Mesay Mekonnen 

 · የኦሮሚያ ብልጽግናና የህወሀት ሰዎች በአፍላ ፍቅር እፍ ብለዋል። መሬት ጠቦአቸዋል። ለረጅም ጊዜ ተለያይተው የተገናኙ ፍቅረኛሞች ይመስል ተቃቅፈው፥ ተሳስመው መጥገብ አልቻሉም። ድንበር ባያጎራብታቸው፡ ቋንቋቸው አንድ ባይሆንም፡ ለጊዜው የሚያስጨንቃቸው ሌላ ጉዳይ አይደለም። የተከዳች ኮበሌ ሌላ ፍቅረኛ ይዛ የበፊቱን ለማስቀናት የምታደርገው ብሽሽቅ ይመስላል። ደግሞም ነው። መልዕክቱ ለማን እንደሆነ ግልጽ ነውና። ንፋስ እንኳን መሀላችን አይግባ ብለው በየወንዝ ዳሩ ይማማላሉ፡ በየምክንያቱ ይፈራረማሉ። ፍቅራቸው የጤና እንዳልሆነ ያውቁታል። ከአንጀት ያልዘለቀ፡ አፍ ላይ የሚንከባለል የለበጣ እንደሆነም አልጠፋቸውም። ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ፖለቲካን አስቀያሚ በማድረግ ተወዳዳሪ የላቸውም። የትላንት ወዳጃቸውን አይንህን ለአፈር በማለት የሚሽቀዳደማቸው የለም። ”ኢሱ” በ ”ጌቾ” ሊቀየር የወሰደው ጊዜ ከሁዜን ቦልት ጋር ክብረወሰን የሚጋራ ነው። በፖለቲካ ዘላቂ ወዳጅና ጠላት የለም የሚለው ዝነኛ አባባል ጠፍቶኝ አይደለም። የእሳቸው ፍጥነቱ አስደምሞኝ እንጂ።

የኦሮሚያ ክልል በወሰን ከማይጋራው ብቸኛ የትግራይ ክልል ጋር እንዲህ ያለ መርህና ሞራል አልባ ግንኙነት ሲመሰርት ታሳቢ የተደረገው ጊዜያዊ ጥቅም ነው። ሁለቱ ክልሎችን እንወክላለን የሚሉት ፖለቲከኞቹ ከሚያመሳስላቸው ይልቅ የሚለያዩባቸው ማህበራዊና ባህላዊ መልኮች ብዙ ናቸው። በቋንቋ ቤተሰብ አይገናኙም። በሃይማኖትም ሰፊ ልዩነት አላቸው። ስነልቦናዊ ውቅራቸውም ለየቅል ነው። ሆኖም ኢትዮጵያዊ በመሆናቸው፡ የጋራ ታሪክ ስላላቸው በጋራ ቢቆሙ ሀጢያት ወንጀል አይሆንም። ችግሩ እንዲህ ያፋቀራቸው፡ ዳመና ላይ ያንሳፈፋቸው ሰበብ ምክንያቱ ምንድን ነው የሚለው ነው። ያገናኛቸው ሌላ ምንም አይደለም። ሁለቱም ስለአንድ ወገን ያላቸው ፍጹም ጥላቻ ነው። የፍቅራቸው ቋሚ ማገር ይኸው ነው። ያስተሳሰራቸው ውልም ይኸው ክፉ ደዌ ነው። የፍቅራቸው ኮንትራት መሰረቱ ለአንድ ማህበረሰብ ያላቸው ተመሳሳይ አቋምና ስሜት ነው።

ሰሞኑን ቋንቋችንን በጋራ ለማሳደግ ብለው መፈራረማቸው ተሰምቷል። በተለያዩ የቋንቋ ቤተሰቦች የሚገኙት ኦሮሚኛና ትግርኛ እንዴት አንድ ላይ አብረው እንደሚያድጉ ከእነሱ ብዙ እንማራለን ብዬ እጠብቃለሁ። አስገራሚው ነገር ይህንንም የሚነጋገሩት በአማርኛ ቋንቋ መሆኑ ነው። ፍቅራችሁን ከአይን ያውጣውና ቋንቋችሁ አንድ ላይ አድጎ ለማየት ያብቃን የሚለው መልካም ምኞቴን እኔም በአማርኛ ቋንቋ ብሰድላቸው እንደሚገባቸው አምናለሁ። በእርግጥ መርህ አልባው ግንኙነታቸው እስከትልቅ ጦርነት ማፈንዳት ድርስ እንደሚዘልቅ ምልክቶችን እያየን ነው። በዚህ የታይታና ከአንጀት ያልዘለቀ ፍቅራቸው ተያይዘው የሚገቡበትን ጦርነት ያሸንፉት ይሆን? ጌታዋን የተማመነች አይነት እምነት ኖሮአቸው በአሜሪካን ትከሻ ጦርነቱ ውስጥ ለመግባት ወስነው ሊሆን ይችላል። አሜሪካን አታደርገውም ብዬ ልሟገትላት አልችልም። ስድስት ሀገራትን ስታፈርስ በእኔ እድሜ ያየኋት አሜሪካን ምስራቅ አፍሪካ ላይ ትናንሽ መንግስታት እንዲመጡ በሚያደርገው አዲስ የፖለቲካ አሰላለፍ ውስጥ ዋንኛ ተዋናይ መሆኗ ብዙም አይስደንቀኝም።

አስገራሚውና ቅስም የሚሰብረው ሀቅ ሁለቱ በተራገጡና በተፋቀሩ ቁጥር መከራውን የሚበላው የኦትዮጵያ ህዝብ መሆኑ ነው። ጦርነት ውስጥ ሲገቡ ለጥይት መግዢያ ኪሱ ሲበረበር የነበረው ይኸው የፈረደበት ህዝብ ነው። አሁን ደግሞ አቅር ላይ ሲሆኑ ለጥሎሽ አዋጡ ተበልው ኢትዮጵያውያን ጉሮሮአቸው ተይዟል። ሰሞኑን ከንቲባ አዳነች አቤቤ መቀሌ ደርሰው ሲመለሱ ለትግራይ ግንባታ የገቡትን የ500ሚሊዮን ብር ቃል እንዲሸፍኑላቸው የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪን ቤት ለቤት እያስጨነቁ መሆኑ ተሰምቷል። እሳቸው በሞቅታ ለገቡት ቃል የአዲስ አበባ ህዝብ እዳ ከፋይ የሚሆንበት ነገር ነው ግራ የሚያጋባው። ህዝብ ለህዝብ ተገናኝቶ፡ የምር ሰላም ተፈጥሮ ቢሆን ኖር ከዚህም በላይ ቢደረግ ቁምነገሩ ከፍ ያለ ነው። እነሱ ተጣልተው እነሱው ለታረቁት ሌላው ምን ቤት ሆኖ ነው መከራውን የሚበላው? ሲጣሉ ጥይት ገዝቶ፡ ሲታረቁ ለውስኪያቸው አዋጥቶ እንዴት ይቻላል?

ይሄ የመዋጮ ነገር ሲነሳ የጠቅላይ ሚኒስትሩ መጽሀፍ ኢትዮጵያ ህዝብ ላይ ጎትቶ ያመጣው እዳ ትዝ አለኝ። ከተለያዩ ቦታዎች የሚደርሱኝ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት የጠቅላይ ሚኒስትሩን ”የመደመር ትውልድ” የተሰኘ መጽሀፍ መግዛት ግዴታ ሆኗል። የ2ሺህ ብር ደመውዝተኛ መጽሀፉን 1500ብር እንዲገዛ ተፈርዶበታል። ክልሎች በጠቅላይ ሚኒስትሩ ርካሽ ተወዳጅነትን ለማትረፍ ከፍተኛ ሽያጭ አስመዘገብን የሚል ሪፖርት ለመላክ በሚል የህዝቡን ኪስ እያጠቡት ነው። መጽሀፉን ያልገዛ የሚኒባስ ሹፌር መውጪያ እንደሚከለከል ከወደምስራቅ ሀረርጌ ሰማሁ። ድሬዳዋ ላይ ባለሀብቶች ከ200ሺህ እስከ1ሚሊየን ብር በነፍሰወከፍ እንዲከፍሉ ደብዳቤ ተሰጥቶአአቸዋል። በየቦታው ተመሳሳይ ነው። በአንዳንድ አከባቢዎች የሰውዬውን መጽሀፍ አለመግዛት እንደሚያሳስር ተነግሮኛል። የሚገርመው ለመጽሀፉ ገንዘብ ይከፈላል እንጂ መጽሀፉን ማግኘት አይቻልም። ደምበኛ ዘረፋ ማለት ይህ ነው። በጠራራ ጸሀይ መንግስት ህዝብን ሲዘርፍ! ከዚያ ቴሌቪዥን ላይ ዲያቆን ዳንዔል ይመጣና ”ይህ የአምስት አመት የጠቅላይ ሚኒስትሩ ማስታወሻ ኢትዮጵያን ለዘመናት ከተጣባት ደዌ የሚፈውስ በመሆኑ ለትወልድ ተሰንዶ መቀመጥ አለበት” ይለናል።

ለማንኛውም የኦሮሚያ ብልጽግናና ህወሀቶች ፍቅራችሁን በልኩ አድርጉት። የትላንቱ እርግጫችሁ ተመልሶ የማይመጣበት ምንም ምክንያት የለም። አንዳንዴ ስትጣሉም ስትፋቀሩም ራሳችሁን ብትችሉ ደግሞ ለህዝቡ ትልቅ ውለታ ነው። ለገንዘቡና ለሞቱ ጊዜ የምትፈልጉት ህዝብ የበቃው ዕለት……አልጨርሰውም