
የህዝብና የሀገር ህልውና ከግል ኑሮና ህይዎት በላይ ነው! ልደቱ አያሌው ግንቦት 15/2015
===
የአለፈው የ31 ዓመታት የትግል ታሪኬ በግልፅ እንደሚያሳየው እኔ አሸባሪነትን አምርሬ የምቃዎም ሰው ነኝ።
እንኳንስ ሽብርተኝነትን ማንኛውንም አይነት የትጥቅ ትግል የማልደግፍና ፀረ-አብዮተኛ የሆንኩ ፖለቲከኛ ነኝ። በየትኛውም አይነት ግፊትና ጫና ከዚህ ሰላማዊ አመለካከቴ መቸም ቢሆን ተዛንፌ ላለመገኘት ለራሴ ቃል ከገባሁም ቢያንስ ሁለት አስርት ዓመታት አልፈዋል። ወደፊትም ከዚህ የተለዬ አቋም አይኖረኝም።
ይሁንና በሚሊዬን ለሚቆጠር ህዝብ ዕልቂትና ስደት የህግ ተጠያቂ መሆን የሚገባው የወቅቱ የዶ/ር ዐቢይ
መንግስት ያለምንም ተጨባጭ ምክኒያት በአሸባሪነት ከሶኛል። የአገሪቱ መንግስት ጦርነትንና ሽብር መንዛትን የአገዛዝ ስልቱ ዋና መሳሪያ አድርጐ በሚጠቀምበት፣ የመንግስት መገናኛ ብዙሀንና ባለስልጣናት የዘር ጭፍጨፋን ጭምር በይፋ እየቀሰቀሱ ከህግ ተጠያቂነት ውጭ ሆነው በሚኖሩበት፣ ንፁሀን ዜጐችን በአደባባይ በስለት ያረዱና በቁማቸው በእሳት ያቃጠሉ አረመኔዎች የህግ ተጠያቂ ሲሆኑ ባልታዬበት አገር እድሜ ልኬን የሰላም ጠበቃ ሆኘ የኖርኩትንና ለዚህ አቋሜም ከፍተኛ ዋጋ የከፈልኩትን ሰው በሽብርተኝነት መወንጀሉ አገዛዙ በምን ዓይነት የሞራል ቀውስ ውስጥ እንደሚገኝ ግልፅ ማሳያ ስለሆነ አገዛዙ ምን ያህል
ጨካኝና የሚሰራውን የማያውቅ መሆኑን ባውቅም ህወሃትና “ኦነግ-ሸኔን” ሳይቀር በሽብርተኝነት መፈረጅ ለአገራችን ሠላም አይጠቅምም እያልኩ የምከራከረውን ሰው በሽብርተኝነት ይከሳሉ ብዬ ግን አልጠበቅሁም
ነበር፡፡
በእኔ እምነት እንዲህ አይነት የፈጠራ ክስ የቀረበብኝ በሚከተሉት ምክኒያቶች ነው።
1. ዶ/ር ዐቢይ አገሪቱን በብቃት ለመምራት የሚያስችል ዕውቀት፣ ልምድ፣ ቅንነት የሌላቸውና የብሄራዊ ደህንነታችን ስጋት የሆኑ አምባገነናዊ መሪ በመሆናቸው በስልጣን ላይ ሊቀጥሉ አይገባም የሚል አቋም በይፋ እያራመድኩ በመሆኑ፣
2. የኢትዮጵያ ህዝብ የጐንዮሽ የእርስ-በርስ ግጭትን አቁሞ የትግል ሙሉ ትኩረቱን በአምባገነናዊው መንግስት ላይ እንዲያደርግ ግፊት እያደረግሁ በመሆኔ፣
3. በኦሮሞ ህዝብ ስም የሚነግዱ ጥቂት ፅንፈኛ ብሄርተኞች ሲቻል በኢትዮጵያ ፍርስራሽ ላይ “አገረኦሮሚያን” ለመመስረት፣ ካልተቻለም የአንድን ብሄር ሁለንተናዊ የበላይነት በአገሪቱ ላይ ለመጫን እየሰሩ መሆናቸውን ለህዝብ በማጋለጤ፣
4. የትግራይና የአማራ ህዝብ ከእርስ-በርስ ግጭት እንዲዎጡና በመካከላቸው ያለውን ቅራኔ በውይይትና በድርድር በመፍታት ለህልውናቸው መከበር በጋራ እንዲቆሙ የሚያስችል ጥረት እያደረግሁ በመሆኔ፣
5. የኢትዮጵያ ህዝብ በምን ዓይነት ሁኔታ ጠንካራ ሰላማዊ ትግል ማካሄድና ራሱንና ሀገሩን ከህልውና አደጋ መታደግ እንደሚችል አቅጣጫ ለማሳየት እየሞከርኩ በመሆኔ፣
6. የሽብርተኝነት ክሱን በመፍራትም ወደ አገሬ እንዳልመለስና ሰላማዊ ትግሉን መቀጠል የማልችልበት ሁኔታ እንዲፈጠር በመታሰቡ፣
7. ዓይነተኛዎቹ ምክኒያቶች ከዚህ በላይ የጠቀስኳቸው ቢሆኑም የወቅቱ የጥቃት ተረኛ የሆነው የአማራ ህዝብ ተዎላጅ ሆኘ መገኘቴም በተለየ ሁኔታ የጥቃት ሰለባ እንድሆን ተጨማሪ ምክኒያት ሆኗል ብዬ አምናለሁ።
በአጠቃላይ የወቅቱ አምባገነናዊ መንግስት ፍላጐት ዜጐችን በማስፈራራት፣ በማሰርና በመግደል ማንኛውንም አይነት የተቃውሞ እንቅስቃሴ ፀጥ-ዕረጭ አድርጐ በማፈን የሚፈልገውን ዐላማ በኃይል ማስፈፀም መቻል ነው።
አገዛዙ ይህንን ፍላጐቱን የማሳካት ዕድል እንዲያገኝ ፈፅሞ ልንፈቅድለት አይገባም። እርግጥ ነው እንደ እኔ ለእውነተኛ ሰላምና ዴሞክራሲ ሲል የህይዎት ዘመን ዋጋ ለከፈለና
በከፍተኛ የጤና ችግር ውስጥ ለሚገኝ ሰው በሚጠየፈው የሽብርተኝነት ድርጊት በጭፍን መፈረጅና መታሰር መፈጠርንና ዓለምን እየጠሉ የመኖር ያህል ስሜትን በእጅጉ የሚጐዳ ሁነት ነው። ይሁንና የዶ/ር ዐቢይ መንግስት በአሁኑ ወቅት የጋረጠብን አደጋ ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶችን
ከመጨፍለቅም ባለፈ ዜግነትን፣ ማንነትንና አገርን የሚያሳጣ ነው።
እንዲህ አይነቱን በታሪካችን አይተነው በማናውቀው መጠን የገጠመንን የወቅቱን ከፍተኛ አደጋ ዜጐች ከመታሰርና ከመታፈንም በላይ የህይዎት መስዋዕትነት ጭምር ሳንከፍል የአደጋውን ክብደት በአግባቡ ማሳዬትም ሆነ አደጋውን በቀላሉ ልንቀለብሰው አንችልም።
ስለሆነም እንደ ዶ/ር ዐቢይ አይነት ስልጣናቸውን ከአገርና ከህዝብ በላይ አድርገው የሚያዩ ግብዝ መሪዎች ለአገርና ለህዝብ ህልውና ስንል ማናቸውንም ዓይነት መስዋዕትነት ለመክፈል ዝግጁ የሆን ዜጐች በአገሪቱ መኖራችንን እንዲያውቁ ማድረግና ህዝብን በጅምላ አፈናና ግድያ በዘላቂነት ማሸነፍ እንደማይቻልም በተግባር ማሳየት ያስፈልጋል።
ዶ/ር ዐቢይ “በገንዘብ ወይም በስልጣን ጥቅም የማይገዛ ማንም ሰው የለም” ብለው እንደሚያምኑት ሳይሆን የአገርንና የህዝብን የህልውና ጉዳይ ከግል ኑሮአችንና ውድ ህይዎታችን በላይ ታላቅና ምትክ-የለሽ አጀንዳ አድርገን የምናይ አያሌ ዜጐች በአገሪቱ ስለመኖራችን በተግባር ማሳዬት
አለብን ብዬ አምናለሁ።
ከአገዛዙ አፈና፣ እስርና ግድያ ሸሽቶ በማምለጥ የሚመጣ መፍትሄ የለም። ትግላችን ሰላማዊና ህጋዊ እስከሆነ ድረስ በገፍ እየታሰርንና እየሞትን አገዛዙ በሀይልና በአፈና ሊያሸንፈን እንደማይችል ተስፋ ልናስቆርጠው ይገባል። በዚህ መጠን ዋጋ ለመክፈል ካልቆረጥን በስተቀር የአገርና የህዝብ ህልውና ከጥፋት ሊድን አይችልምና። ይህንን በለጋ የልጅነት ዘመኔ ለራሴ የገባሁትን የትግል ቃል-ኪዳንና የምታመንለትን
የሰላማዊነትና ህጋዊነት መርህ መሰረት በማድረግ ወደ አገሬ ለመመለስና የዶ/ር ዐቢይን የፈጠራ የአሸባሪነት ክስ እንደተለመደው በፍትህ አደባባይ ለመጋፈጥ ወስኛለሁ።
ስለሆነም በታሰርኩ ቁጥር ከእኔ በላይ ስቃዬን የምትሰቃዩ ቤተ-ዘመዶቸ፣ ጓደኞቸ፣ የሃሳብ ደጋፊዎቸና የትግል አጋሮቸ ይህንን ውሳኔዬን የሞኝነት፣ የአጉል ጀብደኝነት ወይም የመንግስትን የጭካኔ ደረጃ በአግባቡ ያለመረዳት ድክመት አድርጋችሁ እንዳታዩብኝና ያልተገባ ጫና እንዳትፈጥሩብኝ በዚህ አጋጣሚ በአክብሮት እማፀናለሁ። ይህንን ውሳኔ በሚገባ አስቤበትና ከልቤ አምኘበት የወሰንኩት ስለሆነ በሞራል ልታግዙኝ ይገባል እንጂ ልታዝኑልኝም ሆነ ልታዝኑብኝ አይገባም እላለሁ።
እርግጥ ነው የአንድ ሰው ብቸኛ ፈላጭ ቆራጭነት በነገሰበትና ባለስልጣናት ከህግ በላይ በሆኑበት አገር ከህግ በታች ሆኖ ለመገኘት ወደ ኢትዮጵያ መሄድና ወህኒ-ቤት መግባት የሞኝነት ውሳኔ ተደርጐ ቢታይ አያስደንቅም። እንዲህ ዓይነቱ ውሳኔም ውድ ህይዎትን እስከማጣት የሚደርስ ውጤት ሊያስከትል እንደሚችልም በሚገባ እገነዘባለሁ።
የሚሊዬን ህዝብ ዕልቂት የማያስደነግጠው የወቅቱ አገዛዝም ለአንድ ዜጋ ህይወት ደንታ እንደማይኖረው ጠንቅቄ አውቃለሁ። ይሁንና ኢትዮጵያና የኢትዮጵያ ህዝብ በመኖርና ባለመኖር የህልውና አደጋ ላይ በወደቁበት በአሁኑ ወቅት እንደ እኔ በትግሉ ሂደት የህይዎት ዘመን ዋጋ ለከፈለ የፖለቲካ ሰው ከህዝቡ ተለይቶና በፈጠራ ክስ የወንጀል ታዳኝ (Fugitive) ሆኖ በስደት መኖር ከሙትነት ያላነሰና እንቅልፍ የማያስተኛ መራር ህይዎት ስለሆነ ወደ አገሬ ለመሄድና ማንኛውንም ዋጋ ለመክፈል ወስኛለሁ። እንዲያውም የምንገኝበት አሳሳቢ ወቅት አንዳችን ታጋይ ሌላችን ገላጋይ የምንሆንበት ስላልሆነ ሁላችንም ለጋራ ህልውናችን መከበር የጋራ ትግል ለማድረግ ከመቸውም ጊዜ በላይ በብቃት መንቃት፣ በከፍተኛ ፍጥነት መደራጀትና በቁርጠኝነት
የሰላማዊ ትግሉ ቀዳሚ ሰልፈኛ መሆን ይገባናል።
በመጨረሻም ወደ አገሬ ተመልሸ የግፈኛው የዶ/ር ዐቢይ አህመድ የአካልና የህሊና ዕስረኛ ከመሆኔ በፊት
በውጭ አገር በሚኖረኝ የጥቂት ጊዜ ቆይታ በአገራችን ወቅታዊ ጉዳዮችና የወደፊት ዕጣ-ፈንታ ዙሪያ
በተለያዩ የመገናኛ ብዙሀን ተከታታይ ቃለ-መጠይቆችን ለመስጠት አስቤአለሁ። በእነዚህ ቃለ-መጠይቆች
ወይም የውይይት መድረኮች ላይም
1. አገራችን የምትገኝበት ወቅታዊ ሁኔታ ምን ይመስላል?
2. የኦሮሞ፣ የአማራና የትግራይ ብሄርተኝነት እንዴት ሊገራና ወደ ጤናማና ገንቢ የትብብር ፖለቲካ
ሊሸጋገር ይቻላል?
3. በአሁኑ ወቅት በተለዬ ሁኔታ የጥቃት ዒላማ ተረኛ የተደረገው የአማራ ህዝብ ራሱን ከህልውና
አደጋ እንዴት በብቃት መታደግ ይችላል?
4. አገሪቱን ከህልውና አደጋ ለመታደግ የሚያስችለን ዘላቂ መፍትሄ ምንድን ነው?
5. ኢትዮጵያውያን ሰላማዊ ትግሉን እንዴት ማጠናከርና ለአሸናፊነት መብቃት እንችላለን? በሚሉትና በሌሎች ተዛማጅ ጥያቄዎች ዙሪያ ያለኝን የግል ምልከታ ለማሳየት እሞክራለሁ።
ስለሆነም ተመልሰን እንደምንገናኝ እርግጠኛ መሆን አይቻልምና በመገናኛ ብዙሀኑ በግልፅነትና በድፍረት
ለማቅረብ የምሞክራቸውን አስተያዬቶች ከመቸውም ጊዜ በላይ በአንክሮ ለመከታተልና ከስሜታዊነት በራቀ
መንፈስ ለመረዳት እንድትሞክሩ ልባዊ ተማፅኖዬን ከወዲሁ በአክብሮት ለማቅረብ እዎዳለሁ። መገናኛ ብዙሀንም በእነዚህ ርዕሰ-ጉዳዮች ዙሪያ የውይይት መድረክ በማመቻቸት እንድትተባበሩኝ በዚህ አጋጣሚ እጠይቃለሁ።
ልደቱ አያሌው
ግንቦት 1 ቀን 2015 ዓ.ም
ዋሽንግተን ዲሲ
