሳብ ልዕልና የመናገር የሞራል ደረጃ ላይ አልደረሱም። እንደልማድዎ በሀይል ይሞክሩት። መጨረሻው ግን እንደበፊቱ እንደማይሆን ማረጋገጥ ይገባል።
(መሳይ መኮንን እንደፃፈው)
