May 3, 2023 

“የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት” ቁልፍ በሆኑ የፖለቲከ ጉዳዮች ላይ መግባባት አልታቻለም አለ

(አዲስ ማለዳ) “የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት” ከመንግሥት ጋር ባደረገው የመጀመሪያው ምዕራፍ ድርድር ቁልፍ በሆኑ የፖለቲካ ጉዳዮች መግባባት ላይ አለመደረሱን አስታወቀ፡፡

ራሱን “የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት” ብሎ የሚጠራውና በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አሸባሪነት የተፈረጀው “ኦነግ ሸኔ” ባወጣውና ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር ተመሳሳይነት ባለው መግለጫ ፤ በታንዛኒያ ሲካሄድ የነበረው የመጀመሪያው ምዕራፍ የሰላም ንግግር ዛሬ መጠናቀቁን አስታውቋል።

በውይይቱ በአንዳንድ አንኳር ጉዳዮች ላይ መግባባት ላይ መደረሱን የገለጸው የኦሮሞ ነፃነት ሰራዊት፤ ነገር ግን ቁልፍ በሆኑ የፖለቲካ ጉዳዮች ላይ በዚህኛው ምዕራፍ ስምምነት ላይ መድረስ አለመቻሉን ገልጿል።

ኹለቱም ወገኖች ግጭቱን በዘላቂነትና ሰላማዊ በሆነ መንገድ ለማስቆም እንዲቻል የሰላም ውይይቱን መቀጠል አስፈላጊ ስለመሆኑ መግባባት ላይ መድረሳቸውንም በመግለጫው አሳውቋል።

በመግለጫው አክሎም፤ የኦሮሞ ነፃነት ሰራዊት በኦሮሚያ ክልል ያለው ግጭት በሰላማዊ መንገድ እንዲፈታ ቁርጠኛ መሆኑን አረጋግጧል።

የፌደራሉ መንግሥት ቀደም ብሎ ባወጣው መግለጫ፤ የታንዛኒያው የመጀመሪያ ምዕራፍ የሰላም ንግግር በአብዛኛው በአዎንታዊ መልኩ መከናወኑን በመግለጽ፤ ነገር ግን በአንዳንድ ጉዳዮች ላይ በዚህኛው የውይይት ምዕራፍ ስምምነት ላይ ለመድረስ አለመቻሉን አስታውቋል።

ነገር ግን ግጭቱን በዘላቂነትና ሰላማዊ በሆነ መንገድ ለማስቆም፤ ኹለቱም አካላት በሰላም ውይይቱ ቀጣይነት ላይ መግባባት ላይ መድረሳቸውን ገልጿል።

ኹለቱም ተደራዳሪ አካላት በታንዛኒያው የሰላም ድርድር፤ በምን ጉዳዮች ላይ ተወያይተው መግባባት ላይ እንደደረሱና በምን በምን ጉዳዮች ላይ ስምምነት ላይ መድረስ እንዳልቻሉ በመግለጫቸው ይፋ አላደረጉም።