May 4, 2023 

የጅማ አገር ስብከት ከእውቅናው ውጭ ለኹለተኛ ጊዜ የተመደቡትን ‹‹ጳጳስ›› ለመቀበል ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ገለጸ

የኦሮሚያ እና የብሔር ብሔረሰብ ሲኖዶስ በማለት ራሳቸውን የሚጠሩ አካላት ከጅማ ሀገረ ስብከት እውቅና ውጭ የሆነ ስብሰባ ማካሄዳቸውንና ያለ አገረ ስብከቱ እውቅና ለኹለተኛ ጊዜ የመደቧቸውን ጳጳስ ለመቀበል ሕገወጥ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑ ተገልጿል፡፡

አገረ ስብከቱ ፈቃድና እውቅና ሳይሰጥ በአገረ ስብከቱ ማህበረ ካህናትና ምዕመናን ሥም በጅማ ከተማ የተካሄደው ስብሰባ ሕገወጥ መሆኑን የተገለጸ ሲሆን፤ በሕገወጥ መንገድ ከተሾሙት መካከል አባ ሚናስ የተባሉ ለሀገረ ስብከቱ እንደተመደቡና ለእሳቸውም አቀባበል ለማድረግ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን መረጃ እንደደረሰው አገረ ስብከቱ ለአዲስ ማለዳ ገልጿል፡፡

ይህም የተደረገው በጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ አቀራራቢነት የተደረሱትን አስር የስምምነት ነጥቦች በመተላለፍ እንዲሁም፤ በኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ፕሬዘዳንት ሽመልስ አብዲሳ አሳሳቢነት ተሾምን ያሉ መነኮሳት አባቶች በሙሉ ወደ ቤተ ክርስቲያኒቱ ተመልሰው በሕግና ሥርዓት መሠረት እንዲሄዱ የተደረሰውን ውሳኔ ወደጎን በመተው ነው ተብሏል፡፡

ከዚህ ቀደም በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ሕገወጥ ነው በተባለው የኦሮሚያና የብሄር ብሔረሰቦች ሲኖዶስ አማካኝነት፤ አባ ተክለሀዋርያት (በቀድሞ ስማቸው አባ ኪዳነማርያም ቶሎሳ) ለጅማ አገረ ስብከት ተመድበው የነበረ ሲሆን፤ አሁን ደግሞ አባ ሚናስ የተባሉ ሌላ አባት በሕገወጥ መንገድ ለኹለተኛ ጊዜ ለአገረ ስብከቱ መመደባቸው ነው የተገለጸው፡፡

በተጨማሪም፤ ያለ መደበኛው መዋቅር በጅማ ከተማ ለተከናወነው ሕገወጥ ስብሰባ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን የጅማ ሀገረ ስብከት የካህናትና የምዕመናን ሕብረት በወቅታዊ ጉዳይ ላይ ተወያይቷል የሚል ዘገባ ያሰራጨውን እና የዘገባ ሽፋን የሰጠውን ፕራይ ሚዲያን በሕግ እንደሚጠይቅ የሀገረ ስብከቱ ጽህፈት ቤት አስታውቋል፡፡

በሌላ በኩል፤ በኦሮሚያ ክልል በሚገኙ አህጉረ ስብከቶች መንፈሳዊ አገልግሎት የሚሰጠው ወልዳ ዳንዲ አቦቲ ማክሰኞ ሚያዚያ 24/2015 ባወጣው መግለጫ፤ በመጪው ግንቦት ወር የሚደረገው የአዳዲስ ኤጲስ ቆጶሳት ምልመላና ምርጫ ለቤተክርስቲያኒቱ በሚጠቅም መልኩ ማድረግ እንደሚገባ በመግለጽ፤ ምርጫው ግልጽ እና ፍትሐዊ እንዲሆን ጠይቋዋል፡፡

 (አዲስ ማለዳ)