May 10, 2023 – BBC Amharic 

በፖሊስ ቁጥጥር ስር መዋሏ የተነገረው ተጠርጣሪ
የምስሉ መግለጫ,በፖሊስ ቁጥጥር ስር መዋሏ የተነገረው ተጠርጣሪ

9 ግንቦት 2023

ሁለት ህጸናትን በአሰቃቂ ሁኔታ ገድላለች ተብላ በመጠርጠር ከቅዳሜ ጀምሮ በፖሊስ ስትታደን የነበረችው ግለሰብ ዛሬ ማክሰኞ ከሰዓት በኋላ በቁጥጥር ሥር መዋሏን ፖሊስ አስታወቀ።

ከአዲስ አበባ በቅርብ ርቀት በምትገኘው የቡራዩ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ የወንጀል ምርመራ ክፍል ባልደረባ የሆኑት ዋና ሳጅን ቀነኒሳ ታደሰ ለቢቢሲ እንደተናገሩት፣ ተጠርጣሪዋ ልትያዝ የቻለችው ሕብረተሰቡ በሰጠው ጥቆማ ነው።

በኦሮሚያ ክልል፣ በሸገር ከተማ፣ በቡራዩ ክፍለ ከተማ ውስጥ የእንጀራ ልጆቿ የሆኑትን ሁለት ታዳጊዎችን በአሰቃቂ ሁኔታ በመግደል መጠርጠሯን የሚገልጸው ዜና ከወጣ ወዲህ ፖሊስ ከፍተኛ አሰሳ ላይ ነበር ብለዋል ሳጅን ቀነኒሳ።

ወንጀሉ የተፈፀመው ቅዳሜ ሚያዝያ 28/2015 ዓ.ም. በቡራዩ ክፍለ ከተማ፣ በከታ ወረዳ ልዩ ስሙ ሦስተኛ ቡራዩ በሚባል ስፍራ ነበር።

ነጋሴ ከበደ የተባለችው ተጠርጣሪ ልጆቹን በአሰቃቂ ሁኔታ በመግደል፣ ብርድ ልብስ አልብሳ በእሳት በመለኮስ ጭምር ወንጀሉን ፈጽማለች ተብላ መጠርጧ ብዙ ሰዎችን ሲያነጋግር ቆይቷል።

በቡራዩ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ የወንጀል ምርመራ ክፍል ባልደረባ የሆኑት ዋና ሳጅን ቀነኒሳ ታደሰ ተጠርጣሪዋ የተያዘችው፣ እዚያው ቡራዩ ኤጀርሳ ጎሮ ሳንሱሲ በሚባል ስፍራ ራሷን ለማጥፋት ወደ ጫካ ስትሄድ ለፖሊስ በደረሰ ጥቆማ መሆኑን ለቢቢሲ ተናገረዋል።

በአሁኑ ጊዜ በፖሊስ ቁጥጥር ስር የምትገኘውን የተጠርጣሪዋን ጉዳይ በተለይ የሚከታተል የምርመራ ቡድን ተዋቅሮ አስፈላጊውን ተግባር እያከናወነ መሆኑ ተገልጿል።

በግድያው ተጠርጥራ የተያዘችው ግለሰብ እየተነገረ እንዳለው የቤት ሠራተኛ ሳትሆን የሟቾቹ ልጆች የእንጀራ እናት እንደነበረች ዋና ሳጅን ቀነኒሳ ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።

የልጆቹ አባት የሆኑት አቶ ጌታሁን ባልቻ በአካባቢው የሚገኝ ቄራ የሚሰሩ ሲሆኑ፣ ግድያው በተፈፀመበት ዕለት ማምሻውን ከባለቤታቸው ጋር በልጆቻቸው ጉዳይ ተነጋግረው እንደነበር ለቢቢሲ ገልጸዋል።

“በልጆቼ ጉዳይ ተነጋግረን ነበር። እንደዚህም ምክንያት እንለያይ ተባብለን፤ እርሷም ‘እኔ እሄዳለሁ፣ አንተ እዚህ ትኖራለህ’ አለችኝ” ሲሉ ለመጨረሻ ጊዜ የተነጋገሩትን ያስታውሳሉ።

ምሽት ሲነጋገሩ አቶ ጌታሁን ከባለቤታቸው ዛቻም ሆነ ለእንደዚህ አይነት አሰቃቂ ድርጊት ያበቃል ብለው የሚጠረጥሩት ጠቋሚ ነገር አለማየታቸውን ይናገራሉ።

አክለውም “ሌሊት ከዘጠኝ ሰዓት በኋላ ወደ ቤት ስመለስ የቤቱ በር ክፍት ነበር። ወደ ውስጥ ስገባ እሳት ይነዳል። ልጆቼን አልጋ ላይ ሳያቸው ጭሱ አፈነብኝ ብዬ ሮጬ ወደ ውጪ አወጣኋቸው። በወቅቱ ትልቁ ልጄ ተቃጥሏል። ትናሿ ልጄንም አወጣኋት። ወደ ውጪ ካወጣኋቸው በኋላ እነርሱ ላይ ወድቄ ራሴን ሳትኩኝ።”

በአሰቃቂ ሁኔታ የተገደሉት የአቶ ጌታሁን ልጆች አንደኛው የ13 ዓመት ወንድ ሲሆን፣ ሌላኛዋ ደግሞ የ4 ዓመት ተኩል ሴት ናቸው።

አቶ ጌታሁን በ2013 ዓ.ም የልጆቻቸውን እናት በሞት ካጡ በኋላ፣ ልጆች እንዳላቸው ተናግረው እና ተስማምተው ባለፈው ታኅሣሥ ወር ነበር ከተጠርጣሪዋ ጋር የተጋቡት።

ከእናታቸው ሞት በኋላ ልጆቹ አያታቸው ጋር የነበሩ ሲሆን፣ የአቶ ጌታሁን አባት ባለፈው ነሐሴ ማረፋቸውን ተከትሎ ልጆቹ ወደ አባታቸው ዘንድ መጥተዋል።

በሁለቱ ታዳጊዎች ላይ የተፈጸመው ድርጊት በርካቶችን ያሳዘነ ሲሆን፣ በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ መነጋገሪያ በመሆን ፖሊስ ያሰራጨው የተጠርጣሪዋ ፎቶ ግራፍ በስፋት ሲዘዋወር ነበር።