
7 ግንቦት 2023, 07:57 EAT
አባ ሚጌል ፓንታሌዮን የቅስና ማዕረግ የተቀበሉባትን ቀን እንደገና እንደተወለዱባት ቀን አድርገው ይመለከቷታል።
ባለፈው ወር ነበር በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ካህን ሆነው የተቀቡት።
የ28 ዓመት እድሜ ያላቸው አባ ሚጌል ለአስር ዓመታት ያህል ይህችን ቀን ሲጠባበቁ፣ እንዲሁም በመንፈሳዊ አገልግሎታቸውም ሲተጉ ነበር።
በምዕራብ ሜክሲኮ በምትገኘው አቧራማ መንደራቸው፣ ሪንኮን ዴል ካርመን በነበረ የቅዳሴ ሥነ ሥርዓት ላይ ነው የተሾሙት።
በሥነ ሥርዓቱ ላይ በርካታ የአካባቢው ነዋሪዎች የተሳተፉበት ሲሆን፣ የአካባቢው ጳጳስም ናቸው የቅስና ሹመቱን የሰጧቸው።
እናታቸው ፔትና ፍሎሬንሲዮ ከፊት ለፊት ባለው ወንበር ተቀምጠው ፊታቸው በኩራት እና በፈገግታ ደምቋል። ሚጌል ከ13 ልጆቻቸው 11ኛው ልጅ ሲሆን በቤተ ክርስቲያንም ያላቸው አገልግሎት ለቤቱ ትልቅ ክብር ነው።
ሆኖም ከዚህ ክብርም ጋር እናታቸው ፔትራ ስጋት ቢያደርባቸው የሚገርም አይደለም። ለዚህም ምክንያቱ አባ ሚጌል በዓለም ላይ ካህን መሆን አደገኛ በሆነበት ስፍራ በመገኘታቸው ነው።
ከአውሮፓውያኑ 2006 ጀምሮ በሜክሲኮ ከ50 በላይ ካህናት የተገደሉ ሲሆን፣ ከእነዚህም ውስጥ ዘጠኙ አገሪቷን እየመራት ባለው በአሁኑ አስተዳደር ወቅት ነው የተገደሉት።
አንዳንዶቹ የአደንዛዥ ዕጽ ነጋዴዎች እና ቡድኖችን ጥቃት ተቃውመው በመናገራቸው፣ ሌሎቹ ደግሞ በተቃናቃኝ የወንጀለኛ ቡድኖች የማያባራ ግጭት መካከል ውስጥ በመገኘታቸው ነው የተገደሉት።
ሁሉም ማለት በሚቻልበት ሁኔታ ለተፈጸሙ ግድያዎች ተጠያቂ የሆነ ወገን የለም። አብዛኛዎቹ ግድያዎችም እንዲሁ ተድበስብሰው ቀርተዋል።
- በመስቀል ላይ የሚፈጸም ስቅላት እንዴት እና የት ተጀመረ?14 ሚያዚያ 2023
- ቀሳውስት እና ጳጳሳት ለመሆን እየታገሉ ያሉት ሴቶች18 ታህሳስ 2022
- ስለኢትዮጵያ የቤተ ክርስቲያን ስዕሎች ምን ያህል ያውቃሉ?28 ህዳር 2017

አብዛኛዎቹ ግድያዎች የተፈጸሙት በምዕራባዊው የሚክሲኮ ክፍል ቲዬራ ካሊየንቴ ግዛት ነው።
ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የጃሊስኮ አዲሱ ትውልድ የአደንዛዥ ዕጽ ነጋዴዎች ቡድን እና ፋሚሊዮ ሚቸቾአካና የተሰኘው ሌላ ቡድን ግዛቲቷን ለመቆጣጠር ሲዋጉ ነበር።
“ለእኔ በቴዬራ ካሊየንቴ ግዛት ካህን መሆኔ ጥልቅ ፍቅርን ያሳያል” ሲሉ አባ ሚጌል ለቢቢሲ ተናግረዋል።
“በዚህ አካባቢ ወንጀለኞች ተብለው የተፈረጁ በብዙ ስቃይ፣ ጉዳት እና ህመም ውስጥ የሚኖሩ ሰዎች ናቸው። ስለዚህ ለአምላክ ጥሪ ምላሽ ስንሰጥ የፍቅሩም ምልክት ነው” ብለዋል።
አባ ሚጌል የቲየራ ካሊየንቴ ማዕከል በሆነችው እና ከሲውዳር አልታሚራኖ ከተማ ወጣ ባለች ስፍራ ነው የመንፈሳዊ ትምህርታቸውን የተከታተሉት።
በየማለዳውም 18 ሰልጣኝ ካህናት ለጠዋት ቅዳሴ ይሰባሰባሉ፤ ይጸልያሉ። ቀሳውስት ከሆኑ በኋላም ሊያጋጥሟቸው የሚችሉ አደጋዎችን እያሰላሰሉ በዚህ ትምህርት ቤት ያስተምሩ የነበሩ እና የተገደሉ ቄስ መቃብርንም አየት አድርገው ያልፋሉ።
በቀላል እምነበረድ በተሰራው መቃብር ላይም “ቄስ ሃባኩክ ሄርናንዴዝ ቤኒቴዝ፣ ጥር 16 ቀን 1970 – ሰኔ 13 ቀን 2009” የሚል ጽሁፍ በብረት ላይ ሰፍሯል።
ፓድሬ ኩኮ በመባል የሚታወቁት አባ ሃባኩክ በአካባቢው እንደ ሰማዕት ነው የሚታዩት። በሜክሲኮ ውስጥ የተገደሉ ቀሳውስት እና ዲያቆናትም እንደ ሰማዕት ነው የሚቆጠሩት።
“ፓድሬ ኩኮ የተገደሉበት ዓመት በግዛቲቷ ያለው ሁከት ከቁጥጥር ውጪ መውጣቱን ያሳየ ነበር” ሲሉ ጓደኛቸው አባ ማርሴሊኖ ትሩጂሎ ይናገራሉ።
“ከዚያ በፊት የነበሩት የአደንዛዥ ዕፅ ነጋዴዎች አካሄዳቸው ምስጢራዊ ነበር። በተወሰነ መልኩ ትንሽም ቢሆን መቆጣጠር ይቻል ነበር” ይላሉ።
አባ ፓድሬ ኩኮ ከተገደሉ አስር ዓመት ቢያልፋቸውም ክስተቱ አስካሁን አስደንጋጭ ነው።
የ39 ዓመቱ ፓድሬ ኩኮ ከሁለት ተማሪዎቻቸው ጋር ወደ አንድ የወጣቶች ዝግጅት እያቀኑ ነበር። ታጣቂዎቹ መኪናቸውን ከበው ተሳፋሪዎቹን እንዲወርዱ አስገደዷቸው። ምንም ቃል ሳይተነፍሱ በመንገድ ዳር ቄሱን ደፏቸው። ከኋላቸውም በርካታ ጊዜ ተኩሰውባቸዋል።
ለግድያው ምክንያት ምን እንደሆነ የተባለ ነገር የለም።
አባ ሜርሲሊኖ በዚያን ወቅት ከተገደሉት ጓደኛቸው አባ ፓድሬ ጋር አብረው መሄድ ነበረባቸው። ነገር ግን በመጨረሻው ሰዓት ሌላ ነገር በማጋጠሙ ትምህርት ቤት ውስጥ ቆዩ። ይህች አጋጣሚም ሕይወታቸውን አተረፈችላቸው።
ይህ ትምህርት ቤት በአደንዛዥ ዕጽ ነጋዴዎች ሁከት መሪር ሐዘን ያጋጠመበት የአባ ፓድሬ ግድያ ብቻ አልነበረም።

በአውሮፓውያኑ 2014 የገና ዕለት የአባ ፓድሬ ኩኮ የአጎት ልጅ የሆኑት አባ ግሪጎሪዮ ተመሳሳይ ዕጣ ፈንታ ገጠማቸው። የወሮበሎቹ ቡድን በድፍረት ትምህርት ቤቱ ውስጥ ገብቶ ጥቃት ፈጸመ። አባ ግሪጎሪዮንም ወደ አንድ ክፍል ወስደው ጥፍር አድርገው በማሰር አፋቸውን በፕላስተር አሸጉት።
“ታፍነው ነው የሞቱት” ሲሉ አባ ሜርሲሊኖ ያስረዳሉ።
“እንደተረዳነው መጀመሪያ አስረዋቸው እና አፍነዋቸው የነበረው ማስለቀቂያ ገንዘብ ሊጠይቁባቸው አቅደው ነበር። ነገር ግን እንደሞቱ ሲያውቁ በአቅራቢያው በሚገኝ ቆሻሻ ቦታ ትተዋቸው ሄዱ” ይላሉ።
እንደነዚህ ያሉ ታሪኮች ማንኛውም የአካባቢው ወጣቶች ምንም ያህል ሃይማኖተኛ ቢሆኑም በሲዳድ አልታሚራኖ ቀሳውስት እንዳይሆኑ ሊያግዷቸው ይችላሉ ብለን ልናስብ እንችላለን።
ነገር ግን በሃይማኖት ትምህርት ቤቱ ውስጥ ያሉት ተማሪዎች የተገደሉት ካህናት እንደሚያነሷሷቸው እና ማስፈራሪያ እንዳልሆኑ ነው የሚናገሩት።
“ለእኛ መልካም አርዓያ ሆነውልናል። በእንዲህ ባለ ኢ-ፍትሃዊ መንገድ ሲሞቱ የጀግንነት ምሳሌም ሆነውልናል” ሲል የ19 ዓመቱ አንቶኒዮ አቤሌዝ ተናግሯል።
የሃይማኖት ትምህርት ቤቱ ኃላፊ አንቶኒዮ ሬይኖሶ ወጣቶቹ ተማሪዎች በጥንቃቄ ሁኔታዎችን እንዲመረምሩ ያስተምሯቸዋል።
ወንጌልን ከመስበክ ራሳቸውን እንዲገድቡ እንዲሁም ወንጀለኛ ቡድኖች እና የአደንዛዥ ዕጽ ወንበዴዎችን ከማውገዝ እና ከመውቀስም እንዲቆጠቡም እንደሚያስተምሯቸው ኃላፊው ያስረዳሉ።
“የተደራጀ ወንጀል ሺህ ጭንቅላት እንዳለው አውሬ ነው” የሚሉት ኃላፊው “ሁከቶቹን ራሳቸው መፍታት አይችሉም፤ ነገር ግን በእምነት የአውሬውን ጭንቅላት ሊያገኙት ይችላሉ” ብለዋል።
ሆኖም ተማሪዎቹ አንዳንድ ጊዜ ቤተ ክርስቲያንን ለማገልገል ያሳለፉትን ውሳኔ መጠየቃቸው አልቀረም።
“የምንኖረው በአመጽ እና በሞት በተከበበ ሁኔታ ነው” የሚለው በ20ዎቹ መጀመሪያ ላይ የሚገኘው ተማሪ ጊለርሞ ካኖ ነው።
“በርካቶች ካለፉበት ሁኔታ አንጻር ተመሳሳይ ዕጣ ፈንታ ሊገጥመን ይችላል ብለን ስናስብ ያስፈራናል” ይላል።

ወደ ሪንኮን ዴል ካርመን ስንመለስ አዲሱን ካህን አባ ሚጌል ፓንታሌዮን የቅስና ሹመት ሥነ ሥርዓትን አብዛኛው የመንደሩ ነዋሪ ወጥቶ ነበር ያከበረው።
አባ ሚጌል ከቤተክርስቲያኑ ሲወጡ ሕዝቡም በጎዳናው ላይ በሰልፍ፣ በመዝሙር፣ በርችት እና በፈንጠዝያ ተከተሏቸው።
አባ ሚጌል ክህነታቸውንም ከቤተሰባቸው እና ከጓደኞቻቸው ጋር እያከበሩም፣ ወደፊት ለሚጠብቃቸው ማንኛውም ነገር ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል።
“አንድ ቀን ከአደንዛዥ ዕጽ ነጋዴዎች እና ቡድኖች ጋር እንደምገናኝ አውቃለሁ። ነገር ግን ከእነርሱ ጋር ለመፋጠጥ ሳይሆን፣ ይልቁንም የአምላክን የምህረት ፊት ላሳያቸው እፈልጋለሁ። ምክንያቱም አምላክ ለእነሱም ጭምር የቆመ ነው” ብለዋል።
