
ከ 9 ሰአት በፊት
በሰሜን ናይጄሪያ የምትኖር አንዲት የ20 ዓመት ወጣት ለማታውቀው ሰው ሊድሯት የተነሱትን አባቷን ከሳ ፍርድ ቤት ማቆሟ ተነገረ።
ፋጢማ አሊዩ የተባለችው ወጣት በአባቷ አማካይነት የመጣላትን ባል አላገባም በማለት ከመቃወሟ በተጨማሪ፣ ጉዳዩን በአካባቢዋ ወዳለ የሸሪአ ፍርድ ቤት ወስዳዋለች።
የፋጢማን ጉዳይ የያዙት ጠበቃ በናይጄሪያዋ ግዛት ካዱና ውስጥ ለሚገኘው አስላማዊ ፍርድ ቤት፣ ወጣቷ የምታፈቅረው ሌላ ሰው እንዳላት አስረድተዋል።
“አባት ደንበኛዬ ናይጀር ግዛት ውስጥ ያለ ግለሰብን እንድታገባ ይፈልጋሉ። እሷ ግን ፈቃደኛ አይደለችም፤ አስገድደው እንደሚድሯት ስለዛቱ በአሁኑ ወቅት አክስቷ ጋር ነው ያለችው” በማለት ጠበቃው ለፍርድ ቤቱ ተናግረዋል።
ጨምረው ፋጢማ ለማታውቀው ሰው ሊድሯት ያሰቡትን አባቷን የከሰሰችው ለአባቷ አክብሮት ስለሌላት እንዳልሆነም ተናግረዋል።
አባቷም ለልጃቸው ያመጡትን ባል ወላጆቻቸው በሕይወት እንዳሉ የመረጡት መሆኑን እና አሁን ሊድሯት የተነሱት የወላጆቻቸውን ፍላጎት በማሟላት አክብሮታቸውን ለመግለጽ እንደሆነ ለፍርድ ቤቱ አስረድተዋል።
ነገር ግን ጉዳዩን የተመለከቱት ዳኛ ማላም አይኩ አብዱልራህማን በሰጡት ውሳኔ፣ ምንም እንኳን አባት ለልጃቸው የሚሆን ባል የመምረጥ መብት ቢኖራቸውም በግድ እንድታገባ ማድረግ ግን የሚበረታታ ተግባር አይደለም ብለዋል።
ጨምረውም አባት ልጃቸውን እንዲታገሷት እና ፍላጎቷን እንዲያከብሩ መክረዋል።
“ለማግባት የምትፈልገውን ግለሰብ እንድታስተዋውቅ ፍቀዱላት፣ በሃይማኖቱ እና በፀባዩ ደስተኛ ከሆኑ እንድታገባው ፈቃዳችሁን ስጧት” ሲሉ የሸሪአ ፍርድ ቤቱ ዳኛ ማዘዛቸው ተዘግቧል።
ከዚህ ቀደም ስድስት ሴት ልጆቻቸውን በተመሳሳይ መንገድ እደዳሩ ለፍርድ ቤቱ የተናገሩት አባት፣ ልጆቻቸው ጥሩ ትዳር አላቻው ብለዋል።
ፋጢማ ለማታውቀው ሰው እንድትዳር ሃሳቡን ያቀረቡት እናቷ እንደሆኑ የተገለጸ ሲሆን፣ አባትየውም “በዚህ ጉዳይ ላይ ከሌሎች ሰዎች ጋር መመካከር ስለምፈልግ እንዲፈቀድልኝ እጠይቃለሁ ብለዋል።
