May 9, 2023 

ሽምግልና የስርዓቱ ቋሚ የማወናበጃ ዘይቤ ነው

ከባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ የተሰጠ መግለጫ

ህወሓት የተከበሩ ነገሮችን የማርከስ ክፉ ልክፍት የተጣባው ቡድን ነበር። ህወሓት በስልጣን ላይ በቆየባቸው ሀያ ሰባት አመታት በርካታ የተከበሩ ዕሴቶችን አቃሏል፤ ክብራቸውን ቀንሷል፤ አይነኬ የሆኑ ጉዳዮችን ደፍሯል። የኢትዮጵያውያን ማህበራዊ ውቅር መገለጫ የሆኑ እሴቶችን ዋጋ እንዳይኖራቸው አድርጓል። ክብሩን በጥቅም የሚለውጥ፣ ሰውን በማንነቱ ሳይሆን በዘውግ የሚፈርጅ፣ ታማኝነት እንደ ጅል የሚቆጥር ትውልድ እንዲፈጠር በማድረግ የነበሩንን የማንነት ዕሴቶች እንዲጠፉ ስርዓቱ አቅዶ ሲሰራ ቆይቷል። ዜጎች የመንፈስና የሞራል ልዕልናቸው እንዲያሽቆለቁል እና ሕይወታቸው በቅፅበታዊ ደስታና ዳንኪራ እንዲፈዝ ስርዓቱ ጉልህ አስተወፅኦ አድርጓል። የህወሓት የመንፈስ ወራሽ የሆነው ኦህዴድ/ብልፅግናም እሴቶቻችንን የማርከስ እና የማቃለል ስራውን ቀጥሎበታል። ላለፉት ሰላሳ ሁለት ዓመታት ባለስልጣናቱ በሚያራምዱት ምግባረ ብልሹ አስተዳደር፣  በሚያዘወትሩት የሀሰት ፖሮፓጋንዳ እና መንግስታዊ መዋቅሩ የውንብድና ተግባር ማስፈፀሚያ እንዲሆን በማድረግ የሃገር ሃብትን በመዝረፍ ላይ ተገነባ አሠራርን በማስፈን፣ የሃገሪቱን መንግሥታዊ ተቋም የከሸፈ መንግሥት (Failed state) እንዲሆን አድርገውታል። በዚህም አስከፊ ክንውናቸው የሃገሪቱ መሪዎች በእጅጉ ድኩማኖች እንደሆኑ ለመረዳት ችለናል። ከወለጋ፣ ከቢኒሻንጉል እና ከተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ሰዎችን እያፈናቀሉ እና ዜጎችን በርሀብ እየቆሉ፣ የኢትዮጵያን ሕዝብ የእርዳታ ጠባቂ እና በመፅዋት የሚኖር ሕዝብ እንዲሆን ፈርደውበታል። የራሱን እያሳረረ የሎሌችን የሚያማስል ስርዓት አንግበን፣ በዜጎች ህመም እና ቁስል ላይ የሚሳለቁ ባለስልጣናትን ሀገሪቱ ይዛ መቀጠሏ አሳፋሪም አስገራሚም ሁኗል።

በተመሳሳይ ሁኔታ ስርዓቱ የሽምግልና እና የእርቅ ስርዓታችንን ጥላእሸት እየቀባ መቀለጃ ካደረገው ውሎ አድሯል፡፡ ህዝቡ ለሽምግልና እና ለእርቅ የሚሰጠውን ዋጋ በመረዳት፣ ማህበረሰቡ የሚያከብረውን የሽምግልና እሴት ዛሬም በማታለያነት እየተጠቀመበት ይገኛል። የሌሎች ክልሎች ልዩ ሃይሎች ትጥቅ እንዲፈቱ ሳይደረግ የኦህዴድ/ብልፅግና ስርዓት የአማራን ህዝብ ትጥቁን ለማስፈታት ጦር ካወጀበት ቀናት አልፈዋል። ህዝቡም የተቃጣብትን ጥቃት ለመመከት ሲነሳ የኦህዴድ/ኦነግ ብልፅግና አገዛዝ የተቀጣጠለውን ትግል በሽምግልና ስም ለማዳፈን ደፋ ቀና ሲል ይታያል። ስርዓቱ  በማወናበድ እና በማጭበርበር ስልታዊ ጥቃት ለማድረስ አስቦ እንጅ ጉዳዩን በሽምግልና እንዲታይ ፈልጎ እንዳልሆነ ከስርዓቱ የአጭበርባሪነት ታሪክ ለመረዳት አያዳግትም። ስርዓቱ በሽምግልና ስም ጊዜ ጠብቆ ሊያጠቃ እንጅ በሽምግልና አለመግባባቶችን የመፍታት የመንግስትነትን ብቃት የተላበሰ እንዳልሆነ ልብ ማለት ይገባል። በመሆኑም ባልደራስ የአማራ ህዝብ ለሚከተሉት ጉዳዬች ትኩረት እንዲሰጣቸው ጥሪውን  ያቀርባል።

➢ የአማራ ህዝብ ሆይ! በሽምግልና ስም በርካታ  የቁርጥ ቀን ልጆችህን አጥተሀል። የሀገሪቱን የሽምግልና እሴት በማክበር  በሽምግልና ስም ብርቅዬ ልጆችህ ታፍነዋል፣ ዛሬም በርካታ ልጆችህ በእስር ላይ ይገኛሉ፡፡ ስለዚህም ዛሬም እንደ ትናንቱ ከስርዓቱ ጋር የሚደረግን ሽምግልና አምነህ እንዳትታለል ልትጠነቀቅ ይገባል።

➢ የኦህዴድ/ብልፅግና ስርዓት በሽምግልና ስም የተቀጣጠለውን ትግል ለመጎተት፣ የነፃነት ታጋዬችን ለማፈን፣ ጊዜ በመግዛት ለዳግም ጥቃት የመዘጋጃ ጊዜ ለማግኜት የሚጠቀምበት ስልት እንደሆነ በመረዳት፣ የጀመርከዉን የህልዉና ትግል ወደ ኋላ ሳትጎትት መዳረሻህ የስርዓት ለውጥ መሆኑን ተረድተህ ትግሉን ህዝባዊ አድርገህ መቀጠል ይጠበቅበሃል።

➢ የኦህዴድ/ብልፅግና ስርዓት ዘግናኝ ግፎችን በኢትዮጵያ ሕዝብ በተለይም በአማራው ላይ ሲፈፅም የቆየ እና እየፈፀመ ያለ በመሆኑ አምርረህ ልንታገለው የሚገባ አስከፊ ስርዓት ነው። ይህን አስከፊ ስርዓት ያላወገዘ ሽማግሌ ዛሬ ምን ብሎ ለሽምግልና ይቀመጣል? ዜጎች ሲታረዱ፣ በግሪደር በጅምላ ሲቀበሩ፣ ፅንስ ብሄር ተሰጦት በቢለዋ ሲቀደድ፣ዜጎች ቤታቸው ፈርሶ በጅብ ሲበሉ፣ ዜጎች መንግሥት መር በሆነው የኖሮ ውድነት በችጋር እና ጉስቁልና ሲማቅቁ፣ የሰው ልጅ ህይወት መቀለጃ በሆነበት ሀገር እውን ሽማግሌዎች ወይም አባ ገዳዎች ሊኖሩ ይችላሉን?  ለመሆኑ እነዚህ ሽማግሌዎች ነን ባዮች ባለፉት አምስት ዓመታት ከላይ የተጠቀሱትን ዘግናኝ ሁኔታዎችን ለመንግሥት በማስገንዘብ መንግሥት አካሄዱን እንዲቀይር/እንዲያሻሽል መክረው እንዳማያውቁ ይታወቃል። እውነተኞቹ የአማራው ህዝብ ሽማግሌዎች ከአማራው ህዝብ ተጋድሎ ጎን የሚቆሙ እንጅ የኦህዴድ/ኦነግ የብልጽግና መንግስት በሚዎረወርላቸው መናኛ መደለያ ከርሳቸውን የሚሞሉና እና ለግል ጥቅማቸው ማሟላት አጋጣሚ የሚጠብቁ ዱርዬዎች እንደሆኑ ሊታወቁ ይገባል፡፡ በተለይ በአሁኑ ጊዜ የአማራው ህዝብ ትግል በደረሰበት ወሳኝ ደረጃ ላይ ያላሰለሰ ትግል እንጂ ሽማግልና  የተጀመረውን የህልውና ትግል እንደሚያኮላሽ ተረድቶ፣ የአማራው ማህበረሰብ ለህለዉናህው እና ለክብሩ የጀመረዉን ትግል መቀጠል ይጠበቅበታል፡፡ የአማራው ማህበረሰብ የመደራደር አቅሙን ለማጎልበት የሚችለው በጀመረዉ የህለዉና ትግል ያለማሰለስ በመግፋት ብቻ ነው፡፡ በሽምግልና የሚገኝ ነፃነት እንደሌለ ብቻ ሳይሆን ኑሮም እንደማያውቅ በፅኑ መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ አማራው በተከታታይ ጌዜ ለደረሰበት እና  በተገቢው ላስተዋለው ተደጋጋሚ ክህደት ለመጋለጥ ከፈለገ “የሽምግልና ስርዓቱን” አንቅሮ በመትፋት የጀመረዉን የህልዉና ማስከበር ትግል ሳያሰልስ እንዲገፋበት ፓርቲያችን ባልደራስ በጽኑ ሊያሳስብ ይወዳል፡፡

ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ
ሚያዚያ 30/2015
አዲስ አበባ