May 7, 2023 – BBC Amharic 

ፊቷን ያዞረች ሕጻን
የምስሉ መግለጫ,በእስር ቤቱ ውስጥ በርካታ ሕጻናት ከእናቶቻቸው ጋር ታስረዋል ተብሎ ይታመናል።

6 ግንቦት 2023

በኢራቅ ዋና መዲና ባግዳድ ከፍተኛ ቁጥጥር በሚደረግበት እስር ቤት ውስጥ የሚገኙ ቢያንስ 400 ሴቶች የረሃብ አድማ ከመቱ ሁለተኛ ሳምንት መያዛቸው ተነገረ።

ሴቶቹ ለእስር የተዳረጉት የእስላማዊ መንግሥት ቡድን አባል በመሆናቸው ሲሆን ከ15 ዓመት እስከ የሞት ፍርድ ተላልፎባቸዋል።

የረሃብ አድማውን የመቱትም የተላለፈባቸውን ‘ኢ ፍትሃዊ’ ፍርድ እንዲሁም የእስር ቤት አያያዛቸውን በመቃወም ነው።

በእስር ላይ ከሚገኙት ሴቶች መካከል የሩሲያ፣ ቱርክ፣ አዘርባጃን ፣ ዩክሬን ፣ ሶሪያ፣ ፈረንሳይ ፣ ጀርመን እና አሜሪካ ዜጎች ይገኙበታል።

በእስር ቤቱ 100 የሚሆኑ ሕጻናት እንደሚገኙም ይታመናል።

አይኤስ በሚል የሚታወቀው እስላማዊ መንግሥት ቡድን በሶሪያ እና ኢራቅ ዙሪያ ራስ ገዝ የሆነች እስላማዊ አገር ለመመስረት ጭካኔ የተሞላበት ዘመቻዎች በማካሄድ በአምስት ዓመታት ጊዜ ውስጥ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን በመግደል ሕዝቡ በባርነት እንዲገዛ አድርጓል።

ቡድኑ እንደ አውሮፓውያኑ 2017 ከወደቀ በኋላ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ የቀድሞ የቡድኑ አባላት ተለይተው የተሰባሰቡ ሲሆን፣ከእነዚህም ውስጥ በርካታ ወንዶች ያለ ፍርድ ተገድለዋል።

በሺዎች የሚቆጠሩ ሴቶች እና ሕጻናት ደግሞ ወደ እስር ቤት መወሰዳቸው ተነግሯል።የተወሰኑት ደግሞ ወደ አገራቸው እንዲመለሱ የተደረጉ ሲሆን ሌሎች በርካቶችም በሶሪያ እና በኢራቅ እስር ቤቶች ውስጥ ይገኛሉ።

ከባግዳድ እስር ቤት ለቢቢሲ የአረብኛው ክፍል የተላኩ ተንቀሳቃሽ ምስሎች፣በርካታ ሴቶች ያለምንም እንቅስቃሴ ደረቅ ወለል ላይ ተኝተው ያሳያሉ።እነዚህ ሴቶች ከአውሮፓውያኑ 24 ጀምሮ ምንም ምግብ አልቀመሱም ተብሏል።

የረሃብ አድማው ሲጀመር፣ ተሳታፊዎቹ በቀን ግማሽ ብርጭቆ ውሃ ይጠጡ የነበረ ሲሆን አሁን ላይ የተወሰኑት ሴቶች እርሱንም መጠጣት እንዳቆሙ ቢቢሲ መስማት ችሏል።

በተንቀሳቃሽ ምስሉ ላይ ሕጻናትም የሚታዩ ሲሆን በርካቶቹ የተወለዱት እዚያው እስር ቤት ውስጥ እንደሆነ ይታሰባል።

ሴት እስረኞቹ ከ15 ዓመት እስከ እድሜ ልክ እስር ተፈርዶባቸዋል።የተወሰኑትም የሞት ፍርድ የተላለፈባቸው ሲሆን እስካሁን ግን ፍርዱ እንዳልተፈፀመባቸው ቢቢሲ ማወቅ ችሏል።

ቢቢሲ በሕገ ወጥ መንገድ በእስር ቤት ውስጥ በተያዘ ስልክ ያነጋገራት አንዲት ሩሲያዊት ሴት ከእስር እስከምትለቀቅ ድረስ ምንም ነገር እንደማትቀምስ ተናግራለች።

ሩሲያዊቷ ሴት እንደምትለው በግዳጅ እንድትፈርም በተደረገችው የእምነት ክህደት ቃል መሠረት በ10 ደቂቃ ችሎት የ15 ዓመት እስር ተፈርዶባታል።

እንድትፈርም የተገደደችበት ሰነድም እርሷ መረዳት በማትችለው አረብኛ ቋንቋ የተጻፈ ሲሆን የጦር መሣሪያ ይዛ በሞሱል በቁጥጥር ሥር እንደዋለች ያስረዳል።እርሷ ግን ይህን አስተባብላለች።

ሴቶቹ ከኤምባሲዎቻቸው፣ ከዲፕሎማት ተወካዮች ጋር ምንም አይነት ግንኙነት እንዳልነበራቸው እና በፍርድ ሒደታቸውም ላይ እንዳልተገኙ ተናግረዋል።

ቢቢሲ ያነጋገራቸው ሴቶች ባለፉት ስድስት ዓመታት 60 የሚሆኑ አዋቂ እስረኞች እና 30 ሕጻናት በሩሳፋ እስር ቤት ውስጥ ሕይወታቸው ማለፉን ተናግረዋል።ለመጨረሻ ጊዜ የሞተው የሦስት ዓመት ሕጻን እንደሆነም አንዲት ሴት ተናግራለች።

እስር ቤቱ በምስራቅ ባግዳድ የሚገኝ ሲሆን ከተለያዩ ወንጀሎች ጋር በተያያዘ ፍርደኛ እስረኞችን ይዟል። እስረኞቹ እንደሚሉት በአንዲት ጠባብ ክፍል ውስጥ 40 የሚሆኑ ሰዎች የሚገኙ ሲሆን ብዙውን ጊዜም ድብደባ እና ኢሰብዓዊ ድርጊት ይፈፀምባቸዋል።

ባለፈው ሚያዝያ ወር የኢራቅ ፍትሕ ሚኒስቴር ‘ሾልኮ በወጣ ድምጽ’ ሳቢያ የእስር ቤቱ ዳይሬክተር መባረራቸውን ገልጾ ነበር።

ሚኒስቴሩ እስር ቤቱ መያዝ ከሚችለው አራት እጥፍ የሚሆኑ እስረኞች መያዙንም አምኗል።

የኢራቅ የወንጀል ፍትሕ ሥርዓት፣ ፍርዶች ፍትሃዊ እንዳልሆኑና በስፋት በደሎችን በመፈፀም ይተቻል።

የኢራቅ መንግሥት ስለ ረሃብ አድማው እና የእስረኞች አያያዝን በተመለከተ ከቢቢሲ ለቀረበለት ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት ፈቃደኛ አልሆነም።

ቀደም ብሎ ግን ጥፋተኛ ያልሆኑትን እስረኞች ወደ አገራቸው እንዲመለሱ መርዳት እንደሚፈልግ ገልጾ ነበር።

ዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋች ድርጅት አምነስቲ ኢንተርናሽናል፣ከአይኤስ ጋር በተያያዙ ጉዳዮች “በማሰቃየት ላይ የተመሰረተ የእምነት ክህደት ቃል ላይ ተመስርቶ” የረጅም ጊዜ እስር እና የሞት ፍርድ እንደሚተላለፍ ገልጿል።

የኢራቅ ምክር ቤት የሰብዓዊ መብቶች ኮሚቴ በቅርቡ ከአይኤስ ጋር ግንኙነት ያላቸው የውጭ አገር እስረኞችን ወደ አገራቸው የመመለስ ሒደትን እንዲያፋጥኑ ባለሥልጣናትን አሳስበዋል።

የተወሰኑት ሴቶች አይኤስን በፍላጎት መቀላቀላቸውንና ብዙ ጊዜ ወንጀል ውስጥ መሳተፋቸውን ያመኑ ሲሆን ሌሎች ደግሞ ተታለው ወይም ተገደው ቡድኑን እንደተቀላቀሉ ተናግረዋል።

አንዳንዶችም ተዋጊዎችን እንዲያገቡ መገደዳቸውን እና ጥያቄውን ካልተቀበሉ የግድያ ዛቻ እንደሚደርስባቸው ገልጸዋል።

ከእነዚህ መካከል እንደ አውሮፓውያኑ 2015 ወደ ሶሪያ ያመራችውና በእንግሊዝ ተማሪ የነበረችው ሻሚማ ቤገም አንዷ ናት። ሻሚማ እስካሁን በአገሪቷ ሰሜናዊ ክፍል በሚገኝ ካምፕ ውስጥ በእስር ላይ ትገኛለች።