May 3, 2023 – EthiopianReporter.com 

ዜና መንግሥት ሲቪል ማኅበራት የዘፈቀደ እሥራትን በተመለከተ ያቀረቡትን ምክረ ሐሳቦች እንዲተገብር ተጠየቀ

ኤልያስ ተገኝ

ቀን: May 3, 2023

መንግሥት ከሕግ ውጪ የዘፈቀደ እስራትን በተመለከተ፣ በሲቪል ማኅበራት ተወካዮች ተጣርተው የቀረቡ መረጃዎችንና ምክረ ሐሳቦችን በመቀበል ተግባራዊ እንዲያደርግ ጥያቄ ቀረበለት፡፡

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ጥያቄውን ያቀረበው በባህር ዳር፣ በጅግጅጋና በሐዋሳ ከተሞች ያካሄደውን ግልጽ የምርመራ ውይይቶች ካደረገ በኋላ በአዳማ ከተማ ባዘጋጀው አራተኛው ግልጽ የምርመራ መድረክ መሆኑን አስታውቋል፡፡

በመድረኩ በተለይም የዘፈቀደ እስርን፣ የተራዘመ የቅድመ ክስ እስርና በእስር ወቅት ተከስተዋል ስለተባሉ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት፣ ተጎጂዎችና ምስክሮች ያቀረቧቸው አቤቱታዎች፣ እንዲሁም ጉዳዩ በሚመለከታቸው አካላት የተሰጡ ምላሾች መደመጣቸውን ኮሚሽኑ ለመገናኛ ብዙኃን በላከው መግለጫ አስታውቋል።

በኦሮሚያ ክልል ነፃነታቸውን ከሕግ አግባብ ውጪና በዘፈቀደ የተነፈጉ ሰዎች መብቶች ላይ ያተኮረ የምርመራና ክትትል ግኝቶች ያሏቸው አካላት ይህንኑ እንዲያቀርቡ ኮሚሽኑ ጥሪ ካደረገ በኋላ፣ መቀመጫውን በውጭ ያደረገ ኦሮሞ ሌጋሲ ሊደርሺፕ ኤንድ አድቮኬሲ አሶሴሽን (OLLAA) የተባለ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅትን ጨምሮ፣ ሌሎችም የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች መረጃዎችና ትንተናዎች በጽሑፍ ለኮሚሽኑ ከማስገባታቸው በተጨማሪ፣ በበይነ መረብ ሐሳባቸውን እንዳቀረቡ ተገልጿል፡፡

በመድረኩ የሲቪል ማኅበራት ተወካዮች ከሕግ ውጪ የሆኑና የዘፈቀደ እስራትን በተመለከተ አጣርተው ደርሰንበታል ያሉትን መረጃዎች በመድረኩ ቀርቦ፣ የመንግሥት አካላት ምክረ ሐሳቦቻቸውን በመቀበል ተግባር ላይ እንዲያውሉና ለሰብዓዊ መብቶች መከበር አብረዋቸው እንዲሠሩ ጥሪ ማቅረባቸው ተጠቁሟል፡፡

በግልጽ የምርመራ መድረኩ ተመርጠው ከቀረቡት 18 አቤቱታዎች መካከል ያለ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ መያዝና መደበኛ ባልሆኑና በማይታወቁ ቦታዎች በእስር ማቆየት፣ በሕግ በተቀመጠው ጊዜ መሠረት የታሰረን ሰው ፍርድ ቤት አለማቅረብ፣ እንዲሁም የፍርድ ቤት የዋስትና መብት ትዕዛዝ አለማክበር እንደሚገኝበት ተገልጿል፡፡

የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ደርሶብናል የሚሉ ሰዎች፣ ምስክሮች፣ ሌሎች ባለድርሻ አካላት፣ እንዲሁም የሚመለከታቸው የመንግሥት ተወካዮች በአንድ መድረክ በተገኙበት በሕዝብ ፊት የሚከናወን የምርመራ ሥልት፣ ግልጽ የምርመራ መድረክ እንደሚባል በመግለጫቸው ተገልጿል።

በግልጽ የምርመራ መድረክ አቤቱታ አቅራቢዎች ደርሶብናል የሚሏቸውን የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት ላይ፣ በግልጽ ምስክርነት መስጠትና ማስረጃ ማቅረብ የሚችሉ መሆኑን፣ በሚሰጡት ቃል ሚስጥራዊ ባህሪ ወይም የደኅንነት ሥጋት ያለባቸው ሰዎች ደግሞ በልዩ ሁኔታ በሚስጥር ቃላቸውን የሚሰጡበትን ዕድልንም እንደሚያካትት ኢሰመኮ አስታውቋል፡፡

የተፋጠነ ፍትሕ የማግኘት መብት፣ በእስር ወቅት በቤተሰብ የመጎብኘት መብት፣ በቂ ምግብ፣ ውኃ፣ መፀዳጃና ሕክምና የማግኘት መብት አለማክበርና ጭካኔ የተሞላበትና የማሰቃየት ድርጊት መፈጸም በቀረቡት አቤቱታዎች በተደጋጋሚ ከተጠቀሱት የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ውስጥ እንደሚገኙበት ኢሰመኮ ይፋ አድርጓል፡፡

የኢሰመኮ የሲቪል፣ የፖለቲካ፣ የማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ መብቶች ኮሚሽነር  አብዲ ጅብሪል (ዶ/ር) በመድረኩ ላይ ባደረጉት የማጠቃለያ ንግግር፣ ‹‹በግልጽ የምርመራ መድረኩ ተጎጂዎች፣ ባለግዴታዎችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት በሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶች ዙሪያ በግልጽ መነጋገር መቻላቸው፣ እንዲሁም ለወደፊት ሊወሰዱ ስለሚገባቸው ዕርምጃዎች በሁሉም አካላት በኩል ለመደጋገፍ የመፍትሔ ሐሳቦች መቅረባቸው የሚያበረታታ ነው፤›› ብለዋል። 

ከአንድ ወር አስቀድሞ በባህር ዳር ከተማ ከመጋቢት 19 ቀን እስከ መጋቢት 21 ቀን 2015 ዓ.ም. በተዘጋጀው ሦስተኛው ዙር የግልጽ የምርመራ መድረክ የተገኙት የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዳንኤል በቀለ (ዶ/ር)፣ በብዙ አገሮች ብሔራዊ የሰብዓዊ መብቶች ተቋማት የተለመደውና በኢትዮጵያ ለመጀመርያ ጊዜ ተግባራዊ መደረግ የጀመረው የግልጽ ምርመራ መድረክ ለሰብዓዊ መብቶች መከበርና መጠበቅ ያለውን ጠቀሜታ ተናግረው፣ በዚህ ዓይነት መድረክ ላይ የቀረቡ ሰዎች በሚሰጡት ምስክርነት ወይም ማስረጃ በተለይ ከመንግሥት አካላት ምንም ዓይነት አፀፋዊ ዕርምጃ እንዳይወሰድባቸው አበክረው ማሳሰባቸው አይዘነጋም፡፡