
3 ግንቦት 2023, 16:28 EAT
ዩክሬን በፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን መኖሪያ ቤተ መንግሥት ላይ ጥቃት በመሰንዘር ልትገድላቸው ሞክራለች ስትል ሩሲያ ከሰሰች።
ማክሰኞ ምሽት የፕሬዝዳንት ፑቲን ቤተመንግሥትን ኢላማ ያደረጉ ሁለት ድሮኖችን ጥያለሁ ያለችው ሩሲያ፣ ዩክሬን ፑቲንን ለመግደል እየሞከረች ነው ስትል ከሳለች።
የክሬምሊን ቤተመንግሥት ባለሥልጣናት እንዳሉት ለጥቃት የተሰማሩት ድሮኖችን የፕሬዝዳንቱ ጥበቃ ኃይል በኤሌክትሮኒክ ራዳር ከጥቅም ውጪ አድርገዋቸዋል።
የፕሬዝዳንቱ ቃል አቀባይ ዲሜትሪ ፔስኮቭ ለአገሪቱ መንግሥት የዜና ወኪል እንደተናገሩት፣ ፑቲን በወቅቱ ክሬምሊን ውስጥ አልነበሩም፤ እንዲሁም በቤተመንግሥቱ ሕንጻዎች ላይ ምንም አይነት የደረሰ ጉዳት የለም ብለዋል።
ዩክሬን የቀረበባትን ክስ በተመለከተ ምንም አይነት አስተያየት ለመስጠት እንደማትፈልግ ገልጻለች።

- “ባለፉት አምስት ወራት ብቻ 20 ሺህ የሩሲያ ወታደሮች በዩክሬን ጦርነት ሞተዋል” አሜሪካ2 ግንቦት 2023
- የሩሲያው ቅጥረኛ ተዋጊ ቡድን (ቫግነር) በሱዳን ምን እየሠራ ነው?25 ሚያዚያ 2023
- የፑቲን ቃል አቀባይ ልጅ በዩክሬን ዋግነር ቡድን ተቀላቅሎ መዋጋቱ ተነገረ24 ሚያዚያ 2023
በሩሲያ ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ የተሰራጩ እና እውነተኛነታቸው ያልተረጋገጡ ቪዲዮዎች ዛሬ ረቡዕ ጠዋት ላይ ከማዕከላዊ የሞስኮ ክፍል የሚነሳ ጭስ አሳይተዋል።
ከክሬምሊን በተሰጠ መግለጫ ላይ “ባለፈው ምሽት የዩክሬን መንግሥት ሰው አልባ አውሮፕላኖችን በመጠቀም ክሬምሊን ውስጥ በሚገኘው የሩሲያ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት መኖሪያ ቤት ላይ ጥቃት ለመሰንዘር ሞክሯል።”
ጨምሮም “ፕሬዝዳንቱን ለመግደል የታቀደ የሽብር ተግባር በመሆኑ፣ ሩሲያ አስፈላጊ በሆነ በየትኛው ቦታ እና ጊዜ የአጸፋ እርምጃ የመውሰድ መብት አላት” ብሏል።
ከጥቅም ውጪ እንዲሆኑ ተደርገዋል የተባሉት ድሮኖች ስብርባሪ በክሬምሊን ቤተመንግሥት ግቢ ውስጥ የወደቁ ሲሆን፣ ምንም ጉዳት እንዳላደረሱ ተገልጿል።
መግለጫው በፕሬዝዳንት ፑቲን ላይ ምንም አይነት ጉዳት አለመድረሱን እና ያሏቸው መረሃ ግብሮች በሙሉ በተያዘላቸው ቅደም ተከተል መሠረት በተለመደው ሁኔታ ይካሄዳሉ ብሏል።
ይህ ጥቃት የተፈጸመው የውጭ አገራት እንግዶች የሚታደሙበት እና ከቀናት በኋላ ከሚከበረው ከሩሲያ የድል ቀን በዓል ቀደም ብሎ መሆኑን የፕሬዝዳንቱ ጽህፈት ቤት ጠቅሷል።
በሩሲያ የቀረበውን ክስ በተመለከተ ቢቢሲ የዩክሬን ፕሬዝዳንት ጽህፈት ቤትን አስተያየት የጠየቀ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት በጉዳዩ ላይ አስተያየት መስጠት እንደማይፈልጉ ገልጸዋል።
