May 4, 2023
ከጎንደር ከተማ ጀምሮ ወደ ስሜን ጎንደር አቅጣጫ የሚገኙት የአምባ ጊዮርጊስ፣ የገደብየ፣ የዳባት፣ የወቅን እና የደባርቅ ከተሞች በሕዝባዊ ተቃውሞ ሙሉ ለሙሉ ዝግ ናቸው።
በአማራ ሕዝብ ላይ ያላባራው ግፍ ሳይበቃ አሁን ደግሞ እራሱን መከላከል እንዳይችል መሳሪያ እንንጠቅህ ነው የተባለው።
ከወለጋ ጀምሮ በብዙ የኦሮሞ ክልል ያለቀው እራሱን መከላከል የማይችል አማራ ነው። በመተከልም ተመሳሳይ ነው። አዲስ አበባ ላይ በተደጋጋሚ በር እየተዘጋ በይፋ አማራ አትገባም ተብሎ ሲከለከል ባጀ።
ትህነግ በተደጋጋሚ ያደረሰበትን ወረራ እና ጥቃት ለመመከት የተገደደው አማራ ከራሱ አልፎ ሃገር ታድጓል።
የአራት ኪሎው ገዥ ቡድንም ከሃገር ለመኮብለል ሻንጣ ሸካፊው ብዙ ነበር።
ያ ሁሉ ታልፎ አሁን ደግሞ በገዛ ቀየው፣ አርሶ በሰላም በሚኖርበት ትሪቱን አፍስሶ እራሱን ከጥቃት የሚከላከልበትን የመጨረሻ የህልውና ማስጠበቂያውን እንንጠቅህ ነው የተባለው።
በአማራ ጠል ቡድኖች አማራን ዱላውን ሳይቀር እንንጠቀው ያሉትን በገቢር ሊተገብሩ ነው ሰራዊት ያዘመቱት። ሃቁ ያ ነው።
ከዛም አልፎ ቋሚ በጠላትነት የፈረጁት እርስቱን መልሰው ሊቀሙ ማንነቱን ድጋሜ ሊያጠፉት እንዳሰፈሰፉ ማንም አይስተውም።
ሰሚ ካለ ተው! ማንም በህልውናው አይደራደርም!
Source_Muluneh Yohannes


