
ከ 4 ሰአት በፊት
ዩክሬን ወደ ተለያዩ አገራት ስንዴ እንድትል ከተደረሰው ስምምነት ሩሲያ የምትወጣ ከሆነ አገራትን ለመመገብ አስቸጋሪ እንደሚሆን የዓለም ምግብ ፕሮግራም ገለጸ።
የዓለም ምግብ ፕሮግራም ኃላፊት ሲድኒ ማኬን ለቢቢሲ እንደገለጹት፣ እአአ ግንቦት 18/2023 የስምምነቱ የመጨረሻ ቀን ሲሆን፣ ሩሲያ ስምምነቱን የማታድስ ከሆነ አገራትን ለመመገብ ይቸገራሉ።
ሩሲያ እና ዩክሬን የደረሱበት የስንዴ ስምምነት ከዩክሬን በሚሊዮኖች የሚቆጠር ቶን ስንዴ ከአገሪቱ እንዲወጣ አስችሏል።
አምና ሐምሌ ላይ በተባበሩት መንግሥታት እና በቱርክ አማካይነት ነው ይህ ስምምነቱ የተፈረመው።
የዩክሬን የጥቁር ባሕር መስመር በሩሲያ ተዋጊዎች ከተዘጋ በኋላ በዓለም ሊፈጠር የሚችለውን የምግብ ቀውስ ከግምት በማስገባት ነበር ስምምነት ላይ እንዲደረስ የተደረገው።
ዩክሬን ሱፍ፣ ስንዴ፣ በቆሎ እና ገብስን ጨምሮ የሌሎች ጥራጥሬዎች ዋነኛ አምራች እና ዓለም አቀፍ አከፋፋይ አገር ስትሆን፣ የዓለም ምግብ ፕሮግራም አምና ከገዛው ስንዴ ግማሹ የዩክሬን ነው።
ሲድኒ ማኬን “ሩሲያ ስምምነቱን ማደስ አለባት። ስምምነቱን ካልታደሰ እንኳንስ ዓለምን ቀጠናውን መመገብ አንችልም” ብለዋል።
“ዩክሬን የአውሮፓ ቁርስ አቅራቢ ነበረች። አሁን ተቋርጧል። ሌሎች አገራት ላይም ተጽዕኖ አሳድሯል” ሲሉም አክለዋል።
ስምምነቱ ለ120 ቀናት ሊራዘም ይችላል ቢባልም ሩሲያ ስምምነቱን ለማቋረጥ ስትዝት ነበር። ሩሲያ ለዚህ ምክንያት ያለችው የምግብ እህል እና የማዳበሪያ ኤክስፖርት ላይ መሰናክል መፈጠሩን ነው።
- የዝንጀሮ ፈንጣጣ በሽታ አጣዳፊ ዓለም አቀፍ ስጋት መሆኑ አበቃከ 5 ሰአት በፊት
- መንግሥትን እና የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊትን ያገናኘችው ታሪካዊቷ ዛንዚባርከ 5 ሰአት በፊት
- ትምህርት በተጀመረባት ትግራይ ጠፍጣፋ ድንጋይ በመጠቀም እያስተማሩ ያሉት መምህርከ 5 ሰአት በፊት
ባለፈው ሳምንት የሩሲያ፣ ዩክሬን፣ ቱርክ እና የተባበሩት መንግሥታት ወኪሎች ኢስታንቡል ውስጥ ስምምነቱን ለማደስ ውይይት አድርገዋል።
ሩሲያ ሳትስማማ ውይይቱ ተጠናቋል።
ስምምነቱን ማደስን በተመለከተ የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ከቱርኩ ፕሬዝዳንት ረሲፕ ታይፕ ኤርዶዋን ጋር መነጋገር እንደሚችሉ ቢገለጽም እስካሁን የተባለ ነገር የለም።
ሲድኒ ማኬን እንዳሉት፣ የዓለም ምግብ ፕሮግራም ከሌሎች ምንጮች የምግብ እህል በመግዛት በመላው ዓለም እያከፋፈለ ቢሆንም በኑሮ ውድነት ሳቢያ በርካታ ሰዎችን መመገብ እንዳልቻለ ገልጿል።
“ግጭቱ በመላው ዓለም ሰዎችን እንዳንመግብ እንቅፋት ሆኗል” ይላሉ።
ዘንድሮ የዩክሬን አርሶ አደሮች ምርት ለመሰብሰብ እንደሚቸገሩም ገልጸዋል።
“አሁንም የሚያመርቱ የተወሰኑ የእርሻ መሬቶች አሉ። ሆኖም በብዛት ሰብል ይበቅልባቸው የነበሩ መሬቶች አሁን ቦምብ ተቀብሮባቸዋል” ብለዋል።
ጦርነቱ ቢያከትም እንኳን መሬቱን ከቦምብ አጽድቶ ግብርና ለመጀመር ዓመታት እንደሚወስድም ገልጸዋል።
ሩሲያ ስምምነቱን እንደምትፈርም እርግጠኛ እንዳልሆኑ ሲገልጹም “እርግጠኛ አይደለሁም። 50/50 ዕድል ነው ያለው። በጣም አስግቶኛል። ይህ ሁላችንንም ሊያስጨንቀን ይገባል” ብለዋል።
የቱርክ መከላከያ ሚኒስቴር በስምምነቱ ላይ ተጨማሪ ውይይት የማድረግ ተስፋ እንዳለ ገልጿል።
የዩክሬን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ኦልኪሳንሰር ኩብራኮቭ ንግግሩ በበይነ መረብ ሊቀጥል እንደሚችል ተናግረዋል።
ሩሲያ ስምምነቱን ለማደስ ካቀረበቻቸው ቅድመ ሁኔታዎች አንዱ የግብርና ምርቶቿ ኤክስፖርት የሚደረጉበት መንገድ መመቻቸት ነው።
