
ደብረታቦር ዩኒቨርሲቲ ከሃያ ሺሕ ጫማ ከፍታ በላይ መጓዝ የሚችል ሮኬት አስወነጨፈ
የደብረታቦር ዩኒቨርሲቲ ዘንድሮ ለኹለተኛ ጊዜ “አፄ ቴዎድሮስ 2015” የሚል ስያሜ የተሰጣትን ሮኬት ከሃያ ሺሕ ጫማ ከፍታ በላይ አስወንጭፎ ስኬታማ ሙከራ ማድረግ መቻሉ ተገልጿል፡፡
ዩኒቨርሲቲው በህዋ ምርምር ላይ ትኩረት በማድረግ ጋፋት የህዋ ምህንድስና ልማት ማዕከልንም አቋቁሞ የተለያዩ የምርምር ሥራዎችን በመስራት ላይ እንደሚገኝ ተነግሯል።
የማዕከሉ መሥራችና ሰብሳቢ በለጠ ጌታቸው፤ ሮኬት የማስወንጨፉ ሙከራ ከዚህ በፊት ከተሞከሩት የተሻለ ምርምር የተደረገበትና ለህዋ ሳይንስ የሚያስፈልጉ ቁሳቁሶችን ተሸክሞ መሄድ የሚያስችል ቴክኖሎጅ የተገጠመለት መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ኢትዮጵያ በህዋ ሳይንስ ዘርፍ ትኩረት ሰጥታ እየሠራች ነው ያሉት የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶክተር አነጋግረኝ ጋሻው፤ በዩኒቨርሲቲው ተማሪና ተመራማሪዎች የተሠራው ሥራ ኢትዮጵያ እንደሰለጠኑት አገራት በህዋ ምርምር የበኩሏን ድርሻ እንደምትይዝ ጅምሩን ያሳየ ነው ብለዋል።
በኢትዮጵያ ከሚካሄዱት የህዋ ሳይንስ ምርምሮች ውስጥ በሮኬት ሳይንስ ዘርፍ ደብረታቦር ዩኒቨርሲቲ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ መሆኑንም ገልጸዋል።
የአማራ ሳይንስ እና ቴክኖሎጅ ኮሚሽን ኮሚሽነር ሳሉ አያሌው (ዶ.ር) እንደዚህ አይነት ሙከራዎች ኢትዮጵያ ወደፊት በዘርፉ ለምታደርገው ምርምር አጋዥ ናቸው ማለታቸውን አሚኮ ዘግቧል።
__
አዲስ ማለዳ
