May 7, 2023 – BBC Amharic 

የሩሲያው ቅጥረኛ ተዋጊ ቡድን (ቫግነር) መሪ ከሰራዊቶታቸው ጋር

6 ግንቦት 2023

የሩሲያው ቅጥረኛ ተዋጊ ቡድን (ቫግነር) መሪ በጥይት እጥረት ምክንያት ወታደሮቻቸውን ከዩክሬኗ ባኽሙት ግዛት ሊያስወጡ እንደሆነ አስታወቁ።

የቡድኑ መሪ የቭጀኒ ፕሪጎዝሂን ሰራዊቶታቸውን ከቀናት በኋላ እንደሚያስወጡም ተናግረዋል።

የቅጥረኛው ተዋጊ መሪ ይህንን የተናገሩት በሞቱ ተዋጊዎቻች አስከሬን መካከል እየተመላለሱ የሚያሳይ ቪዲዮ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት ነው።

በዚህም መልዕክታቸው የሩሲያ መከላከያ ከፍተኛ ባለስልጣናትን ተጠያቂ አድርገዋል።

“በአስር ሺዎች ተገድለዋል እንዲሁም ቆስለዋል” ብለዋል የቅጥረኛ ተዋጊው መሪ።

ሩሲያ ስልታዊ ጠቀሜታ አላት ያለቻትን የዩክሬንን ምስራቃዊቷ ከተማን ባኽሙት ለመያዝ ለወራት ስትሞክር ቆይታለች።

በዚህም የሩሲያ ዘመቻ የቫግነር ሰራዊት ከፍተኛ ተሳትፎ አድርገዋል።

በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ የአሜሪካ ብሔራዊ ደኅንነት ምክር ቤት ቃለ አቀባይ ጆን ኪርቢ ከታኅሳስ ወር ጀምሮ በዩክሬን በተደረገው ጦርነት ከ20 ሺህ በላይ የሩሲያ ወታደሮች መገደላቸውን እንዲሁም 80 ሺህ መቁሰላቸውን አዲስ መረጃን ዋቢ አድርገው ተናግረዋል።

ከእነዚህም መካከል ግማሽ የሚሆኑት የቫግነር ተዋጊዎች መሆናቸውንም ጠቅሰዋል።

የ61 ዓመቱ የቫግነር መሪ ከባኽሙት ለመውጣት የወሰዱትን ውሳኔ ባሳወቁበት በግለጫቸው የሩስያ መከላከያ ሚኒስቴርን ዘልፈዋል።

“ሾይጉ! ገራሲሞቭ! ጥይቱ የት አለ? ወታደሮቼ በበጎ ፈቃደኝነት መጥተው ተዋግተው እናንተ በተንቆጠቆጠ ቢሮዎቻችሁ ውስጥ ሆናችሁ ራሳችሁን እንድታደልቡ ሞቱ!” ብለዋል።

የቡድኑ መሪ በተደጋጋሚ የሩሲያ የመከላከያ ሚኒስትር ሰርጌይ ሾይጉ እና የሰራዊቱ ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ቫለሪ ገራሲሞቭን ሲዘልፉና ሲወቅሱ ይሰማል።

ፕሪጎዝሂን በጥይት እጥረት የሚሞቱ የቫግነር ወታደሮች በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ ነው ብለዋል። ነገር ግን ተዋጊዎቻቸው ሩሲያ የሁለተኛ የዓለም ጦርነት የድል መታሰቢያን ዕለት እስከምታከብርበት ግንቦት 1 2015 ዓ.ም ድረስ በየቦታቸው እንደሚቆዩ እና በማግስቱም ከባኽሙት እንደሚወጡም ተናግረዋል።

ቀደም ሲል በተለቀቀው ቪዲዮ ላይ ፕሪጎዝሂን በሰራዊቱ ፊት ቆሞ የሚታይ ሲሆን “በባኽሙት ጦር ሰፈር ውስጥ ያሉ ቦታዎችንና ሎጂስቲኮችን ለሩሲያ መከላከያ ሚኒስቴር አስረክበን እንወጣለን። ሽንፈታችንን ተቀብለናል” ብለዋል።

“ሰራዊቴ በባኽሙት ያለ ጥይት ለማይጠቅምና ተገቢ ያልሆነ ኪሳራ አይዳረጉም” ሲሉም አክለዋል።

አርብ ዕለት በፕሪጎዝሂን ከተለቀቁት ቪዲዮዎች አንዱ የተቀረጸው ከባኽሙት በ2 ኪሎሜትር ርቀት ላይ ያለ ይመስላል።ቢቢሲ የአካባቢውን ቁጥቋጦዎች እና ሌሎች የመሬት ገጽታዎችን የሳተላይት ምስል በማጥናት ነው ስፍራውን መገመት የቻለው።