” ብልፅግና ፓርቲ ለፈፀመውና እየፈፀመ ላለው ወንጀል ተጠያቂው ፓርቲው እራሱ ነው፤ በዚህ ምክንያት የኦሮሞን ህዝብ ስም ማጥፋት ትክክል አይደለም ” – የኦሮሞ ፌዴራላዊ ኮንግረስ
የኦሮሞ ፌዴራላዊ ኮንግረስ (ኦፌኮ) በ2014 ዓ/ም 2ኛ ጠቅላላ ጉባኤውን ካካሄደ በኃላ ባወጣው የአቋም መግለጫ ፤ ገዢውን ብልፅግና ፓርቲ እንደ ኦሮሞ መንግሥት በመቁጠር ፓርቲው የተሳሳተውን ስህተት እና ህገወጥ ተግባር የኦሮሞ ህዝብ ስህተት በማስመሰል የሚቀርቡ አቀራረቦች በህዝብ መካከል ቅራኔ የሚፈጥሩና እጅግ አደገኛ መዘዝ የሚያመጡ ናቸው አለ።
ኦፌኮ ” ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ገዥውን ፓርቲ እንደ ኦሮሞ መንግሥት በመቁጠርና የ ‘ ኦሮሙማ አገዛዝ ‘ የሚል የተሳሳተ ብያኔ በመስጠት አንዳንድ የአማራን ህዝብ እንወክላለን የሚሉ ኃይሎችና ምሁራን ይህ አካል የፈፀመውን ስህተት እና ህገ ወጥ ተግባራት የኦሮሞ ህዝብ ስህተት አስመስለው እያቀረቡ ነው ” ሲል ገልጿል።
” ይህ በህዝቦች መካከል ቅራኔ የሚፈጥርና ከባድ መዝዝ ሊያስከትል የሚችል ስህተት የሆነ አስተሳሰብ ነው ” ያለው ኦፌኮ ፤ ” ብልፅግና ፓርቲ ለፈጸመውና እየፈጸመ ላለው ወንጀል ተጠያቂው ፓርቲው ራሱ ሲሆን በዚህ ምክንያት የኦሮሞ ህዝብ ስም ማጥፋት ትክክል ስላልሆነ እንደዚህ አይነት የጥላቻ ፕሮፓጋንዳ በአስቸኳይ እንዲቆም እንጠይቃለን ” ብሏል።
ኦፌኮ የኦሮሞ ህዝብን በሚመለከቱ ፖለቲካ ጉዳዮች ላይ፤ “ቀሪ የኦሮሞ የፖለቲካ ኃይሎች ያሳተፈ ድርድር መደረግ” አለበት አለ
የኦሮሞ ፌደራላዊ ኮንግረስ (ኦፌኮ) በመንግስት እና በ“ኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት” መካከል የሚደረገው የሰላም ድርድር ከተኩስ አቁም ስምምነት ባለፈ የኦሮሞ ህዝብን በሚመለከቱ ፖለቲካ ጉዳዮች ላይ ቀሪ የኦሮሞ የፖለቲካ ኃይሎችን ማሳተፍ እንዳለበት አሳሰበ። ኦፌኮ እውነተኛ እና ቀጣይነት ላለው ዕርቅ እና መግባባት ሁሉንም የፖለቲካ አመራርና ድርጅቶች ያሳተፈ “የአስተዳደር ስርዓት” መዘርጋት እንዳለበትም በአጽንኦት ገልጿል።
ተቃዋሚ ፓርቲው ይህን የገለጸው፤ የኦፌኮ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት ለሁለት ቀናት ሲያካሄዱት የቆዩትን መደበኛ ስብሰባ ካጠናቀቁ በኋላ ዛሬ ቅዳሜ ሚያዝያ 28፤ 2015 በዋና ጽህፈት ቤቱ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ነው። ዛሬን ጨምሮ ለሁለት ቀናት የተካሄደው የፓርቲው ማዕከላዊ ኮሚቴ ስብሰባ የተጠናቀቀው፤ ሰባት የአቋም መግለጫዎችን በማውጣት መሆኑ ተገልጿል።
ከሰባቱ የአቋም መግለጫዎች ሁለቱ ያተኮሩት መንግስት ከተለያዩ አማጺ ቡድኖች ጋር ሲያደርጋቸው በቆዩ የሰላም ድርድሮች ላይ ነው። የኦፌኮ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ሱልጣን ቃሲም በንባብ ባሰሙት መግለጫ፤ “የኢትዮጵያ መንግስት በትግራይ፣ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ ጋምቤላ እና ኦሮሚያን ጨምሮ በመላ ሀገሪቱ በአጠቃላይ እየሞከረ ያለውን እርቅ እና ድርድር” ፓርቲው “በመርህ ደረጃ” እንደሚደግፍ ያትታል፡፡
ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና ስለ ሰሞኑ የሰላም ውይይት ምን አሉ?
– ኦፌኮ የሰላም ድርድሩ ውጤታማነት ላይ ያለውን ተስፋ በተመለከተ ከ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ጥያቄ የቀረበላቸው የፓርቲው ሊቀመንበር ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና፤ “ከአሁኑ አፍ ሞልቶ መናገር አይቻልም” ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል። ከስድስት ወራት በፊት በፌደራል መንግስት እና በህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) መካከል በተደረገው ስምምነት በአደራዳሪነት ተሳታፊ የነበሩት አካላት ይታወቁ እንደነበር ያስታወሱት የፓርቲው ሊቀመንበር፤ “እዚህኛው ላይ በስሚ ስሚ ካልሆነ አይታወቁም” ሲሉ የሰላም ውይይቱ ዝርዝር መረጃ አሁንም ግልጽ አለመሆኑን አስረድተዋል።
– “ኢትዮጵያን ከመገዳደል ፖለቲካ እንድትሻገር የሚሞክሩ፣ የሚገፉ፣ የሚያደራድሩ፤ ጉልበትም፣ እውቀትም ያላቸው ይኑሩ አይኑሩ እርግጠኛ አይደለንም” ሲሉ በታንዛኒያው ድርድር ተሳታፊ ስለነበሩ ወገኖች ያላቸው መረጃ ውሱን መሆኑን ፕሮፌሰር መረራ ተናግረዋል። የኦፌኮ ሊቀመንበር አክለውም “ግፊት ማድረግ የሚችሉ አደራዳሪዎች፤ ከድርድሩም በኋላ ስምምነቱ ስራ ላይ መዋሉን መቆጣጠር የሚችሉ ኃይሎች ያስፈልጋሉ” ሲሉም የሰላም ውይይቱ ውጤታማ ከሆነ በኋላ ሊደረግ የሚገባውን ጠቁመዋል።
– ሁለቱም ወገኖች ወደ ድርድሩ ሲመጡ “የራሳቸው ስሌት” ይዘው እንደሆነ ያመለከቱት ፕሮፌሰር መረራ፤ በኢትዮጵያ መንግስት እና በ“ኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት” ተወካዮች በኩል ሊነሱ የሚችሉ የድርድር ነጥቦች ምን ሊሆኑ እንደሚችሉ ግምታቸውን አስቀምጠዋል። “ስልጣን ላይ ያለው መንግስት ታንዛኒያ የሄደው ‘እጃችሁን ስጡ፣ መሳሪያ አስቀምጡ፣ ምህረት እናደርጋለን፣ ከሶስት ዓመት በኋላ ደግሞ ምርጫ ይመጣል፣ ያን ጊዜ እድላችሁን ትሞክራላቸሁ’ [ብሎ] ለማባበል ይሆናል። እነዚያ ደግሞ ‘ጠመንጃ አስቀምጠን፣ ምን ዋስትና አለን? ማን ነው ዋስትና የሚሰጠን?’ የሚል ጭንቀት ያላቸው ይመስለናል” ሲሉ ስለ ድርድሩ ያላቸውን ግምገማ ለጋዜጠኞች አጋርተዋል።
– “እንደ ሰሜኑ ድርድር ’በሁለቱ ተደራዳሪዎች መተማመን እንዲፈጠር የሚያደርግ፣ ይሄንን የሚያጠብ ሶስተኛ ወገን ያስፈልጋል’ የሚባለው ለዚህ ነው። ፕሪቶሪያ እና ናይሮቢያ ላይ እነማን ተሳታፊ እንደነበሩ፣ አገናኝ እነደነበሩ፣ አስማሚ እንደነበሩ ይታወቃሉ። አሜሪካንን የሚህል ትልቅ ጭንቅላት ከኋላ አለ። ሶስተኛ ወገን የሚባለው [የኦሮሞ ነጻነት ጦር] ሲጠይቀው የነበረው ጉዳይ ነው” ሲሉ አብራርተዋል።
– ኦፌኮ በዛሬው መግለጫው እንዲዘረጋ የጠየቀው “የአስተዳደር ስርዓት” ምንነትን በተመለከተ ከ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ጥያቄ የቀረበላቸው ፕ/ር መረራ፤ ስርዓቱ “ሁሉንም የሚያሳትፍ” መሆን አለበት ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል። “በተለይ የአሁኑ መንግስት የሽግግር መንግስት የሚለውን ለምን እንደሚጠላው አላውቅም፤ ይሸሻል። የሽግግር መንግስቱን እንተወውና ‘ሁሉን አሳታፊ መንግስት’፣ ‘ሁሉን አቀፍ የፖለቲካ ስርዓት’፣ ‘ብሔራዊ የአንድነት መንግስት’ በፈለጉት ስም ይጥሩት ግን ሁሉንም የሚያሳትፍ ስርዓት ያስፈልጋል” ሲሉ አስረድተዋል።
