May 7, 2023 – BBC Amharic 

የፎስፎረስ ኬሚካል የቦምብ ጥቃት

6 ግንቦት 2023

ሩሲያ በከበባ ውስጥ ባስገባቻት ባኽሙት ከተማ ላይ የፎስፎረስ ኬሚካል የቦምብ ጥቃት ፈጽማለች ስትል ዩክሬን ከሰሰች።

የዩክሬን ጦር በድሮን በተቀረጸ ቪዲዮ እንደለቀቀው የባኽሙት ከተማ ላይ ነጭ ፎስፎረስ የሚመስል ኬሚካል በከተማዋ ላይ ሲዘንብና ከፍተኛ ቃጠሎ አሳይቷል።

ነጭ ፎስፎረስን በጦርነት ላይ መጠቀም ባይከለከልም ሰላማዊ ነዋሪዎች በሚኖሩባቸው አካባቢዎች ላይ ጥቅም ማዋል እንደ የጦር ወንጀል ይቆጠራል።

ኬሚካሉ በከፍተኛ ሁኔታ የሚዛመት የእሳት ቃጠሎዎችን የሚፈጥር ሲሆን ለማጥፋትም በጣም አስቸጋሪ ነው። ሩሲያ ቀደም ሲል ፎስፎረስን በመጠቀም ተከሳለች።

ባኽሙት ያላት ስትራቴጂካዊ ጠቀሜታ ጥያቄ ውስጥ ቢገባም ሩሲያ ባኽሙትን ለመቆጣጠር ለወራት ያህል ስትሞክር ቆይታለች።

ምዕራባውያን ባለስልጣናት ግዛቲቷን ለመቆጣጠር በተካሄደው ጦርነት በሺዎች የሚቆጣጠሩ የሩሲያ ወታደሮች እንደሞቱ ግምታቸውን አስቀምጠዋል።

የዩክሬን መከላከያ ሚኒስቴር የፎስፎረስ ጥቃቱ “ሩሲያ ባልያዘቻቸው የባኽሙት አካባቢዎች ላይ ያነጣጠረ ነው” ሲልም በትዊተር ገጹ አስፍሯል።

የኪዬቭ ልዩ ኃይል ኮማንድ በበኩሉ የሩሲያ ኃይሎች “ከተማዋን ማፍረስ” ቀጥለዋል ብሏል።

የፎስፎረስ ጥቃት መቼ እንደተፈጸመ ግልጽ አይደለም። ነገር ግን በክትትል ድሮን የተቀረጸ የሚመስለውና በዩክሬን ጦር የተጋራው ቪዲዮ ከፍ ያሉ ሕንጻዎች በእሳት ተያይዘው አሳይቷል።

ሌሎች በማኅበራዊ ድረ ገጾች የተጋሩ ቪዲዮዎችም መሬት ላይ የእሳት ቃጠሎችን አሳይተዋል።

ሩሲያ ዩክሬንን ከወረረችበት ከባለፈው ዓመት ጀምሮ ነጭ ፎስፎረስ ተጠቅማለች የሚል ክስ ቀርቦባታል። በጦርነቱ መጀመሪያ ላይ የማሪፑልን ግዛት በከበበችበትም ወቅት በዚህ ተቀጣጣይ መሳሪያ ጥቃት ፈጽማለች ተብሏል።

ሩሲያ ይህንን ነጭ ፎስፎረስ ኬሚካል መጠቀሟን በይፋ አምና አታውቅም።ከዚህ ቀደም የክሬምሊን ፕሬስ ሴክሬታሪ ዲሚትሪ ፔስኮቭ “ሩሲያ ዓለም አቀፍ ስምምነቶችን ጥሳ አታውቅም” ሲሉ የተናገሩ ሲሆን ይህም የዩክሬኑ ፕሬዚዳንት ቮሎዲሚር ዘሌንስኪ ጥቅም ላይ ውሏል ላሉት የተሰጠ ምላሽ ነው።

ነጭ ፎስፎረስ ኬሚካል እንደ ሰም የሚመስል ንጥረ ነገር ሲሆን ከኦክስጅንም ጋር ሲገናኝ በከፍተኛ ሁኔታ የሚቀጣጠልና የከፋ ጉዳትም የሚያደርስ ነው።

የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ ድርጅት የፎስፎረስ ኬሚካል በሰው ልጅ ገላ ላይ የከፋ ቃጠሎ በማድረስ አስከፊ ጉዳትን የሚያስከትል ነው ሲል አስጠንቅቋል።