May 12, 2023 – BBC Amharic

በስቶን ታውን እየተራመደች ያለች ግለሰብ
የምስሉ መግለጫ,ጥንታዊቷ የስቶን ታውን ከተማ

ከ 5 ሰአት በፊት

በዛንዚባሯ ደሴት መዲና ታሪካዊቷ ስቶን ታውን ኮፍያቸውን ያጠለቁ ሙስሊም ሽማግሌዎች የሚያፈሉት ቡና መዓዛ በሩቅ ይጣራል።

ቡናቸውን በቀረፋ፣ ቅርንፉድ እና ዝንጅብል ቅመሞች በመቀመምም ካፈሉ በኋላ ከባልዲያቸው ሲኒ እያወጡ በሲኒዎች ቡናውን በአገሬው አጠራር ‘ካዋ’ ያድላሉ።

ሲኒዎቹ በሚያስገርም ሁኔታ ከኢትዮጵያ ጋርም ተመሳሳይ ናቸው። ሲኒው ብቻ ሳይሆን ዛንዚባራውያን “ሰውን ሰው ያደረገው ዕቁብ ነው” ይላሉ።

በስቶን ታውን ‘ጆስ ኮርነር’ በምትገኘው ደረጃ ላይ የተቀመጡ ሙስሊም ወንዶች፣ ሼሆች ቡናቸውን ያጣጥማሉ።

የአረብ ሱልጣኖች መናገሻ፣ የፋርስ፣ የሕንድ፣ የአውሮፓ እና የአፍሪካ ሥልጣኔዎችን ባዋሃደችው የባሕር ዳርቻዋ የዛንዚባር የድንጋይዋ ከተማ የእንግድነት ስሜት የለም። አላፊ አግዳሚው ሰው ለመሆዎን እውቅና በመስጠት ፈገግ ብሎ ያቀበልዎታል።

ይዘይርዎታል። ከየት እንደመጡ ታሪክዎትን ይጠይቃል።

በታሪካዊቷ የድንጋይ ከተማ (ስቶን ታውን) በእግራችን ስንረማመድም አንድ ጠና ያሉ ሼህ “እንኳን ከአቢሲኒያ በሰላም መጣችሁ አሉን?”

ቆም ብለውም በፈግታ “አቢሲኒያ እንዴት ናት?” ብለው ጠየቁን።

ስለ ሰሜኑ ጦርነት ጠቀሱልን፤ “ጊዜ ይቀየራል፤ አቢሲኒያ ታላቅ ናት” አሉን።

በውጭ አገራት የታሪክ ተመራማሪዎች ዘንድ አቢሲኒያ እየተባለች የምትጠራው ኢትዮጵያ ከጥንቷ ዛንዚባር ጋር ግንኙነት ይኖራት ይሆን?

ለዘጠኝ ቀናት ባደረግነው የዛንዚባር ቆይታችንም በተደጋጋሚ ኢትዮጵያን አቢሲኒያ እያሉ ሲጠሯትም ሰምተናል። ንጉሥ የሚባለው የአቢሲኒያ ስያሜ በዛንዚባር እንደሚታወቅና ነጃሺ እንደሚባሉ ሌላ መንገደኛም አጫወቱን።

በየመን ቢልቂስ በመባል የምትታወቀው ንግሥት ሳባም የአቢሲኒያ መሠረት እንዳላት የስቶን ታውን ነዋሪ ነግረውናል። የጥንቷ አቢሲኒያ ግዛት እስከ ዛንዚባር እና ሕንድ ውቅያኖስ እንደሚደርስ በአፈታሪክ ሲነገርም በተደጋጋሚ ቢሰማም ይህ ነው የሚባል የታሪክ ማጣቀሻ አላገኘንም።

በስቶን ታውን ‘ጆስ ኮርነር’ ቡና እየጠጡ ያሉ የእድሜ ባለጸጋ
የምስሉ መግለጫ,በስቶን ታውን ‘ጆስ ኮርነር’ ቡና እየጠጡ ያሉ የእድሜ ባለጸጋ

አቢሲኒያ እንዴት ናት ወዳሉን እንመለስና ከኬንያ ናይሮቢ ለዘገባ እንደመጣን ነገርናቸው።

የቢቢሲ ጋዜጠኞች ከናይሮቢ ወደ ዛንዚባር የመጣነውም የኢትዮጵያ ፌደራል መንግሥት እና የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊትን ታሪካዊ ንግግርን ለመዘገብ ነበር።

ተደራዳሪዎቹ ከኢትዮጵያ የ3 ሰዓት 42 ደቂቃ የአየር መንገድ ርቀት ያላትን በተፈጥሮ እና በታሪክ የታደለችውን ዛንዚባር ነው ለመጀመሪያ ጊዜ ፊት ለፊት ተቀምጠው ግጭታቸውን በሰላም ለመቋጨት ለውይይት የመረጧት።

ከመንግሥትም ሆነ ከኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት በኩል ታንዛንያ የትኛዋ ከተማ እንደሚካሄድ መረጃ ባይሰጥም ራስ ገዝ አስተዳደር በሆነችው ዛንዚባር ላይ ንግግሩ እንደሚካሄድ ሰምተን ሚያዝያ 18/2015 አቀናን።

ዛንዚባር ለመድረስ በርካታ ኢትዮጵያውያን የሚያጋጥማቸውን የቪዛ ጥያቄ እና የጉዞ መስተጓጎል በዚህ ጽሁፍ ላይ ወደ ኋላ መለስ ብለን የምናየው ይሆናል።

እስከ መጨረሻዋ ሰዓት ድረስ በከፍተኛ ምስጢርነት የተያዘው ይህ ውይይትም በዛንዚባር የት እየተካሄደ እንደሆነ ለማወቅ ቀናትን ፈጅቶብናል።

የድርድሩ ስፍራ - ኤመራልድ
የምስሉ መግለጫ,የድርድሩ ስፍራ – ኤመራልድ

የድርድሩ ስፍራ – ኤመራልድ

በኬንያ እና በኖርዌይ አቀራራቢነት እየተካሄደ የነበረው ውይይት በሰሜናዊ ምሥራቅ ዛንዚባር በምትገኘው ሙዩኒ የባሕር ዳርቻ ላይ በሚገኘው ኤምራልድ ሪዞርት እና ስፓ እንደሆነ ሰማን።

ኤምራልድ በምሥራቅ አፍሪካ እና በሕንድ ውቅያኖስ ውስጥ ያሉ የቅንጦት እና የመዝናኛ ሆቴሎች ስብሰብ ውስጥ ከሆነው አንዱ ሲሆን፣ በመስተንግዶ ኢንዱስትሪ ውስጥ ከ40 ዓመታት በላይ ልምድ ባለው በጣሊያኑ ስካራፒቺያ ቤተሰብ ነው የሚተዳደረው።

ኤመራልድ በዛንዚባር አስደናቂ ከሆነው የሙዩኒ የባሕር ዳርቻ በአንዱ አጠገብ ተንጣሎ ይታያል።

በርካታ ቱሪስቶች በጀልባ የሕንድ ውቅያኖስ አካል የሆነውን ደሴት ለማቋረጥ፣ ደሴቱን የሚከፍለውን ነጭ አሸዋ ለመመልከት፣ በጥልቀት ለመዋኘት እና ብርቅዬ የሆኑትን ሰማያዊ አሳዎችም ለማየት ይጎርፋሉ።

በውይይቱ ለመሳተፍም ሆነ ተሳታፊዎችን ለማግኘት ዕድሉ አልነበረም። ከመዲናዋ ስቶን ታውን በ40 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይም ከሚገኘው ኤመራልድ ሪዞርት ኤንድ ስፓ ከሚገኝበት ሙዩኒ አጠገብም ሌላ ምኔባ የምትባል ደሴት ትገኛለች።

በስቶን ታውን የቢቢሲ ዘጋቢዎች ያገኙት በባሕር ዳርቻዎች ላይ የእግር ኳስ ውድድር (ቢች ፉት ቦል) የሚያዘጋጀው ላጢፍ ምኔባ “ይህ የማን ደሴት እንደሆነ ታውቂያለሽ?” ሲል ጠየቀኝ። በጥያቄ ዐይን ስመለከተውም “በዓለም ቱጃር የሆነው የቢል ጌትስ ደሴት ነው” አለኝ።

በዛንዚባር ቢል ጌትስ የራሱ ደሴት አለው?

ምኔባ የተሰኘችው ደሴት የግል ስትሆን ኤንድ ቢዮንድ የተሰኘ ቅንጡ ሪዞርት ይገኛል።

ወደ ደሴቲቱ እንደፈለጉ ዘሎ መግባት አይቻልም፤ የሪዞርቱ እንግዶች ወይንም በአስጎብኝዎች ከመጡ ብቻ ነው።

ቢል ጌትስም ሆነ ሌሎች ታዋቂ ቱጃሮች ደሴቶቹን በሊዝ እንደተከራዩዋቸው ቢነገርም ቢቢሲ ማረጋገጥ አልቻለም። በዛንዚባር ቆይታችን ምኔባ የተሰኘችው ደሴትን ቢል ጌትስ በሊዝ መከራየቱን ከበርካቶች ሰምተናል።

ምኔባ በርካቶች ከዶልፊን ጋር የሚዋኙበት እንዲሁም በጥልቀት ለመዋኘት የሚያስችለውን የመተንፈሻ መሳሪያ ገጥመው በሕንድ ውቅያኖስ ላይ የሚዋኙበት ነው።

ቢል ጌትስ በሊዝ ተከራይቷታል የምትባለው ምኔባ አይላንድ
የምስሉ መግለጫ,ቢል ጌትስ በሊዝ ተከራይቷታል የምትባለው ምኔባ አይላንድ

ዛንዚባር ቱምባቱ፣ ኑንግዊ እና ኬንድዋ የሚባሉ ደሴቶች እና ምድራዊ ገነት የሚመስሉ የባሕር ዳርቻዎች አሏት።

እነዚህ ደሴቶች በአሁኑ ወቅት በየዓመቱ ግማሽ ሚሊዮን የሚሆኑ ቱሪስቶችን የሳቡ ቢሆንም፣ በርካቶቹ የምሥራቅ አፍሪካ ባሪያዎችን ለማስቀመጥ፣ ለማሰር እና በሕንድ ውቅያኖስንም አሻግሮ ለመሸጥ እና ለመለወጥ ዋነኛ ማዕከላት ነበሩ።

በእነዚህ ደሴቶች ባሪያዎችን በማጋዝ የሚታወቁት ፖርቹጋልን በማሸነፍ ዛንዚባርን የተቆጣጠሩት የኦማን አረቦች ናቸው። የኦማን አረቦች መናገሻ እና መዲናቸውም ጥንታዊቷ የድንጋይ ከተማ – ስቶን ታውን ናት።

ጥንታዊቷ የስቶን ታውን ከተማ
የምስሉ መግለጫ,ጥንታዊቷ የስቶን ታውን ከተማ

ጥንታዊቷ የድንጋይ ከተማ

በአረብኛ ማዲናት ዛንጂባር አል ሃራያ፣ በስዋሂሊ ምጂ ኮንግዌ ይሏታል – የዛንዚባሯን መዲና ስቶን ታውንን።

የድንጋይዋ ከተማ፣ የባሕር ዳርቻዋ መናገሻ የአረብ፣ የፋርስ፣ የሕንድ፣ የአውሮፓ፣ የአፍሪካ የኪነ ህንጻ አሻራዎች ይታዩባታል።

ኮራል በተሰኘው ድንቅ ድንጋይ የተገነባችው ስቶን ታውን ያለፈችባቸውን የምዕተ ዓመታት ታሪክን ግልጽ አድርጋ ታሳያለች።

በአምስት መቶ ዓመታት የተሰሩት ጥንታዊ የሱልጣኖች መናፈሻዎች፣ ቤተ መንግሥቶች፣ የባርያ መሸጫዎች እና ማሰቃያዎች፣ የጦር ምሽጎች መነካትም ሆነ ማፍረስ ጥብቅ ትዕዛዝ በመውጣቱ ጊዜ የቆመ ይመስላል።

ትልልቅ የጣውላ በሮቿ በብር እና በመዳብ አሁንም እንዳጌጡ ነው። በበሮቹ ላይ የሕንድ እና የአረብን ኪነ ጥበብ መራቀቅ የሚያሳዩ የቁርዓን ጥቅሶች እና አበባዎች ተቀርጸዋል። እንዲሁም በበሮቹ ላይ ከነሐስ የተሰሩ ጉጥ መሳይ የተገጠመላቸው ሲሆን ይህም ዝሆንን ለመከላከል እንደሆነም የአካባቢው አስጎብኚዎች ይናገራሉ።

በኪነ ህንጻዋ ብቻ ሳይሆን ነዋሪዎቿም የአረብ፣ የሕንድ፣ የፋርስ፣ የአውሮፓ እና የአፍሪካ ውህድ ማንነት ይዘዋል።

በስቶን ታውን ፎሮታኒ አካባቢ የሚገኙ ሆቴሎች

መኪና በማያሳልፉ ጠባብ መንገዶች ሲረመማዱ በታሪክ ወደ ኋላ የተመለሱ ይመስላል። በየሰዓቱም ከየመስጊዱ የሚወጡት በመወረዋ ድምጽ የሚወጡት አዛኖች ልብን ያማልላሉ።

ስቶን ታውን ያላት ኪነ ህንፃም ሆነ የታሪክ አሻራ የሚያስደምም ቢሆን በጨለማም ታሪክ የተሞላ ነው። በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ባሪያዎችም ተገብረውባታል።

ስቶን ታውን በዓለም አቀፍ ደረጃም የመጨረሻዋ ክፍት የባሪያ ገበያዎች አንዷ ነበረች። ብሪታንያን ጨምሮ አውሮፓውያኑ ባሪያን እንደ እቃ መሸጥ እና መለወጥ ካቆሙ በኋላም ቢሆን እስከ አውሮፓውያኑ 1873 ድረስ ክፍት ነበር።

ጥንታዊቷ የስቶን ታውን ከተማ

ባሪያዎቹ ሜይን ላንድ (ዋና ምድር) ተብሎ ከሚጠራው ከታንዛንያ እና ከሌሎች የምሥራቅ አፍሪካ አገራት ታጭቀው ይመጣሉ። በጉዞም ላይ የሚታመሙ እና ሰምጠው ውሃ የሚባላቸው በርካቶች ነበሩ።

በአሁኑ ወቅት የእንግዶች ማረፊያ በሆነው ሴንት ሞኒካም በርካታ ሴቶች እና ህጻናት ምንም አየር እንዲሁም መጸዳጃ በሌለበት ሁኔታም ታጉረው ይጋዙ ነበር።

ስቶን ታውንን ያስጎበኘን ኦማር እንደነገረን ባሪያዎቹ ወደ ውጭ ወጥተው በአካል መጠናቸው እንዲሰለፉ ይደረጋሉ። ጥንካሬያቸውንም ለመፈተሽም ከዛፍ ላይ ታስረው ደም በደም እስኪሆኑ ይገረፋሉ።

ያላለቀሱ ወይንም ራሳቸውን ስተው ያልወደቁ ዋጋቸው ከፍ ባለ ሁኔታ ለሽያጭ ይቀርባሉ።

የባሮች ክፍት ገበያ በነበረው ስፍራ የአንግሊካን ካቴድራል የክርስቶስ ቤተክርስቲያን
የምስሉ መግለጫ,የባሮች ክፍት ገበያ በነበረው ስፍራ የአንግሊካን ካቴድራል የክርስቶስ ቤተክርስቲያን

በአሁኑ ወቅት ይህ የባሮች ክፍት ገበያ በነበረው ስፍራ የአንግሊካን ካቴድራል የክርስቶስ ቤተክርስቲያን (ክራይስት ቸርች) ቆሟል። የመግረፊያው ቦታም መሰዊያ በሚመስለው የቤተ ክርስቲያኑ በኩል የባሪያዎቹን ደም ለማመልከት ቀይ ቀለም ተቀብቶ በነጭ እምነበረድ ተከቧል።

በአፍሪካ ውስጥ በሚሲዮን መልዕክተኛነቱ የሚጠቀሰውን የስኮትላንዱ ዴቪድ ሊቪንግስተንንም ይህ ስፍራ ይዘክረዋል። ሕይወቱ በዛምቢያ ካለፈ በኋላ አስከሬኑ ወደ ትውልድ መንደሩ ቢላክም ልቡ በአንድ መንደር ተቀበረ።

ልቡ በተቀበረበትም ስፍራ በበቀለ ዛፍ የተሰራ መስቀልም በቤተ ክርስቲያኑ እንደተሰቀለ አስጎብኚያችን ኦማር ነገረን።

በርካታ ቱሪስቶች ከሚጎበኙት ይህ ስፍራ ውጪም የባሪያዎችን ስቃይ የሚያሳይ በካቴና እና በሰንሰለት የተጠፈሩ ሃውልቶች ይታያሉ።

የባሮች ክፍት ገበያ የባሪያዎችን ስቃይ የሚያሳይ በካቴና እና በሰንሰለት የተጠፈሩ ሃውልቶች
የምስሉ መግለጫ,የባሮች ክፍት ገበያ የባሪያዎችን ስቃይ የሚያሳይ በካቴና እና በሰንሰለት የተጠፈሩ ሃውልቶች

በስቶን ታውን ሌላኛዎቹ ታሪካዎቹ ስፍራዎች የሱልጣኖች ቤተ መንግሥት የነበረው ‘ፓላስ ሙዝየም’፣ እንደ የጦር ሰፈር ወይም ሱልጣኖች ምሽግነት የሚጠቀሙበት ኦልድ ፎርት እንዲሁም በዛንዚባር የመጀመሪያው ኤሌክትሪክ የገባለትና በምስራቅ አፍሪካ አሳንሰር የተገጠመለት ሃውስ ኦፍ ዋንደርስ ቤተ መንግሥት ተጠቃሽ ናቸው።

እንደ የጦር ሰፈር ወይም ሱልጣኖች ምሽግነት የሚጠቀሙበት ኦልድ ፎርት
የምስሉ መግለጫ,እንደ የጦር ሰፈር ወይም ሱልጣኖች ምሽግነት የሚጠቀሙበት ኦልድ ፎርት

ደማቁን የኢድ በዓል በፎሮዳኒ ፓርክ

ስለ ስቶን ታውን ስናወራ በሕንድ ውቅያኖስ ስለተከበበችው ፎሮዳኒ ፓርክ ወይም የአትክልት ስፍራ አለመጥቀስ አይቻልም።

ዛንዚባር የደረስነው በአምስተኛዋ የኢድ በዓል ዕለት ነበር።

ምንም እንኳን 55 ሚሊዮን የሚሆነው የታንዛንያ አብዛኛው ሕዝብ ክርስቲያን ቢሆንም፣ 1.3 ሚሊዮን የሚጠጉት የዛንዚባር ነዋሪዎች ሙሉ በሙሉ ሙስሊሞች ናቸው።

እንደ ዕድል ሆኖ በዓመቱ ትልቅ ክብረ በዓል በሆነው እና የዛንዚባር ሕዝብ በፈንጠዝያ በሚሞላበት የኢድ አል ፈጥር በዓል አካባቢ ነው የደረስነው። በዛንዚባር የኢድ በዓል ለአምስት ተከታታይ ቀናት ነው የሚከበረው።

በታንዛንያ የሚገኙት የቢቢሲ ጋዜጠኞችም ወደዚህች ስፍራ ዕራት እንድንበላ እና እንድናይ ጋበዙን።

በኢድ በመጀመሪያው ቀን ህጻናት ከቤት ቤት እየዞሩ በር እያንኳኩ ገንዘብ ይጠይቃሉ፤ ምናልባትም ከቡሄ ወይም ከአሸንዳ ባህል ጋር ተመሳሳይ ይመስላል።

ህፃናቱ ነጭ ካንዙ የተሰኘ ቀሚስ ለብሰው ኮፍያቸውንም አጥልቀው ይዞራሉ። የኢድ ገንዘብም ይበረከትላቸዋል። ሁሉም ቤተሰቦች ለህፃናቱ ገንዘብ መስጠት የባህሉ አካል እንደሆነ ላጢፍ ነገረን።

በስቶን ታውን ፎሮዳኒ አካባቢ የሚገኙ ሆቴሎች
የምስሉ መግለጫ,በስቶን ታውን ፎሮዳኒ አካባቢ የሚገኙ ሆቴሎች

ከተማዋ በርችት ትደምቃለች። የከተማው ሁሉ ሰው ውጭ ያለ በሚመስል ሁኔታ በጠባቦቹ የስቶን ታውን መንገዶች አዳዲስ መኪኖች ጥሩምባቸውን እየነፉ፣ በፒክ አፕ መኪኖች የተጫኑ ሙስሊሞች በሳቅ እና በደስታ መንገዱን አጥለቅልቀውታል።

ህጸናት እጅ ለእጅ ተያይዘው ምግብ ያማርጣሉ። በርካታ እህት እና ወንድማቾች ሰብሰብ ብለው ታዋቂ ከሆነው እና ቱሪስቶች ከሚበዙት ኬፕታውን ፊሽ ማርኬት የሚወጣውን ሙዚቃ እየሰሙ፣ በህንድ ውቅያኖስ በተከከበበችው፣ በጀልባዎች እና በመርከቦች በታጀበችው ፎሮታኒ ፓርክ በዓሉን ያከብራሉ።

ትልቅ ስፍራን በሚሸፍነው ፎሮታኒ ፓርክ ከሚበስለው ምግብ የሚወጣው ጭስ ምራቅ ያስውጣል። የሚጠበስ አክቶፐስ ከካሳቫ ጋር፣ በዝንጅብል የታጠበ የሥጋ ጥብስ፣ ታዋቂው እና የእንቁላል ኦምሌት የሚመስለው የዛንዚባር ፒዛ፣ ዋሊ ና ማሃራጌ (ባቄላ ሩዝ ከኮናት ጋር ተቀላቅሎ)፣ ሺሽ ክበብ የሚመስለው በቅመም ያበደው ሚሽካኪ፣ ጣፋጭ ከፈለጉ ደግሞ ዶናት መሳዩ ቪቱምባ ተሞልቷል።

በፎሮዳኒ  ጋርደን ያለው የምግብ ሽያጭ

ትንሽ በፓርኩ ውስጥ ተረማምደን ከምግብ ምግብ እያማረጥን ቺክን ሺዋርማ ወስደን እንዲሁም የሸንኮራ አገዳ ጭማቂ ከሚንት ጋር የተቀላቀለ የሚጠጣ ይዘን በባሕር ዳሩ ቁጭ አልን። የእነዚህ ትንንሽ የጎዳና ላይ ሬስቶራንቶች ምግብ ቸርቻሪዎች ገንዘብ አይጠይቁም፤ በእምነት ዝም ብለውን ነው የሚሰጡት።

የቢቢሲው የታንዛንያ ባልደረባችን ምግቡን አጣጥማችሁ ከበላችሁ በኋላ ተዝናንታችሁ ስትጨርሱ መጥታችሁ እንደምትከፍሉ ያውቃሉ አለን።

ለእኛ ብቻ ሳይሆን ለሌሎቹም ዛንዚባራውያን በፎሮታኒ ያሉ ክፍት ሬስቶራንቶች ገንዘብ መጀመሪያ አይጠይቁም። እየተገረምን በአካባቢው እየዘለሉ በሕንድ ውቅያኖስ የሚዋኙ ወጣቶችን እየተመለከትን በባሕሩ ድምጽ፣ በኢድ መንፈስ እና በዛንዚባራውያን የሚጋባ ደስታ እና በመርከቦች እና ጀልባዎች ድምጽ ታጅበን ምግባችንን አጣጣምን።

ዛንዚባራውያን አላፊ እና አግዳሚውን ሰላም እንዳሉ ነው። እንዲሁ መንገድ ላይ የሚያዋራችሁ ሰውም አታጡም። ትህትናቸውም ለየት ያለ ነው።

የቢቢሲው ባልደረባችንም ቀልድና ቁም ነገር በታጀበ መልኩ ፖሊሶች ወንጀለኛን በቁጥጥር ስር ሲያውሉ “እባክህ እጅህን በካቴና እንሰረው?” ብለው ጠይቀው ነው አለን። ባልደረባችን ቀልድ እንዳልሆነ ነገረን። እንግዲህ ይሁን አልን።

ለትህትናቸው፣ ቀለል ማለታቸው፣ ሁሉን ነገር ረጋ ባለ ሁኔታ ስለማከናወናቸው ለሰላምተኝነታቸው ብዙም ርቀን መሄድ አላስፈለገንም፤ ለሰውነታችሁ እውቅና የሚሰጣችሁ ሕዝብ እና ስፍራ ነው ዛንዚባር።

ፎሮዳኒ
የምስሉ መግለጫ,ፎሮዳኒ

ቢች ቦይስ በዛንዚባር

ቱሪስቶች እንደሚጎበኟቸው ሌሎች የባሕር ዳርቻዎች የወሲብ ንግድ በዛንዚባር በከፍተኛ ሁኔታ የተዛመተ ነው።

በተለይም ቱሪስቶች በሚያዘወትሯቸው ደሴቶች እንዲሁም በስቶን ታውን ታዳጊ ወንዶችን ከነጭ ሴቶች ጋር ማየት የተለመደ ነው። ቢች ቦይስ (የባሕር ዳርቻ ታዳጊ ወንዶች) የሚል ስያሜ የተሰጣቸው እነዚህ ታዳጊዎች በዕድሜያቸው የሚበልጧቸውን ሴቶችን ከተማዋን ያስጎበኟቸዋል፣ አብረው ቀንም ሆነ ምሽት ይዝናናሉ።

ከነጮቹ ሴቶች ገንዘብ እንዲሁም በተለያዩ ስፍራዎች ያሉ መዝናኛቸውን ይከፍሉላቸዋል። አንዳንዶቹም ወደ ውጭ አገራት እንደሚወስዷቸው ነገረን።

በስቶን ታውን ታዋቂ በሆኑት ሬስቶራንቶችና የምሽት ክበቦች ፓታሙ (ታቱ)፣ ሲክስ ዲግሪስ ሳውዝ፣ አፍሪካ ሃውስ እና ቢች ሃውስ ከቀኑ ለየት ባለ መልኩ ታዳጊ ወንዶች ከትልልቅ ነጭ ሴቶች ጋር ሲሳሙም ይታያል።

በበርካቶቹ የምሽት ክበቦች ኮኬይንን የመሳሰሉ አደንዛዥ ዕጾችም የተለመዱ ናቸው። በግልጽም መግዛት ይፈልጉ እንደሆነ ሲጠይቁ ይሰማል። መጠጥ ነውር በሆነባት ዛንዚባር በተለየ መልኩ መጠጥ ይንቆረቆራል። በአንዳንድ ሬስቶራንቶች ታዳጊ ሴቶችን በዕድሜ ጠገብ ካሉ ፈረንጅ ወንዶች ጋር ማየትም የተለመደ ነው።

የምሽት ህይወት በስቶን ታውን
የምስሉ መግለጫ,የምሽት ህይወት በስቶን ታውን

የዛንዚባር የምሽት ሕይወት ደመቅ ያለ ነው። ስቶን ታውን ሌቱ አይነጋባትም። የዛንዚባር ታራብ እና ቦንጎ ፍሌቫ፣ አፍሪካን ያጥለቀለቃትን የደቡብ አፍሪካው አማፒያኖ፣ የናይጄሪያው አፍሮ ቢትስ እና የጃይማካው ሬጌ ዳንስ ሆል የምሽቱን ታዳሚ ያወዛውዙታል። የዛንዚባርን ሙዚቃ በዓለም የሙዚቃ መድረክ እንዲታወቅ ያደረገችውን ቢ ኪዱዴን እንዴት ዛንዚባራውያን እንደሚኮሩባት ይናገራሉ።

በየዓመቱ አገሪቷን የሚጎበኙት ኦማኖች ወደነዚህ መጠጥ ቤቶች ባይሄዱም በርካታ ሺሻ ቤቶችን ያዘወትራሉ። ስቶን ታውን በእነዚህ ሁሉ ቱሪስቶች ትጨናነቃለች።

ዛንዚባርን በጎበኘንበት ወቅት የቱሪስቶች ቁጥር አነስተኛ በሆነበት ወቅት ነበር። ሆኖም አንዳንድ ያልተለመዱ ነገሮችን ተመልክተናል።

ባረፍንበት ታሪካዊው እና መቶ ዓመታትን ባስቆጠረው ዳው ፓላስ ሆቴል በነጻ ቁርስ የምትበላ እና ቤት አልባ የሆነች ፈረንጅ ሴት አጋጥማናለች።

የሆቴሉ ምክትል አስተዳደር ቤት የሌላቸው ፈረንጆች ወደ ሆቴሉ እንደሚመጡና አንዳንዴም በሆቴሉ የመጨረሻ ፎቅ ባለው ክፍት ቦታ ላይ ሲያድሩ እንደያዟቸው ነገረን። ይህ ብቻ ሳይሆን በወሲብ ንግድ የሚተዳደሩ ፈረንጅ ሴቶችም አሉ አለን።

የዛንዚባርን ሙዚቃ በዓለም የሙዚቃ መድረክ እንዲታወቅ ያደረገችውን ቢ ኪዱዴን
የምስሉ መግለጫ,የዛንዚባርን ሙዚቃ በዓለም የሙዚቃ መድረክ እንዲታወቅ ያደረገችውን ቢ ኪዱዴን

እርቃንዎን ከወጡ አስጎብኚዎ 2 ሺህ ዶላር ይቀጣል

በአፍሪካ ቁንጮ የቱሪስት መዳረሻ የሚል ስያሜ የተሰጣት እና በውብ ደሴቶቿ የምትታወቀው ዛንዚባር ባለፈው ዓመት 600 ሺህ የሚሆኑ ቱሪስቶችን ተቀብላ ነበር።

ሕዝቧ ሙሉ በሙሉ ሙስሊም በሆነባት ዛንዚባር መሸፋፈን አስገዳጅ ባይሆንም፣ በበርካታ አካባቢዎች ባህሉን እና አገሪቷን ባከበረ መልኩ እንዲለብሱ የሚያስታውሱ ጽሁፎች እዚህም እዚያም ተለጥፈዋል።

በሪዞርቶች እና በሆቴሎች አካባቢ የመዋኛ ልብሶችን መልበስ ቢቻልም እንደ ስቶን ታውን ባሉ አካቢዎች ግን እነዚህ አለባበሶች አይበረታቱም። ከሁለት ዓመታት በፊት የዛንዚባር ቱሪዝም ሚኒስትር በአደባባዮች እርቃን የወጣ ሰው 2 ሺህ ዶላር አስጎብኚዎችን እንደሚቀጣ አስጠንቅቋል።

ይህም በርካቶች ምንም አይነት እራፊ ጨርቅ ሳይጥሉ እርቃናቸው በመታየታቸው ነበር።

በተጨማሪም አልኮል በሕዝብ አደባባዮች ላይ መጠጣት እንዲሁም መሳሳም ሆነ የትኛውንም የተቃራኒ ጾታ ፍቅር ማሳየት ነዋሪዎችን ሊያስቆጣ ስለሚችልም አገሪቷን የሚጎበኙ ቱሪስቶች ከዚህ እንዲቆጠቡ ይመከራሉ።

በስቶን ታውን የሚገኙ ቱሪስቶች

ኢትዮጵያውያንና ስደተኞች የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታ

በዛንዚባር የተካሄደውን የኢትዮጵያ መንግሥት እና የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ውይይት ለመዘገብ ከናይሮቢ ስንነሳ አስበን የነበረው ቪዛ በምንደርስበት ወቅት እንደምናገኝ ነበር። ነገር ግን ለኢትዮጵያውያን ቪዛ ሲደርሱ እንደማይቻል እና የታንዛንያም ኢሚግሬሽን ቪዛ ካላገኙ እንዳታሳፍሯቸው የሚል ትዕዛዝ እንደተሰጣቸውም ከናይሮቢ ተነገረን።

ቢቢሲ ለኬንያም ሆነ ለታንዛንያ ኢሚግሬሽን የጻፋቸው የትብብር ደብዳቤዎች ትርጉም ስላልነበራቸው ያቀድነው በረራ አመለጠን። በዚያኑ ቀን ቪዛ አግኘተን ወደ ዛንዚባር ብናቀናም ቪዛ ማግኘት ለኢትዮጵያውያን እንዲህ የጠበቀበትን ምክንያት መጠየቃችን አልቀረም።

በታንዛንያ የሚዲያ ምናብ ውስጥ ኢትዮጵያውያን ሲባል ጎልቶ የሚሰማው ስደተኞች ብቻ ናቸው የሚለው ነው። ይህንንም ለማየት ብዙ ርቀት መሄድ አያስፈልግም። ኢትዮጵያውያን በታንዛንያ ብሎ ጉግል ላይ ቢፈልግ በርካታ አሰቃቂ ዜናዎች ይወጣሉ።

በጭነት መኪና ታፍነው የሞቱ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች፣ በተጨናነቀ አውራ ጎዳና ላይ አስከሬናቸው ተጥሎ መገኘት፣ መውጪያ ያጡ በሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች፣ በሕገወጥ መንገድ ሲገቡ የተገኙ ኢትዮጵያውያን እስር፣ ፍርድ ቤት መቅረብ፣ ወደ አገር መጋዝ፣ አፈና፣ ሕገወጥ የሰው ዝውውር እና ሌላም ሌላም ሞልቶታል።

አንዳንዶች ኢትዮጵያውያንም አስደንጋጭ ታሪክ ሲናገሩም ይሰማል። በዛንዚባር ያገኘናት ኢትዮጵያዊት በአንድ ወቅት በሕገወጥ መንገድ ገቡ የተባሉ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ሲያዙ የዘጠኝ ዓመት ልጅ አግተው አንለቅም ማለታቸው ተሰምቷል።

ምናልባት በርካታ ስደተኞች ታንዛንያን ወደ ደቡብ አፍሪካ ለመሄድ መሻገሪያ አድርገው መጠቀማቸው የኢሚግሬሽን እና የቪዛ ፖሊሲው ላይ ተጽእኖ አሳርፏል ማለትም ይቻላል። ሆኖም በመጨረሻ አንድ ሰዓት ከ20 ደቂቃ ከበረረን በኋላ አቤይድ አማኒ ካሩሜ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ደረስን።

 አቤይድ አማኒ ካሩሜ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ
የምስሉ መግለጫ,አቤይድ አማኒ ካሩሜ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ

‘አብዮታዊቷ ዛንዚባር’

አየር ማረፊያው የተሰየመው ለ500 ዓመታት ያህል በአረቦች በበላይነት እና ሚሊዮኖች እንደ እቃ የተለወጡባት እና የተሸጡባትን የባርያ ንግድ እንዲከትም ያደረገውን አብዮት ተከትሎ አገሪቷን በመጀመሪያ ፕሬዚዳንትነት የመሩት አቤይድ አማኒ ካሩሜ ስም ነው።

የዛንዚባር የመጨረሻው ሱልጣን ሰር ጃምሺድ ቢንን የገረሰሰው አብዮትም በዛንዚባር ውስጥ ስር ነቀል ለውጥ ላመጡት አቤይድ አማኒ ካሩሜ በር ከፈተ።

በአውሮፓውያኑ ጥር 1964 አብዮቱ ከተቀሰቀሰ ከሦስት ወራት በኋላ የተባበሩት የታንዛንያ ሪፐብሊክ ተመሠረተች። የኅብረቱም መሪ ሶሻሊዝምን በአፍሪካዊ መንገድ የቃኙት እና ተራማጅ የሚባሉት የታንጋኒካው መሪ ጁሊየስ ኔሬሬ የመጀመሪያው ፕሬዚዳንት ሆኑ። ካሩሜ ኅብረቱን መቃወምም ሆነ መንካት እንደ ክህደት በሚታይባት ታንዛንያ ምክትል ፕሬዚዳንት ሆኑ።

ካሩሜ በፓርቲያቸው አፍሮ ሽራዚ ዋና መሥሪያ ቤት ባኦ የተሰኘውን የሙዚቃ መሳሪያ ሲጫወቱ አራት ታጣቂዎች ተኩሰው ገደሏቸው።

ካሩሜ በሥልጣን ዘመናቸው የአረቦች እና የሕንዶችን መሬት ወደ አገሪቱ ብሔራዊ ሃብት በማስገባት ለበርካታ መሬት አልባ ዛንዚባራውያን አከፋፋለዋል።

ሌላኛው ከመቃብር በላይ የነገሰው ስማቸው እና ጥለውት ያለፉት አሻራቸው ቀለም እና ዘር ሳይለዩ ነጻ የትምህርት እና የጤና አገልግሎት ሥርዓት መዘርጋታቸው ነው።

ለዛንዚባር ትልቅ ራዕይ ነበራቸው የሚባሉት አብዮተኛው መሪ፣ በተለይም ንጋምቦ በተሰኘችው በቀድሞ ባሮች በተቆረቆረችው ከተማ ምቼንዚ በሚባለው ሰፈር በሶሻሊስት ርዕዮተ ዓለም የተቃኙ ቤቶችን መገንባታቸው ነው።

ዛንዚባርን  በመጀመሪያ ፕሬዚዳንትነት የመሩት አቤይድ አማኒ ካሩሜ
የምስሉ መግለጫ,ዛንዚባርን በመጀመሪያ ፕሬዚዳንትነት የመሩት አቤይድ አማኒ ካሩሜ

ካሩሜ አብዮተኛ ብቻ ሳይሆኑ አወዛጋቢም ነበር። በ1970 የ64 ዓመቱ ካሩሜ አራት የፋርስ ታዳጊዎች ሊያገቡት ፈቃደኛ ባለመሆናቸው በተለያዩ ባህሎች እና ዘሮች እንዳይጋቡ እንቅፋት ሆነዋል ያላቸውን አስር ወንድ ዘመዶቻቸው እንዲታሰሩ አድርገዋል።

እነዚህን እና ሌሎች ኢታንሼሪ የተሰኙትን የፋርስ ማኅበረሰቦችን ከአገር አስወጣችኋለሁ በሚልም አስፈራሩ። ፕሬዚዳንት ጁሊየስ ኔሬሬ ባደረጉት ተጽእኖ ክሱን ቢተዉትም ከወራት በኋላ አራት ሌላ የፋርስ ሴት ታዳጊዎች የአብዮታዊ ምክር ቤት አባላቱን እንዲያገቡ ተገደዱ። የእነዚህ ታዳጊዎች 11 ዘመዶችም እንዲታሰሩ እና እንዲገረፉ ተወሰነ።

ካሩሜ ስለዚህም ተጠይቀው ሲናገሩ “በቅኝ ግዛት ዘመን አረቦች አፍሪካዊ ዕቁባቶቻቸውን ዝም ብለው ይወስዳሉ፤ አያገቧቸውም ነበር። አሁን እኛ ነን ሥልጣን ላይ ያለነው። ሁኔታው ተቀይሯል” ማለታቸውን ታሪክ ያስታውሳል።

የቻይና ኮሚዩኒስት አብዮተኛው ማኦ ዜዶንግ ‘ሊቀ መንበር ማኦ’ ስም የተገነባው ስታዲየም

አዲሷ ወይም አብዮታዊቷ ዛንዚባር ኮሚኒስቶች እና የአፍሪካ አብዮተኞች እንዲሁም የታሪክ ታላላቆችን ለትምህር ቤቶቿ መጠሪያ፣ ለስታዲየሟ፣ ለሆስፒታሏ በመሰየም ትዘክራቸዋለች።

* ከእነዚህም ውስጥ ኮንጎ ከቤልጂየም ቅኝ ግዛት ቀንበር ከተላቀቀች በኋላ የመጀመሪያው ጠቅላይ ሚኒስትር በነበሩት ፓትሪስ ሉምሙባ የተሰየመ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት

* ሶቭየት ኅብረትን የመሠረተው እና የመጀመሪያው መሪ አብዮተኛው እና ፖለቲከኛው በቭላድሚር ሌኒን የተሰየመ የማስታወሻ ሆስፒታል

* የኢትዮጵያ የሰለሞናዊው ስርወ መንግሥት የመጨረሻው ንጉሥ አጼ ኃይለ ሥላሴን ለማስታወስ የተቋቋመ የሕዝብ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት

* ከነጻነት በኋላ የአልጀሪያ የመጀመሪያ ፕሬዚዳንት፣ የሶሻሊስት ወታደር እና አብዮተኛው በአህመድ ቤን ቤላም ስም ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት አቋቁማለች

* የቻይናን ሕዝባዊ ሪፐብሊክ የመሠረቱት እና የቻይና ኮሚዩኒስት አብዮተኛው ማኦ ዜዶንግ ‘ሊቀ መንበር ማኦ’ ስምም ስታዲየምም ገንብታለች

ዛንዚባር ትልቋ የምሥራቅ አፍሪካ የባሪያ መሸጫ፣ መለወጫ ማዕከል ትባላለች

የባሪያ ማዕከሏ ዛንዚባር

ዛንዚባር ትልቋ የምሥራቅ አፍሪካ የባሪያ መሸጫ፣ መለወጫ ማዕከል ትባላለች። በምዕተ ዓመታት ውስጥም በሚሊዮን የሚቆጠሩ አፍሪካውያን ሕንድ ውቅያኖስን አቋርጠው ወደ አረብ ባሕረ ሰላጤ ግዛቶች ተልከዋል።

ከዛንዚባር ስቶን ታውን በስተሰሜን 20 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኘው ማንጋፕዋኒ ዋሻ ጥልቅ ዋሻ አንዱ ነው። የተፈጥሮ ዋሻው ጥቅጥቅ ያለ ጨለማ ያለው ሲሆን መጎብኘት የቻልነውም ባትሪ ይዘን ነበር።

በርካታ ባሪያዎችን ያከማች የነበረው ይህ ዋሻ በጥልቀት ሲገቡበት ለመተንፈስም ያስቸግራል። አስጎብኚችንም የልብ ህመም ወይም የመተንፈስ ችግር ያለባቸው ሰዎች ይህንን የባሪያዎች ማከማቻ ዋሻ እንዳይጎበኙ ይመከራል አለን።

ትንፋሻችን ለራሳችን እየተቆራረጠ ስለተሰማንም ከሰላሳ ደቂቃ በላይ በዋሻው መቆየት ፈታኝ ነበር። የዋሻው መውጫ ተራራ የሚመስል ቋጥኝ ሲሆን፣ ላብ በላብም ሆነን ነው የወጣነው።

ከዛንዚባር ስቶን ታውን በስተሰሜን 20 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኘው ማንጋፕዋኒ ዋሻ

የ40 ደቂቃው ጦርነት

ታላቋ ብሪታንያ በአውሮፓውያኑ 1890 የዛንዚባር ሱልጣን በእኔ ቁጥጥር ስር ነው አለች። ከስድስት ዓመት በኋላ ገዢው ሱልጣን ሲሞት ካሊድ ኢብን ባርጋሽ ራሱን የዛንዚባር ሱልጣን አድርጎ ሰየመ።

ብሪታንያ ሱልጣኑን ከሥልጣን እንዲለቅ ብትጠይቀውም ፈቃደኛ ባለመሆኑ፣ እንግሊዞች ቤተ መንግሥቱን በማጥቃት ወደ አንግሎ ዛንዚባር ጦርነት አመሩ።

በታሪክ አጭር ጦርነት ተብሎ የሚጠራው ይህ ጦርነት፣ ከአንድ ሰዓት ባነሰ ለአርባ ደቂቃ ብቻ ነበር የተካሄደው።

እንግሊዞች ኻሊድን ካሸነፉ በኋላ ለእነሱ ታዛዥ የሆነውን ሱልጣን በመሾም የእጅ አዙር ቅኝ ግዛታቸውን ቀጠሉ።

በአውሮፓውያኑ 1963 ዛንዚባር የኮመንዌልዝ አባል በመሆን ገዢው ሱልጣን ነጻነት ቢሰጠውም፣ በቀጣዩ ዓመት በዛንዚባር በተነሳው አብዮት ተገለበጠ።ዛንዚባርም ነጻነቷን አወጀች።

ፎሮዳኒ

ተያያዥ ርዕሶች