
ከ 5 ሰአት በፊት
በኑሮ ውድነት ምክንያት የተጀመረው የሱዳን ሕዝባዊ እንቅስቃሴ ለሦስት አስርት ዓመታት ለሚጠጋ ጊዜ አገሪቱን አንቀጥቀው የገዙትን ኦማር ሐሰን አልበሽርን ከሥልጣን ያስወገደው በአውሮፓውያኑ በ2019 ነበር።
ይህንንም ተከትሎ አገሪቱ ወደ ዲሞክራሲያዊ አስተዳደር እስክትሸጋገር ድረስ በሲቪል ፖለቲከኞች እና በወታደራዊ መሪዎች መካከል የሥልጣን ክፍፍል ስምምነት ተደረገ።
በዚህ ሂደት ውስጥም በሺህዎች የሚቆጠሩ ሱዳናውያን በሕይወት ዋጋ ከፍለዋል። ይህ ግን አገሪቱን ወደ ጠበቀችው ዴሞክራሲ ሱዳናውያንንም ከኑሮ ውድነት አልታደገም።
የኋላ ኋላም በጄኔራል አብደል ፋታህ አል ቡርሐን የሚመራው ወታደራዊው ኃይል “የእርስ በእርስ ጦርነትን” ለመከላከል በሚል ምክንያት በመፈንቅለ መንግሥት አድርጎ ከሲቪሉ ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሐመዶክ ሥልጣኑን ተጠቀ።
አል ቡርሐን ሱዳንን ወደ ሲቪል አስተዳደር ለማሸጋገር ቁርጠኛ መሆናቸውን ገልጹ። ባለንበት የአውሮፓውያን ዓመት እንደታቀደም ተናግረው ነበር።
ነገር ግን በወታደሩ ላይ እምነት ያልበራቸው አፍቃሪ ዲሞክራሲ ፖለቲከኞች በተቃውሟቸው ገፍተው ቆይተዋል። ወታደራዊ መንግሥቱን በመቃወም ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን በመጠየቅ ወደ አደባባይ በመውጣት ድምጻቸውን ሲያሰሙ ቆይተዋል።
ሰልፍ ይወጣሉ። የሞተው ሞቶ የተጎዳው ተጎድቶ ለሌላ ተቃውሞ ቀጠሮ ይዘው ይለያያሉ። ይህም ለወራት የማያቋርጥ ዑደት ሆኖ ቀጠለ።
ወታደሮቹ ካካሄዱት መፈንቅለ መንግሥቱ ማግስት ጀምሮ ሱዳን በሽግግር ሉዓላዊ ምክር ቤት አማካይነት በሁለት የጦር ጄነራሎች የበላይነት ስትመራ ቆይታለች።
የአገሪቱ ጦር አዛዥ ጄኔራል አብደል ፈታህ አል-ቡርሐን የሉዓላዊ ምክር ቤቱ ዋነኛ ሰው ሲሆኑ፣ የፈጥኖ ደራሹ ልዩ ኃይል አዛዥ ጄኔራል መሐመድ ሐምዳን ዳጋሎ (ሄሜቲ) ደግሞ ምክትል ሆነው ቆይተዋል።
ተቃውሞው በቀጠለበት እና ሥልጣን ወደ ሲቪል አስተዳደር የሚሸጋገርበት ጊዜ በተቃረበበት ጊዜ በጄኔራሎቹ መካከል መቃቃሮች እየተስተዋሉ ነበር።
የሱዳን ብሔራዊ የሽግግር ሉዓላዊ ምክር ቤት ምክትል ፕሬዝዳንት ጄኔራል ሐምዳን ዳጋሎ፣ በጄኔራል ቡርሐን መሪነት የተካሄደው ወታደራዊውን መፈንቅለ መንግሥት “ስህተት” ነበረ በማለት ለመፈንቅለ መንግሥቱ ድጋፍ ማድረጋቸውን ከፈጸሟቸው ስህተቶች መካከል አንዱ መሆኑን በመግለጽ መጸጸታቸውን ተናገሩ።
ቴሌቭዥን ላይቀርበው በሰነዘሩት ሃሳብም መፈንቅለ መንግሥቱ ለውጥ ከማምጣት ይልቅ ለቀድሞው የአልበሽር ሥርዓት አስተዳደር “ርዝራዦች ከተጠያቂነት ማምለጫ” ሆኗልም አሉ።
የአሁኑ ግጭት መነሻም ሁለቱ ጄነራሎች አለመግባባት ነው። ጄነራሎቹ ስልጣኑን ለሲቪል አስተዳደር ለማስተላለፍ ቃል ገብተው፣ የጄኔራል ዳጋሎ ፈጥኖ ደረሽ ኃይል አባላትም ወደ አገሪቱ ጦር እንዲቀላቀለረም ተስማምተው ነበር።
ሄምቲ የሚመሩት 100ሺህ አባላት ያሉት ልዩ ኃይል የአገሪቱን ጦሩን መቼ ይቀላቀላል፤ ጥምር ጦሩንስ ከዚያ በኋላ ማን ይመራዋል በሚለው ቁልፍ ጉዳይ ላይ ግን ሁለቱ ጄኔራሎች አልተግባቡም።
የጦር ጄነራሎቹ ልዩነቶቻቸውን በንግግር ይፈታሉ ተብሎ ለቀናት ከዚያም ለሳምንታት ቢጠብቁም፣ ያ ሳይሆን ቀርቶ ጊዜውን ሠራዊታቸውን ማዘጋጃ እና ማሰማሪያ በማድረግ ወደ ግጭት አመሩ።
ሁለቱ የጦር ጄኔራሎች በሱዳን ብቻ ሳይሆን ከጀርባቸው ሆነው የሚደግፏቸው እና የሚቃወሟቸው ኃይሎች እና አገራት እንዳሉ ይነገራል።
ከእነዚህም መካከል በዙሪያቸው ያሉ ጎረቤት አገራት፣ ባሕር ተሻግረው የሚገኙ አረብ መንግሥታት እንዲሁም የዓለም ኃያላን ሳይቀሩ ከአንደኛው ወይም ከሌላኛው ወገን እንደቆሙ ሲገምት እና ሲተነተን ቆይቷል።
- ተቀናቃኞቹ የሱዳን ጄኔራሎች ውጊያውን ለማቆም ፍላጎት የላቸውም ተባለ5 ግንቦት 2023
- ከሱዳን በመሸሽ ወደ መተማ የገቡ የተለያዩ አገራት ዜጎች ቁጥር ከ12 ሺህ በላይ ደረሰ7 ግንቦት 2023
- በሱዳን ግጭት ውስጥ የአካባቢው ዋነኛ አረብ አገራት ሚና ምንድን ነው?29 ሚያዚያ 2023

ኢትዮጵያ እና ኤርትራ ከማን ወገን ናቸው?
የምሥራቅ አፍሪካ ፖለቲካን በቅርበት የሚከታተለው ጋዜጠኛ መሐመድ አቡበከር በተለያዩ መገናኛ ብዙኃን ውስጥ ሰርቷል። የፖለቲካ ሳይንስ ያጠናው መሐመድ የመመቂያ ጽሑፉም የአሜሪካ ስትራቴጂክ ፖሊሲ በአፍሪካ ቀንድ የሚል ነበር።
ኤርትራ ከሩሲያ ጋር ካላት ወዳጅነት እና ጄኔራል ሞሐመድ ሐምዳን ዳጋሎ በቅርቡ ወደ አሥመራ ከመጓዛቸው አንጻር ፕሬዝዳንት ኢሳያስ በሄሜቲ የሚመራውን የፈጥኖ ደራሽ ኃይል ይደግፋሉ ተብሎ ይታመናል። እሱ ግን በዚህ አይስማማም።
በቅርቡ በኤርትራ ቴሌቭዥን ቀርበው ቃለ ምልልስ የሰጡት ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ‘ፖለቲካዊ ትንታኔ’ በሚመስልው ቆይታቸው “ዕውቅና እና ድጋፍ የሚሰጡት ለጀኔራል አልቡርሃን ይመስላል። ይሄ ብዙ ሰው ከሚያስበው በተቃራኒ ነው” ይላል።
ለዚህ የሚያቀርበው ምክንያት ፕሬዝዳንቱ እንደ ኢጋድ ባሉ ቀጠናዊ ተቋማት ችግሩ ሊፈታ እንደሚችል መናገራቸውን ነው። የአሜሪካን ስም አለማንሳታቸውን ብቻ ሳይሆን፣ የያዙት አቋም ከዋሽንግተን ጋር ተመሳሳይ መሆኑንም ይጠቅሳል።
በዚህ ቃለ ምልልስ ፕሬዝዳንቱ ጣታቸውን የቀሰሩት የተባበሩት መንግሥታት እና ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ላይ ነው።
በዩናይትድ ኪንግደም በርሚንግሃም ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ፣ ፌደራሊዝም እና የፖሊሲ መምህር የሆኑት ዶ/ር ብዙነህ ይመኑ ደግሞ ኢትዮጵያ እና ኤርትራ “ከሁለቱ ጄኔራሎች አንዳቸውን ስለመደገፋቸው ምንም ዓይነት ተጨባጭ መረጃ የለም” ይላሉ።
እስካሁን ከሁለቱ ጄኔራሎች የበላይነት የያዘው አለመታወቁን የሚያነሱት ምሑሩ፣ በዚህ ወቅት አንድን አካል መደገፍ አደጋ እንደሚኖረው ጠቁመዋል።
ሆኖም ጦርነቱ ከተራዘመ የሱዳንን እንድትረጋጋ በማለት “ጎረቤት አገራት አንድን ወገን መደገፋቸው አይቀርም” ሲሉ ስጋታቸውን ያስቀምጣሉ።

ኢትዮጵያ እና ኤርትራ ምን ሚና ሊኖራቸው ይችላል?
እንደ መሐመድ ከሆነ ፕሬዝዳንት ኢሳያስ “በአንድ አገር ውስጥ አንድ ጠንካራ ሠራዊት መኖርን” ይደግፋሉ።
ከአልበሽር ውድቀት በኋላ አገሪቱ በአንድ መደበኛ ሠራዊት ብቻ መመራት እንደነበረባት እና አሁን ለተፈጠረው ምስቅልቅል በወቅቱ የተደረገው ስምምነት እና የጋራ መንግሥት ምሥረታን ተጠያቂ እንደሚያደርጉ ይገልጻል።
ይህ በሲቪሉ እና በወታደራዊው ኃይሎች መካከል የተደረሰው የጋራ መንግሥት ምሥረታ ነው አብደላ ሐምዶክን ጠቅላይ ሚኒስትር አድርጎ ለከፍተኛው ሥልጣን አብቅቷቸው የነበረው።
በዚህ ውስጥ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የአሸማጋይነት ሚና ትልቅ እንደነበር ይታወሳል። አሁንም ከግጭቱ መቀስቀስ በኋላ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሁለቱም ወገኖች እንዲነጋገሩ እና ለችግሩ መፍትሄ እንዲፈልጉ ጥሪ ማቅረባቸው እና መነጋገራቸው ተዘግቧል።
ከዚህ አንጻር ይህ የፕሬዚዳንት ኢሳይያስ ወደ አንድ ወገን የማዘንበል አዝማሚያ እና አስተያየት፣ ለመሐመድ የጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይን ሚና (ኢኒሼቲቭ) የሚቃረን ይመስላል።
እንደ መሐመድ ከሆነ የሱዳን እና የኢትዮጵያ ግንኙነት በተለይም ከሰሜን ኢትዮጵያው የእርስ በእርስ ጦርነት በኋላ ንፋስ ገብቶታል።
“አለመተማመን ተፈጥሯል፤ አሁን የኢትዮጵያ ሚና እምብዛም የጎላ አይደለም። በእርግጥ የኢትዮጵያ አቋም ነበር ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባው። ከቱርክ ጋር የጋራ ኢኒሼቲቭ አቅርበዋል የሚል መረጃ ቢኖርም ይህን ያህል ሚዛን የሚደፋ አይደለም” ብሏል።
ይህ በሁለቱ አገራት መካከል ያለውን ግንኙነት ከማሳየት ባለፈ ኢትዮጵያ የሱዳንን ችግር ለመፍታት የቱርክ እገዛም አያስፈልጋትም ይላል።
ዶ/ር ብዙነህ በበኩላቸው ሁለቱም ጎረቤት አገራት አንድን አካል ከመደገፍ ይልቅ፣ ቢቻል የሚዋጉትን አካላት እንዲወያዩ መገፋፋት ይኖርባቸዋል ይላሉ።
በሱዳን ያለውንም ነገር የአገር ጥቅምን ባማከለ ከጎረቤት አገራት እና ከዓለም አቀፍ አጋሮች ጋር ያላቸውን ግንኙነት ከግምት ውስጥ በማስገባት መከታተልም ይኖርባቸዋል።
ኢትዮጵያ እና ኤርትራ በሱዳን ያለውን ጦርነት ከመተንተን ባለፈ ግብፅ እና ሱዳን ከኢትዮጵያ ጋር በታላቁ ሕዳሴ ግድብ ምክንያት ለዓመታት ውዝግብ ውስጥ መቆየታቸውም መታየት እንዳለበት ይጠቁማሉ።
ኢትዮጵያን ጨምሮ ሌሎች ጎረቤት አገራትም አሁን ባለው ሁኔታ ጦርነቱ እንዲያበቃ መፈለጋቸውን በማንሳት አገራቱ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እና የአፍሪካ ኅብረትን በመሰሉ ተቋማትን ተጠቅመው ሁለቱም አካላት ወደ ድርድር እንዲመለሱ መንገድ ማመቻቸት አለባቸው ይላሉ።
የፖለቲካ ተንታኞኙ አደም ካሴ በቅርቡ ለቢቢሲ እንደተናገሩት ኢትዮጵያ ከሱዳን ጋር ያላትን ግንኙነት ከዓለም አቀፍ ግንኙነት አንጻር ልታየው እንደሚገባ መክረዋል።
ኢትዮጵያ በሰሜን ክፍሏ ጦርነት ወቅት በሱዳን ተወስደውብኛል የምታላቸውን አካባቢዎች በዚህ ወቅት መልሶ መውሰድ ከሠላም፣ ከሕዳሴ ግድብ እና ከዓለም አቀፍ ተቀባይነት አንጻር ማየትም ይገባታል ይላሉ።
በተለይም እነዚህ የግዛት ይገባኛል ጥያቄ የሚነሳባቸውን አካባቢዎችን በኃይል መልሶ ለመያዝ ጥረት ማድረጉ አዋጭ አለመሆኑን አደም ያስረዳሉ።
ግጭቱ ለኢትዮጵያ እና ለኤርትራ ሊተርፍ ይችላል?
የሱዳን ግጭት በካርቱም እና በአካባቢዋ ብቻ አልተወሰነም። ወደ ሌሎች ከተሞችም ተዛምቷል። እስካሁን ግን ይህ ነው የሚባል ተጽዕኖ በኢትዮጵያም ሆነ በኤርትራ ላይ አላሳረፈም።
ግጭቱ ተባብሶ ከቀጠለ ሰፊ ድንበር ለሚጋሩት፤ የባህል እና የብሔር ስብጥር ባላቸው በእነዚህ አገራት መካከል አደጋው ቀላል ላይሆን እንደሚችል ይታመናል።
የሱዳን ግጭት ከተራዘመ በሁለቱ ጎረቤት አገራት ላይ ጫናው እንደሚበረታ ሁሉም ምሑራን የሚስማሙበት ነው።
“የኢትዮጵያ ሕዝብ ሲቸገር ወደ ሱዳን ይሰደዳል። የሱዳን ዜጎች ሲቸገሩ ደግሞ ወደ ኢትዮጵያ ያማትራሉ” ይላሉ ዶ/ር ብዙነህ። ከኢትዮጵያ ጋር ሰፊ ድንበር የምትጋራው ሱዳን ወደ ግጭት ማምራቷ ለኢትዮጵያ የፀጥታ ስጋት ሊደቅን እንደሚችልም ያስረዳሉ።
የሰዎች ስደት እና የሕገወጥ የጦር መሣሪያ ዝውውር በአካባቢው መጧጧፍ በደንበር አካባቢ ለሚንቀሳቀሱ ሽምቅ ተዋጊዎች መሣሪያ በቀላሉ እንዲያገኙ እንደሚያደርግ እንደአብነት ያነሳሉ።
ሽምቅ ተዋጊዎች ብቻ ሳይሆኑ ሲቪሎችም የጦር መሣሪያ በቀላሉ እንዲያገኙ ዕድል በመፍጠር በግለሰቦች እና በማኅበረሰቦች ማከል የግጭት ምንጭ ሊሆን ይችላል ይላሉ።
ሌላው ደግሞ የሱዳን ተዋጊዎች የኢትዮጵያን ድንበር መጠለያ ሊያደርጉት መቻላቸውን በማንሳት ጦርነቱ ከተራዘመ “ወደ ሠላም እየተመለሰች ያለችውን ኢትዮጵያ ሠላም እንዲደፈርስ ሊያደርግ ይችላል” በማለት ስጋታቸውን የስቀምጣሉ።
“ጦርነቱ ወደ ምሥራቅ ሱዳን [ገዳሪፍ፣ ከሰላ እና አካባቢው] የሚጠጋ ከሆነ ለኢትዮጵያም ሆነ ለኤርትራ ከፍተኛ የፀጥታ ችግር ሊደቅን ይችላል። ይህ ጦርነት የሚቀጥል ከሆነ ከፍተኛ ጠባሳ ጥሎ ሊያልፍ ይችላል” ይላል ጋዜጠኛ መሐመድ።
አሁን እየታየ እንዳለውም ጦርነቱ ባስከተለው ስጋት ምናልባትም ከፍተኛ የሱዳናውያን መፈናቀል እና ስደት ሊያስከትል እንደሚችል በመጥቀስ የሱዳን ጦርነት ዘርፈ ብዙ ተጽእኖን በጎረቤቶቿ ላይ እንደሚያስከትል አመልክቷል።
