
ከ 4 ሰአት በፊት
አሜሪካ የሰሜን ኢትዮጵያውን ጦርነት ለማብቃት በተደረሰው ስምምነት መሠረት ውጤታማ ትጥቅ የማስፈታት እና ተያያዥ ተግባራትን ለማጠናቀቅ ተጨማሪ ተቆጣጣሪዎች እንዲሰማሩ ጠየቀች።
በኢትዮጵያ ፌደራል መንግሥት እና በህወሓት መካከል ለሁለት ዓመታት የተካሄደውን ጦርነት ለማብቃት ፕሪቶሪያ ላይ የተደረሰው ስምምነትን ስድስተኛ ወር ምክንያት በማድረግ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ባወጣው መግለጫ ሊከናወኑ የሚገቡ ተግባራትን አመልክቷል።
በዚህም መሠረት የሰላማዊ ሰዎችን ጥበቃ እና ውጤታማ ትጥቅ የማስፈታት፣ ታጣቂዎችን የማሰናበት እና ከኅብረተሰቡ ጋር መልሰው የሚቀላቀሉበትን ሂደት የሚከታተሉ ተቆጣጣሪዎች በማሰማራት በስምምነቱ ላይ የተቀመጡ ሃሳቦች መቋጫ እንዲበጅላቸው አሜሪካ ጠይቃለች።
በተጨማሪም የኤርትራ ጦር እና ከፌደራል መንግሥቱ ሠራዊት ውጪ ያሉ ኃይሎች ሙሉ ለሙሉ ከትግራይ እንዲወጡ መደረግ እንዲሁም የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን የፈጸሙ እና ተሳታፊዎችን ተጠያቂ ማድረግን ጨምሮ ተአማኒ የሽግግር ፍትሕ ሂደት በሰሜን ኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም ለማስፈን ቁልፍ ጉዳዮች ናቸው ብሏል የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤቱ።
- የፕሬስ ነጻነት ሁኔታ በኢትዮጵያ እና ጋዜጠኞች የሚገጥሟቸው ተግዳሮቶችከ 5 ሰአት በፊት
- ወደ ትግራይ የየብስ ትራንስፖርት መጀመር እና የክልል ርዕሳነ መስተዳድሮች ጉብኝት27 ሚያዚያ 2023
- የዓለም ምግብ ፕሮግራም በትግራይ የእርዳታ አቅርቦቱን ለጊዜው አቋረጠ2 ግንቦት 2023
በመንግሥት እና በህወሓት መካከል በተደረሰው ስምምነት መሠረት ከአገሪቱ የመከላከያ ሠራዊት ውጪ ያሉ ኃይሎች ከትግራይ ክልል እንደሚወጡ እንዲሁም የህወሓት ተዋጊዎች ትጥቅ እንደሚፈቱ መገለጹ ይታወሳል።
ስምምነቱ ከተፈረመ ስድስት ወራት የተቆጠሩ ሲሆን፣ በርካታ አውንታዊ እርምጃዎች መወሰዳቸውን የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት በመግለጫው ላይ አመልክቷል።
ሁለት ዓመታት ለሚሞላ ጊዜ በትግራይ ተቋርጠው የቆዩ መሠረታዊ አገልግሎቶች መልሰው ሥራ መጀመራቸው፣ የሰብአዊ እርዳታ ያለገደብ መቅረቡ፣ ህወሓት ከባድ የጦር መሳሪያዎችን ማስረከቡ፣ እስረኞች መፈታታቸው፣ ሁሉን አካታች የሽግግር ፍትህ ሂደት መጀመር እና በትግራይ ጊዜያዊ መስተዳደር መቋቋሙ ተጠቅሷል።
ይህ በሰሜን ኢትዮጵያ የተከናወነው ስኬታማ የሰላም ሂደትም በኦሮሚያ ክልል ሰላም ለማምጣት ዕድል መፍጠሩን መግለጫው አመልክቶ፣ በመንግሥት እና በኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት መካከል የተጀመረውን ንግግር አድንቋል።
ሁለቱም ወገኖች “ለሁሉም ተቀባይነት ያለው ስምምነት ላይ ለመድረስ “በቅን ልቦና” እንዲደራደሩ አሜሪካ ታበረታታለች ብሏል መግለጫው።
ትግራይ ውስጥ ተቀስቅሶ የሰሜን ኢትዮጵያን ክልሎች ያዳረሰው ደም አፋሳሹን ጦርነት ለማብቃት በኢትዮጵያ መንግሥት እና በህወሓት መሪዎች መካከል ዘላቂ ግጭት የማቆም ስምምነት የተደረሰው ጥቅምት 23/2015 ዓ.ም. ነበር።
በአፍሪካ ኅብረት መሪነት በተካሄደው ድርድር አሜሪካ በታዛቢነት መሳተፏን ብትገልጽም፣ ሁለቱ ወገኖች ከስምምነት ላይ እንዲደርሱ ከፍተኛ ሚና እንደነበራት ይታመናል።
የጦርነቱም መቀስቀስ ተከትሎ ንግግር እንዲደረግ ግፊት ስታደርግ የነበረችው አሜሪካ ልዩ መልዕክተኛ በመሰየም ቀውሱን በቅርበት ስትከታተል እና መፍትሄ እንዲያገኝም ድጋፍ ስታደርግ ቆይታለች።
