ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን
የምስሉ መግለጫ,ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን

ከ 1 ሰአት በፊት

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን የሚካሄደው ውጊያ እንዲቆም በማሳሰብ በሱዳን ግጭት ውስጥ ተሳታፊ በሆኑ ግለሰቦች ላይ ማዕቀብ ለመጣል የሚያስችል ውሳኔ አሳለፉ።

ባይደን በሱዳን እየተካሄደ ያለውን “ግጭት አሰቃቂ እና በአገሪቱ ሕዝብ ላይ የተፈጸመ ክህደት ነው” ብለውታል።

ሳምንታት ያስቆጠረው እና በዋነኞቹ የአገሪቱ ጦር ጄኔራሎች በሚመሩት ኃይሎች መካከል እየተካሄደ ያለው ውጊያ በሱዳን ውስጥ ቀውስን ከማስከተል አልፎ አካባቢውን ሊያናጋ ይችላል የሚል ስጋት ፈጥሯል።

በሱዳን የሚካሄደው ውጊያ “ያልተለመደ እና ለአሜሪካ ብሔራዊ ደኅንነት እንዲሁም ለውጭ ጉዳይ ፖሊሲ የተለየ ስጋት ነው” ብለውታል።

ባይደን ባወጡት መግለጫ ያስተላለፉት ትዕዛዝ “የሱዳንን ሰላም፣ ደኅንነት እና መረጋጋትን አደጋ ላይ የጣሉ፤ የአገሪቱን ዴሞክራሲያዊ ሽግግርን ያደናቀፉ፤ በሰላማዊ ሰዎች ላይ ጥቃት የፈጸሙ፤ ወይም ከባድ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን የፈጸሙ” ግለሰቦችን ተጠያቂ የሚያደርግ ነው።

በተጨማሪም “ዘላቂ የተኩስ አቁም” ተደርጎ የሰብአዊ እርዳታ አቅርቦት እንዲመቻች እና በአገሪቱ ውስጥ ያሉ ዜጎቿን ለመርዳት አሜሪካ ዲፕሎማሲያዊ አማራጮችን መጠቀሟን ትቀጥላለች ብለዋል ባይደን።

ፕሬዝዳንቱ ይህንን ውሳኔ ከማሳለፋቸው በፊት የአሜሪካ ብሔራዊ ደኅንነት መረጃ ዳይሬክተር የሆኑት አቭሪል ሄይንስ፣ ለአገሪቱ ምክር ቤት ኮሚቴ እንደተናገሩት፣ ሁለቱም ወገኖች በወታደራዊ ኃይል ማሸንፍ እንደሚችሉ ስለሚያምኑ እና እንዲደራደሩ የሚያበረታታ ብዙም ነገር ስለሌለ የሱዳን ግጭት ተራዝሞ የሚቀጥል ነው ብለዋል።

ተፋላሚዎቹ በአገሪቱ ጦር ሠራዊት አዛዥ ጄኔራል አብደል ፋታህ አል ቡርሐን እና በፈጥኖ ደራሽ ኃይል መሪ ጄኔራል አህመድ ዳጋሎ የሚመሩት አንጃዎች ናቸው።

ሁለቱ ጄኔራሎች ሱዳን ወደ ሲቪል አስተዳደር በምትመለስበት እና የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ወደ አገሪቱ ሠራዊት በሚካተትበት ዕቅድ ላይ መግባባት ባለመቻላቸው ነው ጦርነቱ የተቀሰቀሰው።

ተፋላሚዎቹ ኃይሎች ለሰባት ቀናት የሚቆይ የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ ቢደርሱም ሳይከበር ውጊያው ቀጥሏል። በተለይ በዋና ከተማዋ ካርቱም እና በአቅራቢያዋ በሚገኙት በኦምዱርማን እና ባሕሪ ከተሞች ውስጥ ከባድ ውጊያ እየተደረገ ነው።

ፕሬዝዳንት ባይደን በሱዳን ያለው ቀውስ እንዲያበቃ ለማገዝ ይረዳል የተባለውን ውሳኔያቸውን ያሳለፉት፣ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች የሞቱበት እና በርካታ ሺዎች የተጎዱበት ጦርነት ከተቀሰቀሰ ሦስት ሳምንት ሊሞላው በተቃረበበት ወቅት ነው።

አሜሪካ ሁኔታዎች በፈቀዱት ሁሉ በሱዳን የሚካሄድ የሰብአዊ እርዳታ አቅርቦቶችን ለመደገፍ እንደምትሰራ የገለጹት ባይደን፣ በዋናነት ግጭት ቆሞ ሰላም እንዲወርድ ጠይቀዋል።

ከሦስት ሳምንት በፊት ግጭቱ ከተጀመረ በኋላ ከ500 በላይ ሰዎች ሲገደሉ በሺዎች የሚቆጠሩ ደግሞ ጉዳት ደርሶባቸዋል። እንዲሁም ከ100 ሺህ የሚልቁ ሱዳናውያን አገራቸውን ለቀው ሲሰደዱ፣ ከ300,00 በላይ የሚሆኑ ደግሞ እዚያው ሱዳን ውስጥ ተፈናቅለዋል።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የስደተኞች ተቋም ከዚህም በኋላ ከ800 ሺህ በላይ ሱዳናውያን ሊሰደዱ ይችላሉ በሚል እራሱን እያዘጋጀ ነው። እነሱንም ለቀጣይ አምስት ወራት ለመርዳት 450 ሚሊዮን ዶላር የሚጠጋ ገንዘብ እንደሚያስፈልገውም አሳውቋል።

በሱዳን ጦርነቱ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ ለሱዳን እንዲቀርብ የታቀደ 13 ሚሊዮን ዶላር የሚያወጣ የምግብ እርዳታ እንደተዘረፈበት የዓለም ምግብ ፕሮግራም ገምቷል።

ድርጅቱ እንዳለው ሱዳን ውስጥ በኃይል በመታገዝ የሚፈጸም ዝርፊያ ተስፋፍቷል።

የተባበሩት መንግሥታት የሕጻናት መርጃ ድርጅት ዩኒሴፍ፣ ታዳጊዎች በጦርነቱ መካከል ጉዳት እየደረሰባቸው እና በአገሪቱ ያለው ሁኔታ ቀስ በቀስ እልቂት ወደሚባል ደረጃ እያመራ ነው ብሏል።