
ከ 2 ሰአት በፊት
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት በሱዳን ተፋፍሞ በቀጠለው ጦርነት ላይ ለመወያያት አስቸኳይ ስብሰባ ጠራ።
ምክር ቤቱ ዛሬ ግንቦት 11/ 2015 ዓ.ም በስዊዘርላንድ ጄነቫ ይወያያል።
ለሶስት ሳምንታት ያህል በቀጠለው ውጊያ በሰላማዊ ሰዎች የሰብዓዊ መብት ረገጣዎች፣ ጥቃቶች መደፈሮችና የሆስፒታል ላይ ዘረፋዎች ስለመፈጸማቸው ሪፖርቶች ወጥተዋል።
በዚህ ከባድ ውጊያ በመቶዎች የሚቆጠሩ ዜጎች የተገደሉ ሲሆን ወደ 450 ሺህ የሚጠጉ ነዋሪዎችም ቀያቸውን ጥለው ተፈናቅለዋል።
ከነዚህም ውስጥ ከ115 ሺህ በላይ የሚሆኑት ወደ ጎረቤት ሃገራት እንደተሰደዱም ከተመድ የዓለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት የተገኘው መረጃ ያሳያል።
ሱዳንን ጨምሮ በርካታ የአፍሪካ ሀገራት እየተካሄደ ያለውን የተኩስ አቁም ድርድር አደጋ ላይ ሊጥል ይችላል በሚል ስጋት የተመድን አስቸኳይ ስብሰባ ቸል ማለታቸው ተዘግቧል።
ይህ ስብሰባ የተጠራው በብሪታንያ፣ በአሜሪካ፣ በጀርመን እና በኖርዌይ ነው።
የሱዳን ጦርና የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ በሳዑዲ አረቢያዋ ከተማ ጅዳ እያደረጉት ያለው ንግግር አምስተኛ ቀኑን ቢያስቆጥርም ስለተደረሰበት ሁኔታ ዝርዝር መረጃዎች እየወጡ አይደለም።
በሁለቱ ኃያላን ጦሮች መካከል እየተደረገ ያለውንም የሽምግልና ሂደት ሳዑዲ አረቢያና አሜሪካ በጋራ እየመሩት ይገኛሉ።
- ያለ እውነተኛ የተኩስ አቁም ንግግሮች ፍሬ አልባ ናቸው- ጄነራል አል ቡርሃን9 ግንቦት 2023
- የሱዳን ተፋላሚ ኃይሎች በሳዑዲ አረቢያ ንግግር ሊያደርጉ ነው6 ግንቦት 2023
- ከሱዳን በመሸሽ ወደ መተማ የገቡ የተለያዩ አገራት ዜጎች ቁጥር ከ12 ሺህ በላይ ደረሰ7 ግንቦት 2023
ሚያዝያ 28/ 2015 ዓ.ም በጅዳ የተጀመረው የቅድመ ድርድር የሰላም ንግግር ምንም አይነት እድገት እንዳላሳየ አንድ የሳዑዲ ዲፕሎማት ለአጃንስ ፍራንስ ፕሬስ የዜና ወኪል ተናግረዋል።
የአሜሪካ እና የሳዑዲ አረቢያ መንግሥታት “ሁለቱም ተፋላሚ ወገኖች ለአገሪቷ እና ለሱዳን ሕዝብ ጥቅም ቅድሚያ በመስጠት ግጭቱን ለማስቆም በሚደረገው ውይይት ላይ በንቃት እንዲሳተፉ፤ ይህም ሁኔታ ለተቸገረው ሕዝብ የሰብዓዊ እርዳታ እንዲደርስ የሚያረጋግጥና የሱዳንን ሕዝብ ስቃይና መከራ የሚታደግ መሆኑን” አሳስበዋል።
የሱዳን ግጭት ሚያዝያ 7/ 2015 ዓ.ም ከተቀሰቀሰበት ጀምሮ በርካታ የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ ቢደረስም ሁለቱም ኃይሎች ተፈጻሚ ሊያደርጉት አልቻሉም።
የሚሊዮኖች ሕይወት ስጋት ውስጥ በገባበት በዚህ ግጭት መሃል ሁለት ጄኔራሎች በባላንጣነት በጽንፍ ስፍራ ተቀምጠዋል።
የሱዳን ጦር ኃይል አዛዥና አገሪቷን እያስተዳደሩ ያሉት አብደል ፈታህ አል ቡርሃን ከፈጥኖ ደራሽ ልዩ ኃይሉ መሪ ጄነራል መሃመድ ሃምዳን ዳጋሎ ወይም ሄምቲ ጋር በመረረ የስልጣን ሽኩቻ ውስጥ ገብተዋል።
