May 3, 2023 – EthiopianReporter.com 

ዶ/ር ሳሙኤል አርቃቶ የኢፌዴሪ ሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ኮሚሽነር/

ዜና በዓለም ባንክ ድጋፍ በሚከናወኑ ፕሮጀክቶች ላይ ሙስናና ብልሹ አሠራሮች እንደሚፈጸሙ ተገለጸ

ሔለን ተስፋዬ

ቀን: May 3, 2023

በዓለም ባንክ ድጋፍ በሚከናወኑ ሰባት ፕሮጀክቶች ላይ ሙስናና ብልሹ አሠራሮች የሚፈጸሙ ቢሆንም በሪፖርት ውስጥ እንደማይካተቱ፣ የፌዴራል ሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን አስታወቀ፡፡

ኮሚሽኑ ይህንን ያስታወቀው ሚያዝያ 21 ቀን 2015 ዓ.ም. በአዳማ ከተማ በዓለም ባንክ ዕገዛ በሚከናወኑ ሰባት ፕሮጀክቶችን በሚመለከት ከባለ ድርሻ አካላት ጋር በነበረው የውይይት መድረክ ነው፡፡ በዓለም ባንክ ድጋፍ ከሚከናወኑ ፕሮጀክቶች የከተማና መሠረተ ልማት፣ የግብርና ዘርፍ፣ የትምህርት ጥራትን ጨምሮ ሌሎችም ፕሮጀክቶች ይጠቀሳሉ፡፡

የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽነር ሳሙኤል ኡርቃቶ (ዶ/ር)፣ ፕሮጀክቶቹን በተመለከተ በዓመት ሁለት ጊዜ ሪፖርት እንደሚያቀርብ ጠቅሰው፣ በዚህም ከሙስናና ብልሹ አሠራሮች ነፃ መሆናቸው ተጠቅሶ ለዓለም ባንክ ሪፖርት እንደሚደረግ በመድረኩ ላይ ተናግረዋል፡፡

ኮሚሽኑ የፕሮጀክቶቹን አፈጻጸም በቅርበት በመከታተል ሪፖርት እንዲያቀርብ ከዓለም ባንክ ጋር ስምምነት እንዳለው በመጠቆም፣ በዓመት ሁለት ጊዜ ከሙስናና ከብልሹ አሠራሮች የፀዱ ስለመሆናቸው የማረጋገጫ ሪፖርት እንደሚያቀርብ ተናግረዋል፡፡

ይሁን እንጂ ፕሮጀክቶቹ ክፍተቶች እንዳሉባቸው አውስተው፣ ሌሎች ድጋፎች እንዳይቋረጡ በማለት ሪፖርቱ ሙሉ በሙሉ ወይም ከእነ ችግሮቻቸው እንደማይቀርብ አስረድተዋል፡፡ የዓለም ባንክ ብድርና ድጋፎችን የሚሰጠው የኮሚሽኑን ሪፖርት እንደ ቅድመ ሁኔታ በመውሰድ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

‹‹ለዓለም ባንክ ሪፖርት ማቅረብ የስምምነት ማሟያ ብቻ አይደለም›› ያሉት ኮሚሽነሩ፣ ገንዘብ ሚኒስቴርም ከባንኩ ለአገር ኢኮኖሚ የሚያስፈልገውን ፋይናንስ ለማምጣት ጭምር መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

ዓለም ባንክ የኮሚሽኑን ሪፖርት እንደ መሥፈርትነት እንደሚጠቀም የገለጹት ሳሙኤል (ዶ/ር)፣ ኢትዮጵያ የውጭ ምንዛሪ ከምታገኝባቸው መንገዶች አንዱና ዋነኛው መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ዓለም ባንክ ሰባቱ ፕሮጀክቶች ተግባራዊ እንዲሆኑ 3.4 ቢሊዮን ዶላር ከ2004 ዓ.ም. ጀምሮ ድጋፍ ያደረገ ቢሆንም፣ በተለያዩ ምክንያቶች የተራዘሙ ፕሮጀክቶችና ሊጠናቀቁ የደረሱ መኖራቸውም ተጠቁሟል፡፡

እንደ ኮሚሽነሩ ገለጻ፣ ፕሮጀክቶቹን በዋናነት የሚያስፈጽሙ ተቋማት ሙስናና ብልሹ አሠራሮች ጥቆማዎችን ለመቀበልና ሪፖርቱን ለመላክ ይዘገያሉ፡፡

ሙስና ሳይፈጸም በፊት ጥቆማዎች ሲደርሳቸው ለመቀበል ዝግጁ አለመሆናቸውን፣ ሙስናን ለመከላከል ያለመፈለግና ተፈጽሞ ሲገኝ አስተማሪ ዕርምጃ መውሰድ ላይ ተቋማቱ ክፍተት እንዳለባቸው አስረድተዋል፡፡

ሰባቱን ፕሮጀክቶች በበላይነት የሚያሠሩ ተቋማት ሙስናና ተያያዥ ጉዳዮችን ሪፖርት በጊዜው እንደማያቀርቡ ተናግረዋል፡፡ ይሁን እንጂ ኮሚሽኑ ዓለም ባንክ ለሪፖርት ከማቅረብ በተጨማሪ፣ በሙስናና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ የተሳተፉትን ለሕግ ለማቅረብ በርካታ ሥራዎች እየተከናወኑ እንደሚገኙ ጠቁመዋል፡፡

ፕሮጀክቶቹ ወደ ታች መዋቅር ሲደርሱ በተለያዩ ምክንያቶች በጀቱ ይሸራረፋል ሲሉ ያለውን ችግር በስፋት በመድረኩ ገልጸዋል፡፡ በዕለቱ ሪፖርት ያቀረቡት የኮሚሽኑ የፕሮጀክት ከፍተኛ አስተባባሪ አቶ ታደሰ ደምሴ በበኩላቸው፣ ፕሮጀክቱ በታችኛው መዋቅር ላይ በታሰበለት ጊዜ ያለመፈጸም፣ የካሳ ክፍያ በጊዜ ያለ መክፈል ሙስናና ማጭበርበር ወንጀል ላይ የታዩ ግለሰቦች አሉ ብለዋል፡፡

በተያዘው በጀት ዓመት በስድስት ወራት ሪፖርት አፈጻጸም፣ ከትግራይ ክልል ውጪ በሁሉም ክልሎች ሙስናና ብልሹ አሠራሮች ምክንያት፣ 357 ጥቆማዎች እንደደረሳቸው አቶ ታደሰ ሪፖርቱን ሲያቀርቡ ተናግረዋል፡፡

በዚህ ጥቆማ መሠረት ከ4.9 ሚሊዮን ብር በላይ ሊሸሽ የነበረ ሀብት ወደ መንግሥት ካዝና መመለሱን ጠቁመው፣ ሕጋዊ ዕርምጃም የተወሰደባቸው መኖራቸውን ገልጸዋል፡፡ ከእነዚህ ውስጥ 11 ኃላፊዎች አስተዳደራዊ ዕርምጃ እንደተወሰደባቸው በመግለጽ፣ ስድስቱ በፍርድ ቤት ጉዳያቸው መያዙን ገልጸዋል፡፡