May 10, 2023

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ፤ የትግራይ ክልልን ጨምሮ 6ኛው አገራዊ ምርጫ ባልተካሄደባቸው አካባቢዎች እና አካባቢያዊ ምርጫን በ2016 ለማካሄድ መታቀዱን በዛሬው ዕለት አስታውቋል።

ቦርዱ ይህን ያሳወቀው የ2015 በጀት ዓመት ያለፉት 9 ወራት የዕቅድ አፈጻጸም ግምገማ ሪፖርት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ባቀረበበት ወቅት ሲሆን፤ የቦርዱ ምክትል ሰብሳቢ ውብሸት አየለ በተለያዩ ችግሮች ምክንያት በተወሰኑ ክልሎች በሚገኙ አካባቢዎች 6ኛው አገራዊ ምርጫ አለመካሄዱን ገልጸዋል።

ይህንኑ ምርጫ ለማካሄድ በ2015 ዝግጅት ለማድረግ ታቅዶ እንደነበርም ተናግረዋል።

ነገር ግን የአካባቢ ምርጫ ለማካሄድ ቢታቀድም አለመሳካቱን የገለጹት ምክትል ሰብሳቢው፤ እነዚህን ምርጫዎች በ2016 ለማካሄድ ቦርዱ ዕቅዱን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ማቅረቡን ተናግረዋል።

በሌላ በኩል፤ ባለፉት ወራት ከፖለቲካ ፓርቲዎች አሠራር ጋር በተያያዘ አንዳንድ ፓርቲዎች ጠቅላላ ጉባኤ እንዳያካሂዱ በተለያዩ አካላት መከልከላቸውን ቦርዱ ማረጋገጡን እና አንዳንድ የፓርቲ አመራሮች ለእስር መዳረጋቸውን ውብሸት ገልጸዋል። ቦርዱ ለዚህ ችግር መፍትሔ ለመስጠት ሥራዎችን እየሠራ እንደሚገኝም መግለጻቸውን ኢቢሲ ዘግቧል።