May 10, 2023 – EthiopianReporter.com

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የኢሠማኮ አመራሮችን እንዲያነጋግሩ ጥያቄ ቀረበላቸው

የኢትዮጵያ ሠራተኞች ማኅበራት ኮንፌዴሬሽን ኢሠማኮ አንገብጋቢ ባሏቸው የሠራተኞች ጥያቄዎች ላይ፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) የኮንፌዴሬሽኑን አመራሮች እንዲያነጋግሩ ጥያቄ አቀረበ፡፡

ኮንፌዴሬሽኑ በዘንድሮው የሜይ ዴይ በዓል ላይ በአደባባይ ሊያነሳቸው የነበሩ ጥቄያዎችን በማካተት ለጠቅላይ ሚኒስትሩ በጻፈው ደብዳቤ፣ እሳቸውን ማነጋገር ለሠራተኞች ጥያቄዎች ምላሽ ለማግኘት እንደሚረዳ አስታውቋል፡፡

በየጊዜው እያሻቀበ በመጣው የኑሮ ውድነት፣ የኢትዮጵያ ሠራተኞችና ቤተሰቦቻቸው መኖር የማይችሉበት ሁኔታ ውስጥ መሆናቸውን በደብዳቤው የጠቀሰው ኢሠማኮ፣ ‹‹ጠቅላይ ሚኒስትሩን ማግኘት ግድና ብቸኛው አማራጭ ሆኖ አግኝቼዋለሁ›› ብላል፡፡

ኢሠማኮ የሠራተኞች አንገብጋቢ የሚባሉ ጥያቄዎችን አስመልክቶ ከዚህ ቀደም በተለያዩ መንገዶች ለሚመለከታቸው መንግሥታዊ አካላት ጥያቄ ቢያቀርብም፣ ምላሽ ሊያገኝ አለመቻሉንም በደብዳቤው ጠቅሷል፡፡

ከዚህ ቀደም የሠራተኞች ጥያቄ የቀረበላቸው መንግሥታዊ አካላት ጥያቄውን ወደ ጎን የመግፋት አዝማሚያ እያሳዩ በመምጣታቸው፣ የኢሠማኮ አመራር ‹‹ጠቅላይ ሚኒስትሩ የአነጋግሩን›› ጥያቄ ለማቅረብ መገደዱን በደብዳቤው አስረድቷል፡፡

ምንጭ: ሪፖርተር ( https://www.ethiopianreporter.com/118442/