
7 ግንቦት 2023, 08:05 EAT
ሕንድ ውስጥ በምትገኘው የማኒፑር ግዛት በጎሳዎች መካከል በተከሰተ ግጭት ምክንያት ቢያን 30 ሰዎች መገደላቸውን ባለሥልጣናት አስታወቁ።
በግዛቲቱ ለሚገኝ አንድ ዋነኛ ማኅበረሰብ የአካባቢው ጎሳ ተደርጎ በመንግሥት እውቅና ለመስጠት መታሰቡን ተከትሎ ነው ቀደምት ነዋሪዎች በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ አንስቶ ለተቃውሞ በመውጣታቸው ግጭት ተቀስቅሷል።
በግጭቱ በቡድን የተሰባሰቡ ግለሰቦች መኖሪያ ቤቶችን፣ ተሽከርካሪዎችን፣ አብያተ ክርስቲያናትን እና ቤተ መቅደሶችን አጥቅተዋል።
በዚህም ሳቢያ በርካታ ሰዎች የተገደሉ ሲሆን አንዳንድ ከአካባቢው የወጡ ዘገባዎች የሞቱ ሰዎችን ቁጥር አስከ 54 እንደሚደርስ እያመለከቱ ነው።
በግጭቱ ሳቢያ 10,000 የሚጠጉ ሰዎች ከቤታቸው መፈናቀላቸውም ተዘግቧል። የሕንድ መንግሥት ሥርዓት እንዲያስከብሩ ወደ ግዛቲቱ በሺዎች የሚቆጠሩ ወታደሮችን አሰማርቷል።
- የሕንድ ግዛት ጠጪ እና ከልክ በላይ ውፍረት ያላቸውን ፖሊሶች ከሥራ ልታሰናብት ነው2 ግንቦት 2023
- ሕንድ ውስጥ በመርዘኛ ጋዝ ምክንያት ቢያንስ 11 ሰዎች ሞቱ1 ግንቦት 2023
- በ2 ሰዓት ውስጥ 14 ሚሊዮን ዶላር ከባንክ የዘረፉት የሰሜን ኮሪያ ጠላፊዎች4 ሚያዚያ 2023
ሕንድ ከምያንማር ጋር በምትዋሰንባት የሰሜን ምሥራቅ ግዛቷ በሆነችው በዚህች ማኒፑር በተባለችው ግዛት ውስጥ በግጭቱ ምክንያት በበርካታ አካባቢዎቿ የሰዓት እላፊ ገደብ የተጣለ ሲሆን፣ የኢንተርኔት አገልግሎትም ተቋርጧል።
ከሌሎች የሕንድ ግዛቶች ለትምህርት ወደ ማኒፑር የመጡ ተማሪዎችም ግዛቲቱን ለቀው እየወጡ ነው።
በግዛቲቱ የተሰማራው የሕንድ ጦር ሠራዊት የተከሰተውን ችግር በቁጥጥር ስር እያዋለው መሆኑን የገለጸ ሲሆን፣ ግዛቲቱን የሚያስተዳድረው ቢጄፒ የተባለው የሒንዱ ብሔረተኛ ፓርቲ ግጭቱን ለመከላከል አስፈላጊውን ነገር አላደረገም በሚል እየተከሰሰ ነው።
ከማኒፑር ግዛት ነዋሪዎች 50 በመቶውን ሕዝብ የሚሸፍኑት ‘ሚቲ’ የተባሉት ማኅበረሰቦች፣ በጎሳነት ተቆጥረው የሚገባቸውን ጥቅም ለማግኘት ሲጠይቁ ዓመታት ተቆጥረዋል።
በሕንድ በጎሳዎች ላይ በታሪክ ውስጥ ተፈጽመዋል የሚባሉ በደሎችን ለማስተካከል ለሁሉም ተመጣጣኝ ዕድል ለመስጠት ሥራ፣ የኮሌጅ ትምህርት እና የምርጫ ወንበሮች የሚደለደሉት ማኅበረሰቦች በጎሳነት ካገኙት እውቅና አንጻር ነው።
እነዚህ ሚቲ የተባሉት ማኒፑር ግዛት ውስጥ የሚገኙት ብዙሃን ማኅበረሰቦች በጎሳነት እውቅናውን ማግኘት ከቻሉ ለአባሎቻቸው የደን መሬት፣ ተመጣጣኝ የመንግሥት የሥራ ዕድል እንዲሁም በትምህርት ተቋማት ውስጥ የመግባት ከቁጥራቸው ጋር የሚመጣጠን ዕድልን ይፈጥርላቸዋል።
ነገር ግን ሚቲዎች ዕውቅናን ካገኙ ሌሎች ቀደም ጎሳዎች የቅድመ አያቶቻቸው መኖሪያ የነበሩ የደን ይዞታዎችን እናጣለን ብለው በመስጋታቸው ነው ተቃውሞ እና ግጭቱ የተቀሰቀሰው።
ባለፈው ማክሰኞ የማኒፑር የቀድሞ ጎሳዎች ተማሪዎች ማኅበር የሚቲዎችን ጎሳ የመሆን ጥያቄን በመቃወም በጠራው ሰልፍ ላይ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች አደባባይ ወጥተው ነበር።
በተከታይ ቀንም ተመሳሳይ ሰልፍ ተደርጎ ግጭት በመፈጠሩ በግዛቲቱ ውስጥ ረብሻ ተዛምቶ ለቀናት በመቆየቱ ቢያንስ 30 ሰዎች መገደላቸው ተገልጿል።
