
ከ 4 ሰአት በፊት
የጥቁሮች በሕይወት የመኖር መብት እንዲከበር ለመጠየቅ አደባባይ ከወጡ ሰልፈኞች መካከል አንዱን ተኩሶ የገደለው የአሜሪካ ሠራዊት አባል የ25 ዓመት እስር ተፈረደበት።
የአሜሪካ ሠራዊት ሃምሳ አለቃ የሆነው የ36 ዓመቱ ዳንኤል ፔሪ ለተቃውሞ የወጣ ሰልፈኛን የገደለው ከሦስት ዓመት በፊት በአውሮፓውያኑ 2020 ነበር።
ወታደሩ ጋሬት ፎስተር የተባለው የ28 ዓመት ወጣትን ለህልፈት ባደረሰው ሁኔታ ተኩሶ የመታው ቴክሳስ ኦስቲን ውስጥ በተካሄደ ሰልፍ ላይ ነው።
ሟች እና ገዳይ ሁለቱም ነጭ አሜሪካውያን ሲሆኑ ፍርዱ የተለያዩ ሐሳቦች እየተሰነዘሩ ሲሆን፣ ገዳይ እርምጃውን የወሰደው እራሱ አደጋ ውስጥ በነበረበት ወቅት በመሆኑ ይቀርታ እንዲደረግለት የሚጠይቁ ወገኖችም አሉ።
የቴክሳስ ግዛት አገረ ገዢ የሆኑት ግሬግ አቦት ከፍርድ ቤቱ ውሳኔ ቀደም ብለው እንደተናገሩት፣ ይፋዊ ጥያቄ ሲቀርብ ወታደሩ ምህረት እንዲያገኝ አስፈላጊውን እንደሚያደርጉ ተናግረው ነበር።
የሪፐብሊካን ፓርቲ አባላት እና የሃምሳ አለቃው ጠበቆች ወታደሩ እርምጃውን የወሰደው እራስን በመከላከል ሂደት ውስጥ ነው ሲሉ ተከራክረዋል።
“ከሦስት ረጅም ዓመታት በኋላ በመጨረሻ ፍትሕ እያገኘን ነው” ሲሉ የሟች ጋሬት ፎስተር እናት ሼላ ፎስተር ለፍርድ ቤቱ መናገራቸውን አሶሺየትድ ፕሬስ ዘግቧል።
- በዙሪያችን ያሉ ነገሮች ሁሉ ከኢንተርኔት ጋር ሲተሳሰሩ ዓለም ምን ትመስላለች?ከ 5 ሰአት በፊት
- በኢትዮጵያ አካባቢ የሚበክሉ ትልልቅ ድርጅቶችን በራሱ ወጪ የሚከሰው ጠበቃ10 ግንቦት 2023
- በአሜሪካ ድብብቆሽ ስትጫወት የነበረች ታዳጊ ጭንቅላቷን በጥይት ተመታች10 ግንቦት 2023
የፍርድ ውሳኔው ይፋ የተደረገው ጉዳዩን ሲመለከት የነበሩት የዳኞች ቡድን ወታደሩ በወጣቱ ግድያ ጥፋተኛ መሆኑን በሙሉ ድምጽ ከወሰኑ ከአንድ ወር በኋላ ነው።
ዳኞቹ የሃምሳ አለቃውን ለሕይወት አደገኛ በሆነ መሳሪያ ጥቃት በመፈጸም የቀረበበትን ሌላኛውን ክስ ግን ውድቅ አድርገውታል።
በጥቁሮች ላይ የሚፈጸሙ ግድያዎችን እና የመብት ጥሰቶችን በመቃወም ሰልፎች በሚካሄዱበት ጊዜ የሃምሳ አለቃ ፔሪ በመኪናው ውስጥ ሆኖ ከተቃዋሚዎች ጋር ተገናኝቶ በተፈጠረ ፍጥጫ ወቅት ነበር ግድያው የተፈጸመው።
ፔሪ መኪናው ውስጥ ሆኖ ታጥቆ በነበረው ሟች ላይ በሽጉጥ አምስት ጊዜ ተኩሶ ከመታው በኋላ ከስፍራው አምልጧል። ነገር ግን ወዲያውኑ ለፖሊስ በመደወል የተፈጠረውን ሪፖርት ማድረጉ ተገልጿል።
ባለፈው ሚያዝያ ወር ጉዳዩን ሲመለከቱ የነበሩት ዳኞች ሃምሳ አለቃ ፔሪ ግድያውን በመፈጸም ጥፋተኛ መሆኑን ይፋ ማድረጋቸውን ተከትሎ የቴክሳስ አገረ ገዢ ግሬግ አቦት፣ በትዊተር ገጻቸው ላይ ለተከሳሹ ምህረት ለመስጠት ፈቃደኛ መሆናቸው አሳውቀዋል።
“የሃምሳ አለቃ ፔሪ ምህረት በፍጥነት እንዲያገኝ የቴክሳስ ግዛት ሕግ በሚያዘው መሠረት አስፈላጊውን ሁሉ እያደረግኩ ነው” ብለዋል አስተዳዳሪው።
ነገር ግን የወታደሩን የምህረት ጉዳይን ለማጽደቅ የቴክሳስ ግዛት የይቅርታ ቦርድ ጥያቄው ከቀረበለት በኋላ ወዲያውኑ ምርመራውን ማድረግ ይጀምራል ተብሏል።
የተከሳሹ ይቅርታ እንዲደረግለት የሚደግፉ ሰዎች በቴክሳስ ግዛት ሕግ ውስጥ ያለውን በአደጋ ጊዜ እራስን በአስፈላጊው ነገር ሁሉ የመከላከል ፈቃድ በመጥቀስ ግለሰቡ ግድያውን የፈጸመው አደጋ ውስጥ በነበረበት ጊዜ ነው ይላሉ።
በግዛቱ ሕግ ውስጥ አንድ ሰው በተፈቀደለት ስፍራ ውስጥ ሆኖ በሕይወቱ ላይ አደጋን የሚያስከትል ስጋት ከገጠመው አስፈላጊውን እርምጃ በመውሰድ የመሸሽ መብትን የሚሰጥ ነው።
